2 ዜና መዋዕል 20:15-22
2 ዜና መዋዕል 20:15-22 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
እንዲህም አለ፥ “ይሁዳ ሁሉ፥ በኢየሩሳሌምም የምትኖሩ፥ አንተም ንጉሡ ኢዮሣፍጥ! ስሙ፤ እግዚአብሔር እንዲህ ይላችኋል፦ ሰልፉ የእግዚአብሔር ነው እንጂ የእናንተ አይደለምና ከዚህ ታላቅ ወገን የተነሣ አትፍሩ፤ አትደንግጡም። ነገ በእነርሱ ላይ ውረዱ፤ እነሆ፥ በአሲስ ዐቀበት ይወጣሉ፤ በሸለቆውም መጨረሻ በኢያርሔል ምድረ በዳ ፊት ለፊት ታገኙአቸዋላችሁ። እናንተ የምቷጉ አይደላችሁም፤ ይሁዳና ኢየሩሳሌም ሆይ፥ ተሰለፉ፤ ዝም ብላችሁ ቁሙ፤ የሚሆነውንም የእግዚአብሔርን ማዳን እዩ፤ እግዚአብሔርም ከእናንተ ጋር ነውና አትፍሩ፤ አትደንግጡም፤ ነገም ውጡባቸው።” ኢዮሣፍጥም በምድር ላይ ሰገደ፤ ይሁዳም ሁሉ፥ በኢየሩሳሌምም የሚኖሩ በእግዚአብሔር ፊት ወደቁ፤ ለእግዚአብሔርም ሰገዱ። ሌዋውያንም፥ ከቀዓት ልጆችና ከቆሬ ልጆች የእስራኤልን አምላክ እግዚአብሔርን ከፍ ባለ ታላቅ ድምፅ ያመሰግኑ ዘንድ ቆሙ። ማልደውም ተነሡ፤ ወደ ቴቁሔም ምድረ በዳ ወጡ፤ ሲወጡም ኢዮሣፍጥ ቆመና፥ “ይሁዳና በኢየሩሳሌም የምትኖሩ ሆይ፥ ስሙኝ፤ በአምላካችሁ በእግዚአብሔር እመኑ፥ ትጸኑማላችሁ፤ በነቢዩም እመኑ፤ ነገሩም ይቀናላችኋል” አለ። ከሕዝቡም ጋር ተማክሮ በሠራዊቱ ፊት የሚሄዱትን፥ “ምሕረቱ ለዘለዓለም ነውና እግዚአብሔርን አመስግኑ” የሚሉትንም፥ በቅድስና የሚያመሰግኑትን፥ ለእግዚአብሔርም የሚዘምሩትን መዘምራን አቆመ። ዝማሬውንና ምስጋናውንም በጀመሩ ጊዜ ይሁዳን ሊወጉ በመጡት በአሞንና በሞዓብ ልጆች በሴይርም ተራራ ሰዎች ላይ እግዚአብሔር ኀይልን ሰጣቸው፤ እነርሱም ተመቱ።
2 ዜና መዋዕል 20:15-22 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
እርሱም እንዲህ አለ፤ “ንጉሥ ኢዮሣፍጥ፣ እናንተም በይሁዳና በኢየሩሳሌም የምትኖሩ ሁሉ አድምጡ! እግዚአብሔር እንዲህ ይላችኋል፤ ‘ውጊያው የእግዚአብሔር እንጂ የእናንተ አይደለምና፣ ከዚህ ታላቅ ሰራዊት የተነሣ አትፍሩ፣ አትደንግጡ፣ ነገ በእነርሱ ላይ ውረዱ፤ እነርሱ በጺጽ መተላለፊያ ሽቅብ ይወጣሉ፣ እናንተም በይሩኤል ምድረ በዳ ውስጥ በሸለቆው መጨረሻ ላይ ታገኟቸዋላችሁ። ይህን ጦርነት የምትዋጉት እናንተ አይደላችሁም፤ ይሁዳና ኢየሩሳሌም ሆይ፤ ቦታ ቦታችሁን ያዙ፤ ጸንታችሁ ቁሙ፤ እግዚአብሔር የሚሰጣችሁንም ማዳን እዩ። አትፍሩ፤ አትደንግጡም፤ ነገውኑ ውጡና ግጠሟቸው፤ እግዚአብሔርም ከእናንተ ጋር ይሆናል።’ ” ኢዮሣፍጥ በግንባሩ ወደ መሬት ተደፋ፤ የይሁዳና የኢየሩሳሌምም ሕዝብ ሁሉ በእግዚአብሔር ፊት ወደቁ፤ ሰገዱም። ከቀዓትና ከቆሬ ወገኖች ጥቂት ሌዋውያንም ቆመው፣ እጅግ ከፍ ባለ ድምፅ የእስራኤልን አምላክ እግዚአብሔርን አመሰገኑ። በማግስቱም ጧት በማለዳ ተነሥተው ወደ ቴቁሔ ምድረ በዳ ሄዱ። መንገድ እንደ ጀመሩም ኢዮሣፍጥ ቆሞ፣ “ይሁዳና የኢየሩሳሌም ሕዝብ ሆይ፣ አድምጡኝ! በአምላካችሁ በእግዚአብሔር እመኑ፤ ትጸኑማላችሁ። በነቢያቱም እመኑ፤ ይሳካላችሁማል” አላቸው። ከሕዝቡም ጋር ከተመካከረ በኋላ ከሰራዊቱ ፊት ቀድመው በመሄድ፣ “እግዚአብሔርን አመስግኑ፣ ፍቅሩ ለዘላለም ጸንቶ ይኖራልና” እያሉ ለእግዚአብሔር የሚዘምሩና ስለ ቅድስናውም ክብር የሚያወድሱ ሰዎችን መደበ። መዘመርና ማወደስ እንደ ጀመሩም፣ እግዚአብሔር ይሁዳን በወረሩት በአሞን፣ በሞዓብና በሴይር ተራራ ሰዎች ላይ ድብቅ ጦር አመጣባቸው፤ ተሸነፉም።
2 ዜና መዋዕል 20:15-22 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
እንዲህም አለ “ይሁዳ ሁሉ፥ በኢየሩሳሌም የምትኖሩ፥ አንተም ንጉሡ ኢዮሣፍጥ፥ ስሙ፤ እግዚአብሔር እንዲህ ይላችኋል ‘ሰልፉ የእግዚአብሔር ነው እንጂ የእናንተ አይደለምና ከዚህ ታላቅ ወገን የተነሣ አትፍሩ፤ አትደንግጡም። ነገ በእነርሱ ላይ ውረዱ፤ እነሆ፥ በጺጽ ዓቀበት ይወጣሉ፤ በሸለቆውም መጨረሻ በይሩኤል ምድረ በዳ ፊት ለፊት ታገኙአቸዋላችሁ። እናንተ በዚህ ሰልፍ የምትዋጉ አይደላችሁም፤ ይሁዳና ኢየሩሳሌም ሆይ! ተሰለፉ፤ ዝም ብላችሁ ቁሙ፤ የሚሆነውንም የእግዚአብሔርን መድኃኒት እዩ፤ እግዚአብሔርም ከእናንተ ጋር ነውና አትፍሩ፤ አትደንግጡም፤ ነገም ውጡባቸው።’” ኢዮሣፍጥም በምድር ላይ ተደፋ ይሁዳም ሁሉ በኢየሩሳሌምም የሚኖሩ በእግዚአብሔር ፊት ወደቁ፤ ለእግዚአብሔርም ሰገዱ። ሌዋውያንም፥ የቀዓት ልጆችና የቆሬ ልጆች፥ የእስራኤልን አምላክ እግዚአብሔርን በእጅግ ታላቅ ድምጽ ያመሰገኑት ዘንድ ቆሙ። ማልደውም ተነሡ፤ ወደ ቴቁሔም ምድረ በዳ ወጡ፤ ሲወጡም ኢዮሣፍጥ ቆመና “ይሁዳና በኢየሩሳሌም የምትኖሩ ሆይ! ስሙኝ፤ በአምላካችሁ በእግዚአብሔር እመኑ፤ ትጸኑማላችሁ፤ በነቢያቱም እመኑ፤ ነገሩም ይሰላላችኋል” አለ። ከሕዝቡም ጋር ተማክሮ በሠራዊቱ ፊት የሚሄዱትን “ምሕረቱ ለዘላለም ነውና እግዚአብሔርን አመስግኑ፤” የሚሉትን፥ ጌጠኛ ልብስ ለብሰው የሚያመሰግኑትን፥ ለእግዚአብሔር የሚዘምሩትን መዘምራንን አቆመ። ዝማሬውንና ምስጋናውንም በጀመሩ ጊዜ ይሁዳን ሊወጉ በመጡ በአሞንና በሞዓብ ልጆች በሴይርም ተራራ ሰዎች ላይ እግዚአብሔር ድብቅ ጦርን አመጣባቸው፤ እነርሱም ተመቱ።
2 ዜና መዋዕል 20:15-22 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
ያሐዚኤልም እንዲህ አለ፦ “ንጉሥ ሆይ! እናንተም የይሁዳና የኢየሩሳሌም ሕዝብ በሙሉ፥ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ ‘ተስፋ አትቊረጡ፤ ይህንንም ታላቅ ሠራዊት ለመቋቋም አትፍሩ፤ ጦርነቱ የእግዚአብሔር ነው እንጂ የእናንተ አይደለም፤ ስለዚህ ነገ እነርሱ በጺጽ አጠገብ ወዳለው መተላለፊያ ሲመጡ አደጋ ጣሉባቸው፤ በይሩኤል አጠገብ ወዳለው በረሓማ አገር በሚያመራው ሸለቆ መጨረሻ ጫፍ ላይ ታገኙአቸዋላችሁ። በዚህ ጦርነት ላይ የምትዋጉ እናንተ አይደላችሁም፤ ስፍራ ስፍራችሁን ይዛችሁ ብቻ ጠብቁ፤ እግዚአብሔር ድልን እንደሚያጐናጽፋችሁ ታያላችሁ፤ የይሁዳና የኢየሩሳሌም ሰዎች ሆይ! ሳታመነቱና በፍርሃት ሳትሸበሩ ነገ በቀጥታ ሄዳችሁ ተዋጉ! እግዚአብሔርም ከእናንተ ጋር ይሆናል!’ ” ከዚህ በኋላ ንጉሥ ኢዮሣፍጥና ከእርሱ ጋር የነበሩት የይሁዳና የኢየሩሳሌም ነዋሪዎች ሁሉ በግንባራቸው ወደ መሬት ተደፍተው ለእግዚአብሔር ሰገዱ፤ የቀዓትና የቆሬ ጐሣዎች አባላት የሆኑ ሌዋውያን ቆሙ፤ ድምፃቸውንም ከፍ አድርገው የእስራኤልን አምላክ እግዚአብሔርን አመሰገኑ። ሰዎቹ በማግስቱ ጠዋት በማለዳ ተነሥተው ተቆዓ ተብሎ ከሚጠራ ስፍራ አጠገብ ወደሚገኘው በረሓማ አገር ሄዱ፤ ወደዚያ ለመሄድ ጒዞ በመጀመር ላይ ሳሉም ኢዮሣፍጥ እነርሱን “የይሁዳና የኢየሩሳሌም ሰዎች ሆይ! በአምላካችሁ በእግዚአብሔር ተማመኑ፤ እርሱም ብርታትን ይሰጣችኋል፤ የእግዚአብሔር ነቢያት የሚነግሩአችሁንም እመኑ፤ ይሳካላችኋልም” አላቸው። ንጉሥ ኢዮሣፍጥ ከሕዝቡ ጋር ከተመካከረ በኋላ መዘምራኑ በተቀደሱ በዓላት የሚለብሱአቸውን ካባዎች ለብሰው “ፍቅሩ ለዘለዓለም ነውና እግዚአብሔርን አመስግኑ!” እያሉ በመዘመር በሠራዊቱ ፊት ለፊት እንዲያልፉ አዘዘ። መዘምራኑ መዘመርና ማመስገን በጀመሩ ጊዜ እግዚአብሔር በወራሪዎቹ ሠራዊት ላይ ድብቅ ጦር አምጥቶባቸው፥ ግራ ተጋቡ፤
2 ዜና መዋዕል 20:15-22 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
እንዲህም አለ፦ “ይሁዳ ሁሉ፥ በኢየሩሳሌም የምትኖሩ፥ አንተም ንጉሡ ኢዮሣፍጥ፥ ስሙ፤ ጌታ እንዲህ ይላችኋል፦ ‘ውግያው የጌታ ነው እንጂ የእናንተ አይደለምና ከዚህ ታላቅ ወገን የተነሣ አትፍሩ፥ አትደንግጡም። ነገ በእነርሱ ላይ ውረዱ፤ እነሆ፥ በጺጽ አቀበት ይወጣሉ፤ በሸለቆውም መጨረሻ በይሩኤል ምድረ በዳ ፊት ለፊት ታገኙአቸዋላችሁ። እናንተ በዚህ ውግያ ላይ የምትዋጉ አይደላችሁም፤ ይሁዳና ኢየሩሳሌም ሆይ! ተሰለፉ፥ ጸንታችሁም ቁሙ፥ የሚሆነውንም የጌታን ድል አድራጊነት እዩ፤’ ጌታም ከእናንተ ጋር ነውና አትፍሩ፥ አትደንግጡም፥ ነገም በእነርሱ ላይ ውጡ።” ኢዮሣፍጥም በግንባሩ ወደ ምድር ሰገደ ይሁዳም ሁሉ በኢየሩሳሌምም የሚኖሩ በጌታ ፊት በምድር በግንባራቸው ተደፍተው ለጌታ ሰገዱ። ሌዋውያንም፥ የቀዓት ልጆችና የቆሬ ልጆች፥ የእስራኤልን አምላክ ጌታን እጅግ ታላቅ በሆነ ድምፅ ሊያመሰግኑት ቆሙ። ማልደውም በመነሣት ወደ ቴቁሔ ምድረ በዳ ወጡ፤ ሲወጡም ኢዮሣፍጥ ቆመና እንዲህ አለ፦ “ይሁዳና በኢየሩሳሌም የምትኖሩ ሆይ! ስሙኝ፤ በአምላካችሁ በጌታ እመኑ፥ ትጸኑማላችሁ፤ በነቢያቱም እመኑ፥ ነገሩም ይሳካላችኋል።” ከሕዝቡም ጋር ተማክሮ በሠራዊቱ ፊት የሚሄዱትን፦ “ጽኑ ፍቅሩ ለዘዓለም ነውና ጌታን አመስግኑ” የሚሉትንም ጌጠኛ ልብስም ለብሰው የሚያመሰግኑትን፥ ለጌታም የሚዘምሩትን መዘምራን አቆመ። ዝማሬውንና ምስጋናውንም በጀመሩ ጊዜ ይሁዳን ሊወጉ በመጡ በአሞንና በሙዓብ ልጆች በሴይርም ተራራ ሰዎች ላይ ጌታ ድብቅ ጦርን አመጣባቸው፤ እነርሱም ተሸነፉ።