የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

ሁለተኛ መጽሐፈ ዜና መዋዕል 20:15-22

ሁለተኛ መጽሐፈ ዜና መዋዕል 20:15-22 አማ05

ያሐዚኤልም እንዲህ አለ፦ “ንጉሥ ሆይ! እናንተም የይሁዳና የኢየሩሳሌም ሕዝብ በሙሉ፥ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ ‘ተስፋ አትቊረጡ፤ ይህንንም ታላቅ ሠራዊት ለመቋቋም አትፍሩ፤ ጦርነቱ የእግዚአብሔር ነው እንጂ የእናንተ አይደለም፤ ስለዚህ ነገ እነርሱ በጺጽ አጠገብ ወዳለው መተላለፊያ ሲመጡ አደጋ ጣሉባቸው፤ በይሩኤል አጠገብ ወዳለው በረሓማ አገር በሚያመራው ሸለቆ መጨረሻ ጫፍ ላይ ታገኙአቸዋላችሁ። በዚህ ጦርነት ላይ የምትዋጉ እናንተ አይደላችሁም፤ ስፍራ ስፍራችሁን ይዛችሁ ብቻ ጠብቁ፤ እግዚአብሔር ድልን እንደሚያጐናጽፋችሁ ታያላችሁ፤ የይሁዳና የኢየሩሳሌም ሰዎች ሆይ! ሳታመነቱና በፍርሃት ሳትሸበሩ ነገ በቀጥታ ሄዳችሁ ተዋጉ! እግዚአብሔርም ከእናንተ ጋር ይሆናል!’ ” ከዚህ በኋላ ንጉሥ ኢዮሣፍጥና ከእርሱ ጋር የነበሩት የይሁዳና የኢየሩሳሌም ነዋሪዎች ሁሉ በግንባራቸው ወደ መሬት ተደፍተው ለእግዚአብሔር ሰገዱ፤ የቀዓትና የቆሬ ጐሣዎች አባላት የሆኑ ሌዋውያን ቆሙ፤ ድምፃቸውንም ከፍ አድርገው የእስራኤልን አምላክ እግዚአብሔርን አመሰገኑ። ሰዎቹ በማግስቱ ጠዋት በማለዳ ተነሥተው ተቆዓ ተብሎ ከሚጠራ ስፍራ አጠገብ ወደሚገኘው በረሓማ አገር ሄዱ፤ ወደዚያ ለመሄድ ጒዞ በመጀመር ላይ ሳሉም ኢዮሣፍጥ እነርሱን “የይሁዳና የኢየሩሳሌም ሰዎች ሆይ! በአምላካችሁ በእግዚአብሔር ተማመኑ፤ እርሱም ብርታትን ይሰጣችኋል፤ የእግዚአብሔር ነቢያት የሚነግሩአችሁንም እመኑ፤ ይሳካላችኋልም” አላቸው። ንጉሥ ኢዮሣፍጥ ከሕዝቡ ጋር ከተመካከረ በኋላ መዘምራኑ በተቀደሱ በዓላት የሚለብሱአቸውን ካባዎች ለብሰው “ፍቅሩ ለዘለዓለም ነውና እግዚአብሔርን አመስግኑ!” እያሉ በመዘመር በሠራዊቱ ፊት ለፊት እንዲያልፉ አዘዘ። መዘምራኑ መዘመርና ማመስገን በጀመሩ ጊዜ እግዚአብሔር በወራሪዎቹ ሠራዊት ላይ ድብቅ ጦር አምጥቶባቸው፥ ግራ ተጋቡ፤