1 ተሰሎንቄ 4:1-9
1 ተሰሎንቄ 4:1-9 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
እንግዲህ በቀረውስ ወንድሞች ሆይ! ልትመላለሱ እግዚአብሔርንም ደስ ልታሰኙ እንዴት እንደሚገባችሁ ከእኛ ዘንድ እንደ ተቀበላችሁ፥ እናንተ ደግሞ እንደምትመላለሱ፥ ከፊት ይልቅ ትበዙ ዘንድ በጌታ በኢየሱስ እንለምናችኋለን፤ እንመክራችሁማለን። በጌታ በኢየሱስ የትኛውን ትእዛዝ እንደ ሰጠናችሁ ታውቃላችሁና። ይህ የእግዚአብሔር ፈቃድ እርሱም መቀደሳችሁ ነውና፤ ከዝሙት እንድትርቁ፥ እግዚአብሔርን እንደማያውቁ አሕዛብ በፍትወት ምኞት አይደለም እንጂ፤ ከእናንተ እያንዳንዱ የራሱን ዕቃ በቅድስናና በክብር ያገኝ ዘንድ እንዲያውቅ፤ አስቀድመን ደግሞ እንዳልናችሁና እንደ መሰከርንላችሁ፥ ጌታ ስለዚህ ነገር ሁሉ የሚበቀል ነውና፥ ማንም በዚህ ነገር አይተላለፍ፤ ወንድሙንም አያታልል። ለርኵሰት ሳይሆን እግዚአብሔር በቅድስና ጠርቶናልና። እንግዲህ የማይቀበል ሰውን ያልተቀበለ አይደለም፤ መንፈስ ቅዱስን በእናንተ እንዲኖር የሰጠውን እግዚአብሔርን ነው እንጂ። እናንተ ራሳችሁ እርስ በርሳችሁ ልትዋደዱ በእግዚአብሔር ተምራችኋልና፥ ስለ ወንድማማች መዋደድ ማንም ይጽፍላችሁ ዘንድ አያስፈልጋችሁም፤
1 ተሰሎንቄ 4:1-9 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
በቀረውስ ወንድሞች ሆይ፤ እግዚአብሔርን ደስ ለማሠኘት እንዴት መኖር እንደሚገባችሁ አስተምረናችኋል፤ በርግጥም እንደዚያው እየኖራችሁ ነው። ስለ ሆነም በጌታ በኢየሱስ የምንለምናችሁና የምንመክራችሁ ከዚህ በበለጠ ሁኔታ በዚሁ እንድትገፉበት ነው። በጌታ በኢየሱስ ሥልጣን ምን ዐይነት ትእዛዝ እንደ ሰጠናችሁ ታውቃላችሁ። የእግዚአብሔር ፈቃድ ከዝሙት ርቃችሁ እንድትቀደሱ ነው፤ ደግሞም እያንዳንዱ የገዛ ሰውነቱን በቅድስናና በክብር መያዝ እንዳለበት እንዲያውቅ ነው፤ ይህም እግዚአብሔርን እንደማያውቁ አሕዛብ በፍትወተ ሥጋ ምኞት አይሁን። በዚህም ነገር ማንም ተላልፎ ወንድሙን አያታልል፤ ምክንያቱም ከዚህ በፊት እንደ ነገርናችሁና እንዳስጠነቀቅናችሁ ጌታ እንደ እነዚህ ያለውን ኀጢአት ሁሉ የሚፈጽሙትን ይበቀላል፤ እግዚአብሔር በቅድስና እንድንመላለስ እንጂ ለርኩሰት አልጠራንምና። እንግዲህ ይህን ምክር ንቆ የማይቀበል፣ የናቀው ቅዱስ መንፈሱን የሰጣችሁን እግዚአብሔርን እንጂ ሰውን አይደለም። ስለ ወንድማማች መዋደድ ማንም እንዲጽፍላችሁ አያስፈልግም፤ ምክንያቱም እርስ በርሳችሁ እንድትዋደዱ እናንተ ራሳችሁ ከእግዚአብሔር ተምራችኋልና።
1 ተሰሎንቄ 4:1-9 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
እንግዲህ በቀረውስ፥ ወንድሞች ሆይ፥ ልትመላለሱ እግዚአብሔርንም ደስ ልታሰኙ እንዴት እንደሚገባችሁ ከእኛ ዘንድ እንደ ተቀበላችሁ፥ እናንተ ደግሞ እንደምትመላለሱ፥ ከፊት ይልቅ ትበዙ ዘንድ በጌታ በኢየሱስ እንለምናችኋለን እንመክራችሁማለን። በጌታ በኢየሱስ የትኛውን ትእዛዝ እንደ ሰጠናችሁ ታውቃላችሁና። ይህ የእግዚአብሔር ፈቃድ እርሱም መቀደሳችሁ ነውና፤ ከዝሙት እንድትርቁ፥ እግዚአብሔርን እንደማያውቁ አሕዛብ በፍትወት ምኞት አይደለም እንጂ፥ ከእናንተ እያንዳንዱ የራሱን ዕቃ በቅድስናና በክብር ያገኝ ዘንድ እንዲያውቅ፤ አስቀድመን ደግሞ እንዳልናችሁና እንደ መሰከርንላችሁ፥ ጌታ ስለዚህ ነገር ሁሉ የሚበቀል ነውና ማንም በዚህ ነገር አይተላለፍ ወንድሙንም አያታልል። ለርኵሰት ሳይሆን እግዚአብሔር በቅድስና ጠርቶናልና። እንግዲህ የሚጥል ሰውን የጣለ አይደለም፥ መንፈስ ቅዱስን በእናንተ እንዲኖር የሰጠውን እግዚአብሔርን ነው እንጂ። እናንተ ራሳችሁ እርስ በርሳችሁ ልትዋደዱ በእግዚአብሔር ተምራችኋልና ስለ ወንድማማች መዋደድ ማንም ይጽፍላችሁ ዘንድ አያስፈልጋችሁም፤
1 ተሰሎንቄ 4:1-9 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
በመጨረሻም ወንድሞች ሆይ! እግዚአብሔርን ለማስደሰት እንዴት መኖር እንደሚገባችሁ ከእኛ ተምራችኋል፤ አሁንም የምትኖሩት እንዲሁ ነው፤ በጌታ በኢየሱስ ስም የምንለምናችሁና የምንመክራችሁም ከዚህ በፊት ካደረጋችሁት ይበልጥ እንድታደርጉ ነው። በጌታ ኢየሱስ ስም ምን ዐይነት መመሪያ እንደ ሰጠናችሁ ታውቃላችሁ። የእግዚአብሔር ፈቃድ እናንተ እንድትቀደሱና ከዝሙት እንድትርቁ ነው። ከእናንተ እያንዳንዱ ሚስቱን በቅድስናና በክብር ጠብቆ መያዝን ይወቅ። እግዚአብሔርን እንደማያውቁ አሕዛብ የፍትወት ምኞት አይኑረው። በዚህ ነገር ማንም ሰው አይተላለፍ፤ ሌላ አማኝን አይበድል፤ ከዚህ በፊት እንደ ነገርናችሁና እንዳስጠነቀቅናችሁ እነዚህን ነገሮች የሚያደርጉትን ጌታ ይቀጣቸዋል። እግዚአብሔር የጠራን በቅድስና እንድንኖር ነው እንጂ በርኲሰት እንድንኖር አይደለም። ስለዚህ ይህን ምክር የሚቃወም፥ የሚቃወመው ቅዱስ መንፈሱን የሚሰጣችሁን እግዚአብሔርን እንጂ ሰውን አይደለም። እርስ በርስ ስለ መዋደድ እናንተ ራሳችሁ ከእግዚአብሔር ስለ ተማራችሁ ስለዚህ ጉዳይ ማንም ሊጽፍላችሁ አያስፈልግም።
1 ተሰሎንቄ 4:1-9 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
እንግዲህ በቀረውስ ወንድሞች ሆይ! እግዚአብሔርን ለማስደሰት እንዴት መመላለስ እንደሚገባችሁ ከእኛ ዘንድ ተቀብላችኋል፤ በእርግጥም እየተመላለሳችሁ ነው፤ ከዚህም በበለጠ አብዝታችሁ እንድታደርጉት በጌታ በኢየሱስ እንለምናችኋለን፤ እንመክራችኋለንም። በጌታ በኢየሱስ ስም ምን ዓይነት መመሪያዎች እንደ ሰጠናችሁ ታውቃላችሁና። ይህ የእግዚአብሔር ፈቃድ ነው፥ እርሱም መቀደሳችሁ፥ ከዝሙትም መራቃችሁ ነው፤ እያንዳንዳችሁም የራሳችሁን አካል በቅድስናና በክብር እንዴት መቆጣጠር እንደምትችሉ እወቁ፥ ይህን ስታደርጉ ግን እግዚአብሔርን እንደማያውቁ አሕዛብ በፍትወት ምኞት መሆን የለበትም፤ አስቀድመን ደግሞ እንደ ነገርናችሁና እንደ መሰከርንላችሁ፥ ጌታ ስለዚህ ነገር ሁሉ የሚበቀል ነውና፥ ማንም በዚህ ነገር አይተላለፍ፤ ወንድሙንም አያታልል። ለርኩሰት ሳይሆን እግዚአብሔር በቅድስና ጠርቶናልና። ስለዚህ ይህን የማይቀበል፥ የማይቀበለው፥ ሰውን ሳይሆን፥ ቅዱስ መንፈሱን ደግሞም የሰጠንን እግዚአብሔርን ነው። እናንተ ራሳችሁ የእርስ በእርስ መዋደድን በእግዚአብሔር ተምራችኋልና፥ ስለ ወንድማማች መዋደድ ማንም ሊጽፍላችሁ አያስፈልጋችሁም፤