የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

1 ተሰሎንቄ 4

4
እግዚአብሔርን ደስ የሚያሰኝ አኗኗር
1በቀረውስ ወንድሞች ሆይ፤ እግዚአብሔርን ደስ ለማሰኘት እንዴት መኖር እንደሚገባችሁ አስተምረናችኋል፤ በርግጥም እንደዚያው እየኖራችሁ ነው። ስለሆነም በጌታ በኢየሱስ የምንለምናችሁና የምንመክራችሁ ከዚህ በበለጠ ሁኔታ በዚሁ እንድትገፉበት ነው። 2በጌታ በኢየሱስ ሥልጣን ምን ዐይነት ትእዛዝ እንደ ሰጠናችሁ ታውቃላችሁ።
3የእግዚአብሔር ፈቃድ ከዝሙት ርቃችሁ እንድትቀደሱ ነው፤ 4ደግሞም እያንዳንዱ የገዛ ሰውነቱን በቅድስናና በክብር መያዝ#4፥4 ወይም ከገዛ ሚስቱ ጋር መኖርን መማር ወይም ሚስት ለማግኘት መማር እንዳለበት እንዲያውቅ ነው፤ 5ይህም እግዚአብሔርን እንደማያውቁ አሕዛብ በፍትወተ ሥጋ ምኞት አይሁን። 6በዚህም ነገር ማንም ተላልፎ ወንድሙን አያታልል፤ ምክንያቱም ከዚህ በፊት እንደ ነገርናችሁና እንዳስጠነቀቅናችሁ ጌታ እንደ እነዚህ ያለውን ኀጢአት ሁሉ የሚፈጽሙትን ይበቀላል፤ 7እግዚአብሔር በቅድስና እንድንመላለስ እንጂ ለርኩሰት አልጠራንምና። 8እንግዲህ ይህን ምክር ንቆ የማይቀበል፣ የናቀው ቅዱስ መንፈሱን የሰጣችሁን እግዚአብሔርን እንጂ ሰውን አይደለም።
9ስለ ወንድማማች መዋደድ ማንም እንዲጽፍላችሁ አያስፈልግም፤ ምክንያቱም እርስ በርሳችሁ እንድትዋደዱ እናንተ ራሳችሁ ከእግዚአብሔር ተምራችኋልና።
10በመላዪቱ መቄዶንያ የሚገኙትን ወንድሞች ሁሉ እንደምትወድዷቸው የታወቀ ነው፤ ነገር ግን ወንድሞች ሆይ፤ ከዚህ በበለጠ እንድታደርጉት እንመክራችኋለን።
11ከዚህ በፊት እንዳዘዝናችሁ በገዛ እጃችሁ ሥሩ፤ በጸጥታ ኑሩ፤ በራሳችሁ ጕዳይ ላይ ብቻ አተኵሩ። 12ይኸውም፣ በዕለት ተለት ኑሯችሁ በውጭ ባሉት ዘንድ እንዲያስከብራችሁና በማንም ሰው ላይ ሸክም እንዳትሆኑ ነው።
የጌታ ዳግም ምጽአት
13ወንድሞች ሆይ፤ አንቀላፍተው ስላሉ ሰዎች ሳታውቁ እንድትቀሩ አንፈልግም፤ ደግሞም ተስፋ እንደሌላቸው እንደ ሌሎች ሰዎች እንድታዝኑ አንሻም። 14ኢየሱስ እንደ ሞተና እንደ ተነሣ ካመንን፣ በኢየሱስ ሆነው ያንቀላፉትን እግዚአብሔር ከእርሱ ጋር እንደዚሁ ያመጣቸዋል። 15በጌታ ቃል የምንላችሁ ይህን ነው፤ እኛ በሕይወት ያለንና ጌታ እስኪመጣ ድረስ የምንቀር ያንቀላፉትን አንቀድምም፤ 16ጌታ ራሱ በታላቅ ትእዛዝ፣ በመላእክት አለቃ ድምፅና በእግዚአብሔር የመለከት ድምፅ ከሰማይ ይወርዳልና። በክርስቶስ የሞቱትም አስቀድመው ይነሣሉ። 17ከዚያም በኋላ እኛ የቀረነው፣ በሕይወትም የምንኖረው ጌታን በአየር ላይ ለመቀበል ከእነርሱ ጋር በደመና እንነጠቃለን፤ በዚህም መሠረት ለዘላለም ከጌታ ጋር እንሆናለን። 18ስለዚህ በዚህ ቃል እርስ በርሳችሁ ተጽናኑ።

Currently Selected:

1 ተሰሎንቄ 4: NASV

ማድመቅ

Share

Copy

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ