የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

1 ተሰሎንቄ ሰዎች 4

4
እግዚአብሔርን ደስ የሚያሰኝ ሕይወት
1በመጨረሻም ወንድሞች ሆይ! እግዚአብሔርን ለማስደሰት እንዴት መኖር እንደሚገባችሁ ከእኛ ተምራችኋል፤ አሁንም የምትኖሩት እንዲሁ ነው፤ በጌታ በኢየሱስ ስም የምንለምናችሁና የምንመክራችሁም ከዚህ በፊት ካደረጋችሁት ይበልጥ እንድታደርጉ ነው። 2በጌታ ኢየሱስ ስም ምን ዐይነት መመሪያ እንደ ሰጠናችሁ ታውቃላችሁ። 3የእግዚአብሔር ፈቃድ እናንተ እንድትቀደሱና ከዝሙት እንድትርቁ ነው። 4ከእናንተ እያንዳንዱ ሚስቱን በቅድስናና በክብር ጠብቆ መያዝን ይወቅ። 5እግዚአብሔርን እንደማያውቁ አሕዛብ የፍትወት ምኞት አይኑረው። 6በዚህ ነገር ማንም ሰው አይተላለፍ፤ ሌላ አማኝን አይበድል፤ ከዚህ በፊት እንደ ነገርናችሁና እንዳስጠነቀቅናችሁ እነዚህን ነገሮች የሚያደርጉትን ጌታ ይቀጣቸዋል። 7እግዚአብሔር የጠራን በቅድስና እንድንኖር ነው እንጂ በርኲሰት እንድንኖር አይደለም። 8ስለዚህ ይህን ምክር የሚቃወም፥ የሚቃወመው ቅዱስ መንፈሱን የሚሰጣችሁን እግዚአብሔርን እንጂ ሰውን አይደለም።
9እርስ በርስ ስለ መዋደድ እናንተ ራሳችሁ ከእግዚአብሔር ስለ ተማራችሁ ስለዚህ ጉዳይ ማንም ሊጽፍላችሁ አያስፈልግም። 10በመላ መቄዶንያ ያሉትንም ወንድሞች ሁሉ ትወዳላችሁ፤ ሆኖም ወንድሞች ሆይ፥ አሁን የምንመክራችሁ ይበልጥ እንድትወዱ ነው፤ 11በጸጥታም ለመኖር እንድትጣጣሩ እና የራሳችሁን ጉዳይ እንድታስቡ ከዚህ በፊት እንዳዘዝናችሁም በገዛ እጃችሁ እንድትሠሩ ነው። 12በዚህ ዐይነት በማያምኑት ሰዎች ዘንድ የተከበራችሁ ትሆናላችሁ፤ የማንም ጥገኛ አትሆኑም።
ጌታ ተመልሶ በሚመጣበት ጊዜ የሕያዋንና የሙታን ሁኔታ
13ወንድሞች ሆይ! ተስፋ እንደሌላቸው ሰዎች እንዳታዝኑ ስለ ሞቱት ሰዎች እውነቱን እንድታውቁ እንወዳለን። 14ኢየሱስ እንደ ሞተና ከሞትም እንደ ተነሣ እናምናለን፤ ስለዚህ በኢየሱስ አምነው የሞቱትን እግዚአብሔር ከእርሱ ጋር ያመጣቸዋል።
15ከጌታ በተቀበልነው ቃል መሠረት የምንነግራችሁ ይህ ነው፤ ጌታ እስከሚመጣበት ጊዜ ድረስ ሕያዋን ሆነን የምንቈይ የሞቱትን አንቀድምም። 16የትእዛዝ ድምፅ፥ የመላእክት አለቃ ድምፅ፥ የእግዚአብሔር እምቢልታም ይሰማል፤ ጌታ ራሱም በእነዚህ ታጅቦ ከሰማይ ይወርዳል፤ በክርስቶስ አምነው የሞቱትም አስቀድመው ይነሣሉ። 17ከዚህ በኋላ እኛ በሕይወት የምንገኘው ጌታን በአየር ላይ ለመገናኘት ከእነርሱ ጋር በደመና እንነጠቃለን፤ ለዘለዓለምም ከጌታ ጋር እንሆናለን። #1ቆሮ. 15፥51-52። 18ስለዚህ በዚህ ቃል እርስ በርሳችሁ ተጽናኑ።

ማድመቅ

Share

Copy

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ