1ኛ ወደ ተሰሎንቄ ሰዎች 4:1-9

1ኛ ወደ ተሰሎንቄ ሰዎች 4:1-9 መቅካእኤ

እንግዲህ በቀረውስ ወንድሞች ሆይ! እግዚአብሔርን ለማስደሰት እንዴት መመላለስ እንደሚገባችሁ ከእኛ ዘንድ ተቀብላችኋል፤ በእርግጥም እየተመላለሳችሁ ነው፤ ከዚህም በበለጠ አብዝታችሁ እንድታደርጉት በጌታ በኢየሱስ እንለምናችኋለን፤ እንመክራችኋለንም። በጌታ በኢየሱስ ስም ምን ዓይነት መመሪያዎች እንደ ሰጠናችሁ ታውቃላችሁና። ይህ የእግዚአብሔር ፈቃድ ነው፥ እርሱም መቀደሳችሁ፥ ከዝሙትም መራቃችሁ ነው፤ እያንዳንዳችሁም የራሳችሁን አካል በቅድስናና በክብር እንዴት መቆጣጠር እንደምትችሉ እወቁ፥ ይህን ስታደርጉ ግን እግዚአብሔርን እንደማያውቁ አሕዛብ በፍትወት ምኞት መሆን የለበትም፤ አስቀድመን ደግሞ እንደ ነገርናችሁና እንደ መሰከርንላችሁ፥ ጌታ ስለዚህ ነገር ሁሉ የሚበቀል ነውና፥ ማንም በዚህ ነገር አይተላለፍ፤ ወንድሙንም አያታልል። ለርኩሰት ሳይሆን እግዚአብሔር በቅድስና ጠርቶናልና። ስለዚህ ይህን የማይቀበል፥ የማይቀበለው፥ ሰውን ሳይሆን፥ ቅዱስ መንፈሱን ደግሞም የሰጠንን እግዚአብሔርን ነው። እናንተ ራሳችሁ የእርስ በእርስ መዋደድን በእግዚአብሔር ተምራችኋልና፥ ስለ ወንድማማች መዋደድ ማንም ሊጽፍላችሁ አያስፈልጋችሁም፤