1 ተሰሎንቄ ሰዎች 4:1-9

1 ተሰሎንቄ ሰዎች 4:1-9 አማ05

በመጨረሻም ወንድሞች ሆይ! እግዚአብሔርን ለማስደሰት እንዴት መኖር እንደሚገባችሁ ከእኛ ተምራችኋል፤ አሁንም የምትኖሩት እንዲሁ ነው፤ በጌታ በኢየሱስ ስም የምንለምናችሁና የምንመክራችሁም ከዚህ በፊት ካደረጋችሁት ይበልጥ እንድታደርጉ ነው። በጌታ ኢየሱስ ስም ምን ዐይነት መመሪያ እንደ ሰጠናችሁ ታውቃላችሁ። የእግዚአብሔር ፈቃድ እናንተ እንድትቀደሱና ከዝሙት እንድትርቁ ነው። ከእናንተ እያንዳንዱ ሚስቱን በቅድስናና በክብር ጠብቆ መያዝን ይወቅ። እግዚአብሔርን እንደማያውቁ አሕዛብ የፍትወት ምኞት አይኑረው። በዚህ ነገር ማንም ሰው አይተላለፍ፤ ሌላ አማኝን አይበድል፤ ከዚህ በፊት እንደ ነገርናችሁና እንዳስጠነቀቅናችሁ እነዚህን ነገሮች የሚያደርጉትን ጌታ ይቀጣቸዋል። እግዚአብሔር የጠራን በቅድስና እንድንኖር ነው እንጂ በርኲሰት እንድንኖር አይደለም። ስለዚህ ይህን ምክር የሚቃወም፥ የሚቃወመው ቅዱስ መንፈሱን የሚሰጣችሁን እግዚአብሔርን እንጂ ሰውን አይደለም። እርስ በርስ ስለ መዋደድ እናንተ ራሳችሁ ከእግዚአብሔር ስለ ተማራችሁ ስለዚህ ጉዳይ ማንም ሊጽፍላችሁ አያስፈልግም።