1 ሳሙኤል 19:1-17

1 ሳሙኤል 19:1-17 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)

ሳኦ​ልም ለልጁ ለዮ​ና​ታ​ንና ለብ​ላ​ቴ​ኖቹ ሁሉ ዳዊ​ትን ይገ​ድሉ ዘንድ ነገ​ራ​ቸው። የሳ​ኦል ልጅ ዮና​ታን ግን ዳዊ​ትን እጅግ ይወ​ድ​ደው ነበር። ዮና​ታ​ንም፥ “አባቴ ሳኦል ሊገ​ድ​ልህ ፈል​ጎ​አል፤ አሁን እን​ግ​ዲህ ለነ​ገው ተጠ​ን​ቅ​ቀህ ተሸ​ሸግ፤ በስ​ው​ርም ተቀ​መጥ። እኔም እወ​ጣ​ለሁ፤ አን​ተም ባለ​ህ​በት እርሻ በአ​ባቴ አጠ​ገብ እቆ​ማ​ለሁ፤ ስለ አን​ተም ለአ​ባቴ እነ​ግ​ረ​ዋ​ለሁ፤ የሆ​ነ​ው​ንም አይቼ እነ​ግ​ር​ሃ​ለሁ” ብሎ ለዳ​ዊት ነገ​ረው። ዮና​ታ​ንም ለአ​ባቱ ለሳ​ኦል ስለ ዳዊት መል​ካም ተና​ገረ እን​ዲ​ህም አለው፥ “እርሱ አል​በ​ደ​ለ​ህ​ምና፥ ሥራ​ውም ለአ​ንተ እጅግ መል​ካም ሆኖ​አ​ልና ንጉሡ ባሪ​ያ​ውን ዳዊ​ትን አይ​በ​ድ​ለው፤ ነፍ​ሱ​ንም በእጁ ጥሎ ፍል​ስ​ጥ​ኤ​ማ​ዊ​ዉን ገደለ፤ እግ​ዚ​አ​ብ​ሔ​ርም በእ​ርሱ ታላቅ መድ​ኀ​ኒት አደ​ረገ፤ እስ​ራ​ኤ​ልም ሁሉ አይ​ተው ደስ አላ​ቸው፤ በከ​ንቱ ዳዊ​ትን ትገ​ድ​ለው ዘንድ ስለ​ምን በን​ጹሕ ደም ላይ ትበ​ድ​ላ​ለህ?” ሳኦ​ልም የዮ​ና​ታ​ንን ቃል ሰማ፤ ሳኦ​ልም፥ “ሕያው እግ​ዚ​አ​ብ​ሔ​ርን! ዳዊት አይ​ገ​ደ​ልም” ብሎ ማለ። ዮና​ታ​ንም ዳዊ​ትን ጠርቶ ይህን ነገር ሁሉ ነገ​ረው፤ ዮና​ታ​ንም ዳዊ​ትን ወደ ሳኦል አመ​ጣው፤ እንደ ቀድ​ሞ​ውም በፊቱ ነበረ። ደግ​ሞም ጦር​ነት ሆነ፤ ዳዊ​ትም ወጥቶ ከፍ​ል​ስ​ጥ​ኤ​ማ​ው​ያን ጋር ተዋጋ፤ ታላቅ ግዳ​ይም ገደ​ላ​ቸው፤ ከፊ​ቱም ሸሹ። ሳኦ​ልም ጦሩን ይዞ በቤቱ ተቀ​ምጦ ሳለ ክፉ መን​ፈስ ከእ​ግ​ዚ​አ​ብ​ሔር ዘንድ ያዘው። ዳዊ​ትም በእጁ በገና ይመታ ነበር። ሳኦ​ልም ዳዊ​ትን ከግ​ንብ ጋር ያጣ​ብ​ቀው ዘንድ ጦሩን ወረ​ወረ፤ ዳዊ​ትም ከሳ​ኦል ፊት ዘወር አለ፤ ጦሩም በግ​ንቡ ውስጥ ተተ​ከለ፤ በዚ​ያም ሌሊት ዳዊት ሸሸቶ አመ​ለጠ። ሳኦ​ልም ዳዊ​ትን ጠበ​ቀው፤ በነ​ጋው እን​ዲ​ገ​ድ​ሉት መል​እ​ክ​ተ​ኞ​ቹን ወደ ዳዊት ቤት ላከ፤ ሚስ​ቱም ሜል​ኮል፥ “በዚ​ህች ሌሊት ነፍ​ስ​ህን ካላ​ዳ​ንህ ነገ ትገ​ደ​ላ​ለህ” ብላ ነገ​ረ​ችው። ሜል​ኮ​ልም ዳዊ​ትን በመ​ስ​ኮት አወ​ረ​ደ​ችው፤ ሄደም፤ ሸሽ​ቶም አመ​ለጠ። ሜል​ኮ​ልም ተራ​ፊ​ምን ወስዳ በአ​ልጋ ላይ አኖ​ረ​ችው፤ በራ​ስ​ጌ​ውም ጕን​ጕን የፍ​የል ጠጕር አደ​ረ​ገች፤ በል​ብ​ስም ከደ​ነ​ችው። ሳኦ​ልም ዳዊ​ትን ይዘው እን​ዲ​ያ​መ​ጡት መል​እ​ክ​ተ​ኞ​ችን ላከ፤ እር​ስ​ዋም ታሞ​አል አለ​ቻ​ቸው። ሳኦ​ልም፥ “እገ​ድ​ለው ዘንድ ዳዊ​ትን ከነ​አ​ል​ጋው” አም​ጡ​ልኝ ብሎ መል​እ​ክ​ተ​ኞ​ቹን ወደ ዳዊት ላከ። መል​እ​ክ​ተ​ኞ​ቹም በገቡ ጊዜ እነሆ፥ ተራ​ፊ​ሙን በአ​ል​ጋው ላይ አገኙ፤ በራ​ስ​ጌ​ውም ጕን​ጕን የፍ​የል ጠጕር ነበረ። ሳኦ​ልም ሜል​ኮ​ልን አላት፥ “ስለ​ምን እን​ዲህ አታ​ለ​ል​ሽኝ? ጠላ​ቴን አስ​ኰ​በ​ለ​ልሽ፤ እን​ዲ​ያ​መ​ል​ጥም አደ​ረ​ግ​ሽው?” ሜል​ኮ​ልም ለሳ​ኦል፥ “እርሱ፦ አው​ጥ​ተሽ ስደ​ጂኝ፤ አለ​ዚያ እገ​ድ​ል​ሻ​ለሁ አለኝ” አለ​ችው።

1 ሳሙኤል 19:1-17 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

ሳኦል ዳዊትን እንዲገድሉት ለልጁ ለዮናታንና ለባልሟሎቹ ነገራቸው። ዮናታን ግን ዳዊትን እጅግ ይወድደው ነበር፣ እንዲህ ሲል አስጠነቀቀው፤ “አባቴ ሳኦል ሊገድልህ አጋጣሚ እየፈለገ ነው፤ ነገ ጧት ተጠንቀቅ፤ ወደ አንድ መደበቂያ ቦታም ሂድ፤ በዚያም ቈይ። እኔም እወጣና አንተ ባለህበት ዕርሻ ከአባቴ አጠገብ እቆማለሁ፤ ስለ አንተም አነጋግረዋለሁ፤ የተረዳሁትንም እነግርሃለሁ።” ዮናታን ለአባቱ ለሳኦል ስለ ዳዊት እንዲህ ሲል መልካም ነገር ተናገረ፣ “ንጉሥ በአገልጋዩ በዳዊት ላይ ክፉ ነገር አያድርግ፤ እርሱ አልበደለህም፤ ያደረገውም ነገር በእጅጉ ጠቅሞሃል። ዳዊት ፍልስጥኤማዊውን የገደለው በገዛ ሕይወቱ ቈርጦ ነው። እግዚአብሔር ለመላው እስራኤል ታላቅ ድልን አቀዳጀ፤ አንተም አይተህ ደስ አለህ። ታዲያ እርሱን በከንቱ በመግደል ዳዊትን በመሰለ ንጹሕ ሰው ላይ ለምን በደል ትፈጽማለህ?” ሳኦልም ዮናታንን ካዳመጠው በኋላ፣ “ሕያው እግዚአብሔርን! ዳዊት አይገደልም” ብሎ ማለ። ስለዚህም ዮናታን ዳዊትን ጠርቶ የተባባሉትን ሁሉ ነገረው፤ ወደ ሳኦልም አመጣው፤ ዳዊትም እንደ ቀድሞው በፊቱ ቆመ። እንደ ገና ሌላ ጦርነት ተነሣ፤ ዳዊትም ወጥቶ ፍልስጥኤማውያንን ወጋቸው፤ ከፊቱም እስኪሸሹ ድረስ እጅግ መታቸው። ነገር ግን ሳኦል ጦሩን ይዞ በቤቱ ተቀምጦ ሳለ፣ ከእግዚአብሔር ዘንድ ክፉ መንፈስ መጣበት፤ ዳዊት በገናውን ይደረድር ነበር፣ ሳኦልም ከግድግዳው ጋራ ሊያጣብቀው ጦሩን ወረወረበት፤ ነገር ግን ዳዊት ዘወር በማለቱ ሳኦል የወረወረው ጦር በግድግዳው ላይ ተሰካ። በዚያች ሌሊት ዳዊት ሸሽቶ አመለጠ። ሳኦልም የዳዊትን ቤት ከብበው በማለዳ እንዲገድሉት ሰዎችን ላከ። የዳዊት ሚስት ሜልኮል ግን፣ “ሕይወትህን ለማትረፍ በዚህች ሌሊት ካልሸሸህ፣ በነገው ቀን ትገደላለህ” ብላ አስጠነቀቀችው። ሜልኮልም ዳዊትን በመስኮት አሾልካ አወረደችው፣ እርሱም ሸሽቶ አመለጠ። ከዚያም ሜልኮል የጣዖት ምስል ወስዳ በዐልጋው ላይ አጋደመችው፤ በራስጌውም የፍየል ጠጕር አኖረች፤ በልብስም ሸፈነችው። ሳኦል ዳዊትን እንዲይዙት ሰዎች በላከ ጊዜ ሜልኮል፣ “እርሱ ታሟል” አለቻቸው። ሳኦልም ሰዎቹ ዳዊትን እንዲያዩት መልሶ ላካቸው፤ እርሱም፣ “እገድለው ዘንድ ከነዐልጋው አምጡልኝ” አላቸው። የተላኩትም ሰዎች በገቡ ጊዜ እነሆ፤ የጣዖት ምስሉ በዐልጋው ላይ ተጋድሞ በራስጌውም የፍየል ጠጕር ተደርጎለት ነበር። ሳኦልም ሜልኮልን፣ “እንዲህ አድርገሽ ያታለልሽኝ፣ ጠላቴ እንዲያመልጥ የሰደድሽው ለምንድን ነው?” ሲል ጠየቃት። ሜልኮልም፣ “ ‘እንዳመልጥ እርጂኝ፤ አለዚያ እገድልሻለሁ’ አለኝ” ብላ መለሰችለት።

1 ሳሙኤል 19:1-17 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)

ሳኦልም ለልጁ ለዮናታንና ለባሪያዎቹ ሁሉ ዳዊትን ይገድሉ ዘንድ ነገራቸው። የሳኦል ልጅ ዮናታን ግን ዳዊትን እጅግ ይወድድ ነበር። ዮናታንም፦ አባቴ ሳኦል ሊገድልህ ፈልጎአል፥ አሁን እንግዲህ ለነገው ተጠንቅቀህ ተሸሸግ፥ በስውርም ተቀመጥ፥ እኔም እወጣለሁ አንተም ባለህበት እርሻ በአባቴ አጠገብ እቆማለሁ፥ ስለ አንተም ከአባቴ ጋር እነጋገራለሁ፥ የሆነውንም አይቼ እነግርሃለሁ ብሎ ለዳዊት ነገረው። ዮናታንም ለአባቱ ለሳኦል፦ እርሱ አልበደለህምና፥ ሥራውም ለአንተ እጅግ መልካም ሆኖአልና ንጉሡ ባሪያውን ዳዊትን አይበድለው፥ ነፍሱንም በእጁ ጥሎ ፍልስጥኤማዊውን ገደለ፥ እግዚአብሔርም ለእስራኤል ሁሉ ታላቅ መድኃኒት አደረገ፥ አንተም አይተህ ደስ አለህ፥ በከንቱ ዳዊትን በመግደልህ ስለ ምን በንጹሕ ደም ላይ ትበድላለህ? ብሎ ስለ ዳዊት መልካም ተናገረ። ሳኦልም የዮናታንን ቃል ሰማ፥ ሳኦልም፦ ሕያው እግዚአብሔርን! ዳዊት አይገደልም ብሎ ማለ። ዮናታንም ዳዊትን ጠርቶ ይህን ነገር ሁሉ ነገረው፥ ዮናታንም ዳዊትን ወደ ሳኦል አመጣው፥ እንደ ቀድሞውም በፊቱ ነበረ። ዳግሞም ጦርነት ሆነ፥ ዳዊትም ወጥቶ ከፍልስጥኤማውያን ጋር ተዋጋ፥ ታላቅ ግዳይም ገደላቸው፥ ከፊቱም ሸሹ። ሳኦልም ጦሩን ይዞ በቤቱ ተቀምጦ ሳለ ክፉ መንፈስ ከእግዚአብሔር ዘንድ ያዘው። ዳዊትም በእጁ በገና ይመታ ነበር። ሳኦልም ዳዊትን ከግንብ ጋር ያጣብቀው ዘንድ ጦሩን ወረወረ፥ ዳዊትም ከሳኦል ፊት ዘወር አለ፥ ጦሩም በግንቡ ውስጥ ተተከለ፥ በዚያም ሌሊት ዳዊት ሸሽቶ አመለጠ። ሳኦልም ዳዊትን ጠብቀው በነጋው እንዲገድሉት መልእክተኞቹን ወደ ዳዊት ቤት ላከ፥ ሚስቱም ሜልኮል፦ በዚህች ሌሊት ነፍስህን ካላዳንህ ነገ ትገደላለህ ብላ ነገረችው። ሜልኮልም ዳዊትን በመስኮት አወረደችው፥ ሄደም፥ ሸሽቶም አመለጠ። ሜልኮልም ተራፊምን ወስዳ በአልጋ ላይ አኖረችው፥ በራስጌውም ጉንጉን የፍየል ጠጉር አደረገች፥ በልብስም ከደነችው። ሳኦልም ዳዊትን እንዲያመጡት መልእክተኞችን ላከ፥ እርስዋም፦ ታምሞአል አለቻቸው። ሳኦልም፦ እገድለው ዘንድ ዳዊትን ከነ አልጋው አምጡልኝ ብሎ መልእክተኞቹን ወደ ዳዊት ሰደደ። መልእክተኞቹም በገቡ ጊዜ እነሆ፥ ተራፊሙን በአልጋው ላይ አገኙ፥ በራስጌው ጕንጕን የፍየል ጠጉር ነበረ። ሳኦልም ሜልኮልን፦ ስለ ምን እንዲህ አድርገሽ አታለልሽኝ? ጠላቴን አስኮበለልሽው አላት። ሜልኮልም ለሳኦል፦ እርሱ፦ አውጥተሽ ስደጂኝ፥ አለዚያም እገድልሻለሁ አለኝ ብላ መለሰችለት።

1 ሳሙኤል 19:1-17 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)

ሳኦል ዳዊትን ሊገድለው ማቀዱን ለልጁ ለዮናታንና ባለሟሎቹ ለሆኑት ባለሥልጣኖች ሁሉ ነገረ፤ ነገር ግን ዮናታን ዳዊትን እጅግ ይወደው ነበር። በእርሱ ላይ የታቀደውን ነገር ሁሉ እንዲህ ሲል ነገረው፥ “አባቴ ሊገድልህ ዐቅዶአል፤ ስለዚህ እባክህ በነገው ማለዳ ይህ እንዳይደርስብህ ተጠንቀቅ፤ ስውር በሆነ ቦታ ተሸሽገህ ቈይ፤ አንተም ተደብቀህ ባለህበት እርሻ ወደ አባቴ ቀርቤ ስለ አንተ አነጋግረዋለሁ፤ የማገኘውንም መልስ እንድታውቀው አደርጋለሁ።” ዮናታንም ዳዊትን በማመስገን ለሳኦል እንዲህ ሲል ነገረው፤ “በአገልጋይህ በዳዊት ላይ ክፉ ነገር አታድርግ፤ እርሱ ምንም ነገር አልበደለህም፤ ይልቅስ እርሱ የሚያደርገው ነገር ሁሉ ታላቅ ጥቅም በማስገኘት ረድቶሃል፤ እርሱ ለሕይወቱ ሳይሳሳ በመጋፈጥ ጎልያድን ገደለ፤ እግዚአብሔርም ለእስራኤል ታላቅ ድልን አቀዳጀ፤ አንተም ይህን ባየህ ጊዜ ደስ ብሎህ ነበር፤ ታዲያ አሁን አንተ በንጹሕ ሰው ላይ በደል ለመሥራት ስለምን ታስባለህ? ምክንያት በሌለውስ ነገር ዳዊትን ለመግደል ስለምን ፈለግኽ?” ሳኦልም ዮናታን የተናገረውን ቃል በመስማት ዳዊትን እንደማይገድለው የእግዚአብሔርን ስም ጠርቶ በመማል አረጋገጠ፤ ስለዚህ ዮናታን ዳዊትን ጠርቶ ይህን ሁሉ ከነገረው በኋላ ወደ ሳኦል አቀረበው፤ ዳዊትም ከዚያ በፊት ያደርገው እንደ ነበር በንጉሡ ፊት እንደ ቀድሞው ማገልገሉን ቀጠለ። ከፍልስጥኤማውያን ጋር ይደረግ የነበረውም ጦርነት እንደገና አገረሸ፤ ሆኖም ዳዊት በእነርሱ ላይ ብርቱ አደጋ በመጣል ድል ስለ መታቸው ሸሽተው ሄዱ፤ አንድ ቀን ከእግዚአብሔር የተላከ ክፉ መንፈስ ሳኦልን ተቈራኘው፤ እርሱም ጦሩን በእጁ እንደ ያዘ በቤቱ ውስጥ ተቀምጦ ነበር፤ ዳዊትም በዚያው በገናውን ይደረድር ነበር፤ ሳኦል ዳዊትን ወግቶ ከግድግዳው ጋር ሊያጣብቀው በማሰብ ጦሩን ወረወረበት፤ ዳዊት ግን ዞር በማለቱ ጦሩ በግድግዳ ላይ ተተከለ፤ ዳዊትም ከዚያ ሸሽቶ አመለጠ። በዚያኑ ምሽት ሳኦል የዳዊትን ቤት ከበው ማለዳ እንዲገድሉት ሰዎችን ላከ፤ የዳዊት ሚስት ሜልኮል “ዛሬ ማታ ነፍስህን ካላዳንህ በቀር ነገ ጧት ትገደላለህ” ስትል አስጠነቀቀችው፤ እርስዋም በመስኮት አወረደችው፤ ሸሽቶም አመለጠ፤ ከዚህ በኋላ የቤተሰቡን ጣዖት ወስዳ በአልጋ ላይ አጋደመችው፤ ከፍየል ጠጒር የተሠራ ትራስም በራስጌው አኑራ በልብስ ሸፈነችው። የሳኦል ወታደሮች ዳዊትን ለመያዝ በመጡ ጊዜ ሜልኮል እርሱ ታሞ ተኝቶአል አለቻቸው። ሳኦል ግን “እኔው ራሴ እገድለው ዘንድ ከነአልጋው ተሸክማችሁ ወደዚህ አምጡት” ብሎ መልሶ ላካቸው። ወደ ቤትም ውስጥ ዘልቀው በገቡ ጊዜ ጣዖቱንና በራስጌው ያለውን ከፍየል ጠጒር የተሠራውን ትራስ ብቻ አገኙ። ሳኦልም ሜልኮልን “ጠላቴ የሚያመልጥበትን ተንኰል በመሥራት ስለምን እንዲህ አታለልሽኝ?” ሲል ጠየቃት። እርስዋም “እኔ ምን ላድርግ፥ ‘ማምለጥ እንድችል ካልረዳሽኝ እገድልሻለሁ’ አለኝ” ስትል መለሰችለት።

1 ሳሙኤል 19:1-17 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)

ሳኦል ዳዊትን እንዲገድሉት ለልጁ ለዮናታንና ለባለሟሎቹ ነገራቸው፤ ዮናታን ግን ዳዊትን እጅግ ይወደው ነበር። እንዲህ ሲልም አስጠነቀቀው፤ “አባቴ ሳኦል ሊገድልህ አጋጣሚ እየፈልገ ነው፤ ነገ ጠዋት ተጠንቀቅ፤ ወደ አንድ መደበቂያ ቦታም ሂድ፤ በዚያም ቆይ። እኔም እወጣና አንተ ባለህበት ከአባቴ እርሻ አጠገብ እቆማለሁ፤ ስለ አንተም አነጋግረዋለሁ፤ የተረዳሁትንም እነግርሃለሁ።” ዮናታን ለአባቱ ለሳኦል፥ ስለ ዳዊት እንዲህ ሲል መልካም ነገር ተናገረ፥ “ንጉሥ በአገልጋዩ በዳዊት ላይ ክፉ ነገር አያድርግ፤ እርሱ አልበደለህም፤ ያደረገውም ነገር በእጅጉ ጠቅሞሃል። ዳዊት ፍልስጥኤማዊውን የገደለው በገዛ ሕይወቱ ቆርጦ ነው። ጌታ ለመላው እስራኤል ታላቅ ድልን አቀዳጀ፤ አንተም አይተህ ደስ አለህ። ታዲያ እርሱን በከንቱ በመግደል ዳዊትን በመሰለ ንጹሕ ሰው ላይ ለምን በደል ትፈጽማለህ?” ሳኦልም ዮናታንን ካዳመጠው በኋላ፥ “በሕያው ጌታ እምላለሁ! ዳዊት አይገደልም” አለ። ስለዚህም ዮናታን ዳዊትን ጠርቶ የተባባሉትን ሁሉ ነገረው፤ ወደ ሳኦልም አመጣው፤ ዳዊትም እንደ ቀድሞው በፊቱ ቆመ። እንደገና ሌላ ጦርነት ተነሣ፤ ዳዊትም ወጥቶ ፍልስጥኤማውያንን ወጋቸው፤ ከፊቱም እስኪሸሹ ድረስ እጅግ መታቸው። ነገር ግን ሳኦል ጦሩን ይዞ በቤቱ ተቀምጦ ሳለ፥ ከጌታ ዘንድ ክፉ መንፈስ መጣበት፤ ያንጊዜ ዳዊት በገናውን ይደረድር ነበር። ሳኦልም ከግድግዳው ጋር ሊያጣብቀው ጦሩን ወረወረበት፤ ነገር ግን ዳዊት ዘወር በማለቱ ሳኦል የወረወረው ጦር እግድግዳው ላይ ተሰካ። በዚያች ሌሊት ዳዊት ሸሽቶ አመለጠ። ሳኦልም የዳዊትን ቤት ከበው በማለዳ እንዲገድሉት ሰዎችን ላከ። የዳዊት ሚስት ሜልኮል ግን፥ “ሕይወትህን ለማትረፍ በዚህች ሌሊት ካልሸሸህ፥ በነገው ቀን ትገደላለህ” ብላ አስጠነቀቀችው። ሜልኮልም ዳዊትን በመስኮት አሾልካ አወረደችው፥ እርሱም ሸሽቶ አመለጠ። ከዚያም ሜልኮል የጣዖት ምስል ወስዳ በአልጋው ላይ አጋደመችው፤ በራስጌውም የፍየል ጠጉር አኖረች፤ በልብስም ሸፈነችው። ሳኦል ዳዊትን እንዲይዙት ሰዎች በላከ ጊዜ ሜልኮል፥ “እርሱ ታሟል” አለቻቸው። ሳኦልም ሰዎቹ ዳዊትን እንዲያዩት መልሶ ላካቸው፤ እርሱም፥ “እገድለው ዘንድ ከነአልጋው አምጡልኝ” አላቸው። የተላኩትም ሰዎች በገቡ ጊዜ፥ እነሆ፥ የጣዖት ምስሉ በአልጋው ላይ ተጋድሞ በራስጌውም የፍየል ጠጉር ተደርጎለት ነበር። ሳኦልም ሜልኮልን፥ “እንዲህ አድርገሽ ለምን አታለልሽኝ? ጠላቴ እንዲያመልጥ የሰደድሽው ለምንድን ነው?” ሲል ጠየቃት። ሜልኮልም፥ “ ‘እንዳመልጥ እርጂኝ፤ ያለዚያ እገድልሻለሁ’ አለኝ” ብላ መለሰችለት።