1ኛ መጽሐፈ ሳሙኤል 19:1-17

1ኛ መጽሐፈ ሳሙኤል 19:1-17 መቅካእኤ

ሳኦል ዳዊትን እንዲገድሉት ለልጁ ለዮናታንና ለባለሟሎቹ ነገራቸው፤ ዮናታን ግን ዳዊትን እጅግ ይወደው ነበር። እንዲህ ሲልም አስጠነቀቀው፤ “አባቴ ሳኦል ሊገድልህ አጋጣሚ እየፈልገ ነው፤ ነገ ጠዋት ተጠንቀቅ፤ ወደ አንድ መደበቂያ ቦታም ሂድ፤ በዚያም ቆይ። እኔም እወጣና አንተ ባለህበት ከአባቴ እርሻ አጠገብ እቆማለሁ፤ ስለ አንተም አነጋግረዋለሁ፤ የተረዳሁትንም እነግርሃለሁ።” ዮናታን ለአባቱ ለሳኦል፥ ስለ ዳዊት እንዲህ ሲል መልካም ነገር ተናገረ፥ “ንጉሥ በአገልጋዩ በዳዊት ላይ ክፉ ነገር አያድርግ፤ እርሱ አልበደለህም፤ ያደረገውም ነገር በእጅጉ ጠቅሞሃል። ዳዊት ፍልስጥኤማዊውን የገደለው በገዛ ሕይወቱ ቆርጦ ነው። ጌታ ለመላው እስራኤል ታላቅ ድልን አቀዳጀ፤ አንተም አይተህ ደስ አለህ። ታዲያ እርሱን በከንቱ በመግደል ዳዊትን በመሰለ ንጹሕ ሰው ላይ ለምን በደል ትፈጽማለህ?” ሳኦልም ዮናታንን ካዳመጠው በኋላ፥ “በሕያው ጌታ እምላለሁ! ዳዊት አይገደልም” አለ። ስለዚህም ዮናታን ዳዊትን ጠርቶ የተባባሉትን ሁሉ ነገረው፤ ወደ ሳኦልም አመጣው፤ ዳዊትም እንደ ቀድሞው በፊቱ ቆመ። እንደገና ሌላ ጦርነት ተነሣ፤ ዳዊትም ወጥቶ ፍልስጥኤማውያንን ወጋቸው፤ ከፊቱም እስኪሸሹ ድረስ እጅግ መታቸው። ነገር ግን ሳኦል ጦሩን ይዞ በቤቱ ተቀምጦ ሳለ፥ ከጌታ ዘንድ ክፉ መንፈስ መጣበት፤ ያንጊዜ ዳዊት በገናውን ይደረድር ነበር። ሳኦልም ከግድግዳው ጋር ሊያጣብቀው ጦሩን ወረወረበት፤ ነገር ግን ዳዊት ዘወር በማለቱ ሳኦል የወረወረው ጦር እግድግዳው ላይ ተሰካ። በዚያች ሌሊት ዳዊት ሸሽቶ አመለጠ። ሳኦልም የዳዊትን ቤት ከበው በማለዳ እንዲገድሉት ሰዎችን ላከ። የዳዊት ሚስት ሜልኮል ግን፥ “ሕይወትህን ለማትረፍ በዚህች ሌሊት ካልሸሸህ፥ በነገው ቀን ትገደላለህ” ብላ አስጠነቀቀችው። ሜልኮልም ዳዊትን በመስኮት አሾልካ አወረደችው፥ እርሱም ሸሽቶ አመለጠ። ከዚያም ሜልኮል የጣዖት ምስል ወስዳ በአልጋው ላይ አጋደመችው፤ በራስጌውም የፍየል ጠጉር አኖረች፤ በልብስም ሸፈነችው። ሳኦል ዳዊትን እንዲይዙት ሰዎች በላከ ጊዜ ሜልኮል፥ “እርሱ ታሟል” አለቻቸው። ሳኦልም ሰዎቹ ዳዊትን እንዲያዩት መልሶ ላካቸው፤ እርሱም፥ “እገድለው ዘንድ ከነአልጋው አምጡልኝ” አላቸው። የተላኩትም ሰዎች በገቡ ጊዜ፥ እነሆ፥ የጣዖት ምስሉ በአልጋው ላይ ተጋድሞ በራስጌውም የፍየል ጠጉር ተደርጎለት ነበር። ሳኦልም ሜልኮልን፥ “እንዲህ አድርገሽ ለምን አታለልሽኝ? ጠላቴ እንዲያመልጥ የሰደድሽው ለምንድን ነው?” ሲል ጠየቃት። ሜልኮልም፥ “ ‘እንዳመልጥ እርጂኝ፤ ያለዚያ እገድልሻለሁ’ አለኝ” ብላ መለሰችለት።