ሳኦል ዳዊትን ሊገድለው ማቀዱን ለልጁ ለዮናታንና ባለሟሎቹ ለሆኑት ባለሥልጣኖች ሁሉ ነገረ፤ ነገር ግን ዮናታን ዳዊትን እጅግ ይወደው ነበር። በእርሱ ላይ የታቀደውን ነገር ሁሉ እንዲህ ሲል ነገረው፥ “አባቴ ሊገድልህ ዐቅዶአል፤ ስለዚህ እባክህ በነገው ማለዳ ይህ እንዳይደርስብህ ተጠንቀቅ፤ ስውር በሆነ ቦታ ተሸሽገህ ቈይ፤ አንተም ተደብቀህ ባለህበት እርሻ ወደ አባቴ ቀርቤ ስለ አንተ አነጋግረዋለሁ፤ የማገኘውንም መልስ እንድታውቀው አደርጋለሁ።” ዮናታንም ዳዊትን በማመስገን ለሳኦል እንዲህ ሲል ነገረው፤ “በአገልጋይህ በዳዊት ላይ ክፉ ነገር አታድርግ፤ እርሱ ምንም ነገር አልበደለህም፤ ይልቅስ እርሱ የሚያደርገው ነገር ሁሉ ታላቅ ጥቅም በማስገኘት ረድቶሃል፤ እርሱ ለሕይወቱ ሳይሳሳ በመጋፈጥ ጎልያድን ገደለ፤ እግዚአብሔርም ለእስራኤል ታላቅ ድልን አቀዳጀ፤ አንተም ይህን ባየህ ጊዜ ደስ ብሎህ ነበር፤ ታዲያ አሁን አንተ በንጹሕ ሰው ላይ በደል ለመሥራት ስለምን ታስባለህ? ምክንያት በሌለውስ ነገር ዳዊትን ለመግደል ስለምን ፈለግኽ?” ሳኦልም ዮናታን የተናገረውን ቃል በመስማት ዳዊትን እንደማይገድለው የእግዚአብሔርን ስም ጠርቶ በመማል አረጋገጠ፤ ስለዚህ ዮናታን ዳዊትን ጠርቶ ይህን ሁሉ ከነገረው በኋላ ወደ ሳኦል አቀረበው፤ ዳዊትም ከዚያ በፊት ያደርገው እንደ ነበር በንጉሡ ፊት እንደ ቀድሞው ማገልገሉን ቀጠለ። ከፍልስጥኤማውያን ጋር ይደረግ የነበረውም ጦርነት እንደገና አገረሸ፤ ሆኖም ዳዊት በእነርሱ ላይ ብርቱ አደጋ በመጣል ድል ስለ መታቸው ሸሽተው ሄዱ፤ አንድ ቀን ከእግዚአብሔር የተላከ ክፉ መንፈስ ሳኦልን ተቈራኘው፤ እርሱም ጦሩን በእጁ እንደ ያዘ በቤቱ ውስጥ ተቀምጦ ነበር፤ ዳዊትም በዚያው በገናውን ይደረድር ነበር፤ ሳኦል ዳዊትን ወግቶ ከግድግዳው ጋር ሊያጣብቀው በማሰብ ጦሩን ወረወረበት፤ ዳዊት ግን ዞር በማለቱ ጦሩ በግድግዳ ላይ ተተከለ፤ ዳዊትም ከዚያ ሸሽቶ አመለጠ። በዚያኑ ምሽት ሳኦል የዳዊትን ቤት ከበው ማለዳ እንዲገድሉት ሰዎችን ላከ፤ የዳዊት ሚስት ሜልኮል “ዛሬ ማታ ነፍስህን ካላዳንህ በቀር ነገ ጧት ትገደላለህ” ስትል አስጠነቀቀችው፤ እርስዋም በመስኮት አወረደችው፤ ሸሽቶም አመለጠ፤ ከዚህ በኋላ የቤተሰቡን ጣዖት ወስዳ በአልጋ ላይ አጋደመችው፤ ከፍየል ጠጒር የተሠራ ትራስም በራስጌው አኑራ በልብስ ሸፈነችው። የሳኦል ወታደሮች ዳዊትን ለመያዝ በመጡ ጊዜ ሜልኮል እርሱ ታሞ ተኝቶአል አለቻቸው። ሳኦል ግን “እኔው ራሴ እገድለው ዘንድ ከነአልጋው ተሸክማችሁ ወደዚህ አምጡት” ብሎ መልሶ ላካቸው። ወደ ቤትም ውስጥ ዘልቀው በገቡ ጊዜ ጣዖቱንና በራስጌው ያለውን ከፍየል ጠጒር የተሠራውን ትራስ ብቻ አገኙ። ሳኦልም ሜልኮልን “ጠላቴ የሚያመልጥበትን ተንኰል በመሥራት ስለምን እንዲህ አታለልሽኝ?” ሲል ጠየቃት። እርስዋም “እኔ ምን ላድርግ፥ ‘ማምለጥ እንድችል ካልረዳሽኝ እገድልሻለሁ’ አለኝ” ስትል መለሰችለት።
አንደኛ መጽሐፈ ሳሙኤል 19 ያንብቡ
ያጋሩ
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: አንደኛ መጽሐፈ ሳሙኤል 19:1-17
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
ቤት
መጽሐፍ ቅዱስ
እቅዶች
ቪዲዮዎች