ሳኦልም ለልጁ ለዮናታንና ለብላቴኖቹ ሁሉ ዳዊትን ይገድሉ ዘንድ ነገራቸው። የሳኦል ልጅ ዮናታን ግን ዳዊትን እጅግ ይወድደው ነበር። ዮናታንም፥ “አባቴ ሳኦል ሊገድልህ ፈልጎአል፤ አሁን እንግዲህ ለነገው ተጠንቅቀህ ተሸሸግ፤ በስውርም ተቀመጥ። እኔም እወጣለሁ፤ አንተም ባለህበት እርሻ በአባቴ አጠገብ እቆማለሁ፤ ስለ አንተም ለአባቴ እነግረዋለሁ፤ የሆነውንም አይቼ እነግርሃለሁ” ብሎ ለዳዊት ነገረው። ዮናታንም ለአባቱ ለሳኦል ስለ ዳዊት መልካም ተናገረ እንዲህም አለው፥ “እርሱ አልበደለህምና፥ ሥራውም ለአንተ እጅግ መልካም ሆኖአልና ንጉሡ ባሪያውን ዳዊትን አይበድለው፤ ነፍሱንም በእጁ ጥሎ ፍልስጥኤማዊዉን ገደለ፤ እግዚአብሔርም በእርሱ ታላቅ መድኀኒት አደረገ፤ እስራኤልም ሁሉ አይተው ደስ አላቸው፤ በከንቱ ዳዊትን ትገድለው ዘንድ ስለምን በንጹሕ ደም ላይ ትበድላለህ?” ሳኦልም የዮናታንን ቃል ሰማ፤ ሳኦልም፥ “ሕያው እግዚአብሔርን! ዳዊት አይገደልም” ብሎ ማለ። ዮናታንም ዳዊትን ጠርቶ ይህን ነገር ሁሉ ነገረው፤ ዮናታንም ዳዊትን ወደ ሳኦል አመጣው፤ እንደ ቀድሞውም በፊቱ ነበረ። ደግሞም ጦርነት ሆነ፤ ዳዊትም ወጥቶ ከፍልስጥኤማውያን ጋር ተዋጋ፤ ታላቅ ግዳይም ገደላቸው፤ ከፊቱም ሸሹ። ሳኦልም ጦሩን ይዞ በቤቱ ተቀምጦ ሳለ ክፉ መንፈስ ከእግዚአብሔር ዘንድ ያዘው። ዳዊትም በእጁ በገና ይመታ ነበር። ሳኦልም ዳዊትን ከግንብ ጋር ያጣብቀው ዘንድ ጦሩን ወረወረ፤ ዳዊትም ከሳኦል ፊት ዘወር አለ፤ ጦሩም በግንቡ ውስጥ ተተከለ፤ በዚያም ሌሊት ዳዊት ሸሸቶ አመለጠ። ሳኦልም ዳዊትን ጠበቀው፤ በነጋው እንዲገድሉት መልእክተኞቹን ወደ ዳዊት ቤት ላከ፤ ሚስቱም ሜልኮል፥ “በዚህች ሌሊት ነፍስህን ካላዳንህ ነገ ትገደላለህ” ብላ ነገረችው። ሜልኮልም ዳዊትን በመስኮት አወረደችው፤ ሄደም፤ ሸሽቶም አመለጠ። ሜልኮልም ተራፊምን ወስዳ በአልጋ ላይ አኖረችው፤ በራስጌውም ጕንጕን የፍየል ጠጕር አደረገች፤ በልብስም ከደነችው። ሳኦልም ዳዊትን ይዘው እንዲያመጡት መልእክተኞችን ላከ፤ እርስዋም ታሞአል አለቻቸው። ሳኦልም፥ “እገድለው ዘንድ ዳዊትን ከነአልጋው” አምጡልኝ ብሎ መልእክተኞቹን ወደ ዳዊት ላከ። መልእክተኞቹም በገቡ ጊዜ እነሆ፥ ተራፊሙን በአልጋው ላይ አገኙ፤ በራስጌውም ጕንጕን የፍየል ጠጕር ነበረ። ሳኦልም ሜልኮልን አላት፥ “ስለምን እንዲህ አታለልሽኝ? ጠላቴን አስኰበለልሽ፤ እንዲያመልጥም አደረግሽው?” ሜልኮልም ለሳኦል፥ “እርሱ፦ አውጥተሽ ስደጂኝ፤ አለዚያ እገድልሻለሁ አለኝ” አለችው።
መጽሐፈ ሳሙኤል ቀዳማዊ 19 ያንብቡ
ያጋሩ
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: መጽሐፈ ሳሙኤል ቀዳማዊ 19:1-17
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
ቤት
መጽሐፍ ቅዱስ
እቅዶች
ቪዲዮዎች