ሳኦልም ለልጁ ለዮናታንና ለባሪያዎቹ ሁሉ ዳዊትን ይገድሉ ዘንድ ነገራቸው። የሳኦል ልጅ ዮናታን ግን ዳዊትን እጅግ ይወድድ ነበር። ዮናታንም፦ አባቴ ሳኦል ሊገድልህ ፈልጎአል፥ አሁን እንግዲህ ለነገው ተጠንቅቀህ ተሸሸግ፥ በስውርም ተቀመጥ፥ እኔም እወጣለሁ አንተም ባለህበት እርሻ በአባቴ አጠገብ እቆማለሁ፥ ስለ አንተም ከአባቴ ጋር እነጋገራለሁ፥ የሆነውንም አይቼ እነግርሃለሁ ብሎ ለዳዊት ነገረው። ዮናታንም ለአባቱ ለሳኦል፦ እርሱ አልበደለህምና፥ ሥራውም ለአንተ እጅግ መልካም ሆኖአልና ንጉሡ ባሪያውን ዳዊትን አይበድለው፥ ነፍሱንም በእጁ ጥሎ ፍልስጥኤማዊውን ገደለ፥ እግዚአብሔርም ለእስራኤል ሁሉ ታላቅ መድኃኒት አደረገ፥ አንተም አይተህ ደስ አለህ፥ በከንቱ ዳዊትን በመግደልህ ስለ ምን በንጹሕ ደም ላይ ትበድላለህ? ብሎ ስለ ዳዊት መልካም ተናገረ። ሳኦልም የዮናታንን ቃል ሰማ፥ ሳኦልም፦ ሕያው እግዚአብሔርን! ዳዊት አይገደልም ብሎ ማለ። ዮናታንም ዳዊትን ጠርቶ ይህን ነገር ሁሉ ነገረው፥ ዮናታንም ዳዊትን ወደ ሳኦል አመጣው፥ እንደ ቀድሞውም በፊቱ ነበረ። ዳግሞም ጦርነት ሆነ፥ ዳዊትም ወጥቶ ከፍልስጥኤማውያን ጋር ተዋጋ፥ ታላቅ ግዳይም ገደላቸው፥ ከፊቱም ሸሹ። ሳኦልም ጦሩን ይዞ በቤቱ ተቀምጦ ሳለ ክፉ መንፈስ ከእግዚአብሔር ዘንድ ያዘው። ዳዊትም በእጁ በገና ይመታ ነበር። ሳኦልም ዳዊትን ከግንብ ጋር ያጣብቀው ዘንድ ጦሩን ወረወረ፥ ዳዊትም ከሳኦል ፊት ዘወር አለ፥ ጦሩም በግንቡ ውስጥ ተተከለ፥ በዚያም ሌሊት ዳዊት ሸሽቶ አመለጠ። ሳኦልም ዳዊትን ጠብቀው በነጋው እንዲገድሉት መልእክተኞቹን ወደ ዳዊት ቤት ላከ፥ ሚስቱም ሜልኮል፦ በዚህች ሌሊት ነፍስህን ካላዳንህ ነገ ትገደላለህ ብላ ነገረችው። ሜልኮልም ዳዊትን በመስኮት አወረደችው፥ ሄደም፥ ሸሽቶም አመለጠ። ሜልኮልም ተራፊምን ወስዳ በአልጋ ላይ አኖረችው፥ በራስጌውም ጉንጉን የፍየል ጠጉር አደረገች፥ በልብስም ከደነችው። ሳኦልም ዳዊትን እንዲያመጡት መልእክተኞችን ላከ፥ እርስዋም፦ ታምሞአል አለቻቸው። ሳኦልም፦ እገድለው ዘንድ ዳዊትን ከነ አልጋው አምጡልኝ ብሎ መልእክተኞቹን ወደ ዳዊት ሰደደ። መልእክተኞቹም በገቡ ጊዜ እነሆ፥ ተራፊሙን በአልጋው ላይ አገኙ፥ በራስጌው ጕንጕን የፍየል ጠጉር ነበረ። ሳኦልም ሜልኮልን፦ ስለ ምን እንዲህ አድርገሽ አታለልሽኝ? ጠላቴን አስኮበለልሽው አላት። ሜልኮልም ለሳኦል፦ እርሱ፦ አውጥተሽ ስደጂኝ፥ አለዚያም እገድልሻለሁ አለኝ ብላ መለሰችለት።
አንደኛ መጽሐፈ ሳሙኤል 19 ያንብቡ
ያጋሩ
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: አንደኛ መጽሐፈ ሳሙኤል 19:1-17
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
ቤት
መጽሐፍ ቅዱስ
እቅዶች
ቪዲዮዎች