የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

1 ነገሥት 13:1-10

1 ነገሥት 13:1-10 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)

እነ​ሆም፥ አንድ የእ​ግ​ዚ​አ​ብ​ሔር ሰው በእ​ግ​ዚ​አ​ብ​ሔር ቃል ከይ​ሁዳ ወደ ቤቴል መጣ፤ ኢዮ​ር​ብ​ዓ​ምም መሥ​ዋ​ዕት ይሠዋ ዘንድ በመ​ሠ​ዊ​ያው አጠ​ገብ ቆሞ ነበር። የእ​ግ​ዚ​አ​ብ​ሔ​ርም ሰው በመ​ሠ​ዊ​ያው ላይ፥ “መሠ​ዊያ ሆይ፥ መሠ​ዊያ ሆይ፥ እግ​ዚ​አ​ብ​ሔር እን​ዲህ ይላል፦ እነሆ፥ ስሙ ኢዮ​ስ​ያስ የሚ​ባል ልጅ ለዳ​ዊት ቤት ይወ​ለ​ዳል፤ ዕጣ​ንም የሚ​ያ​ጥ​ኑ​ብ​ህን የኮ​ረ​ብታ መስ​ገ​ጃ​ዎ​ቹን ካህ​ናት ይሠ​ዋ​ብ​ሃል፤ የሰ​ዎ​ቹ​ንም አጥ​ንት ያቃ​ጥ​ል​ብ​ሃል” ብሎ በእ​ግ​ዚ​አ​ብ​ሔር ቃል ጠራ። በዚ​ያም ቀን፦ እግ​ዚ​አ​ብ​ሔር የተ​ና​ገ​ረው ቃል ይህ ነው፤ “እነሆ፥ መሠ​ዊ​ያው ይሰ​ነ​ጠ​ቃል፤ በው​ስ​ጡም ያለው ስብ ይፈ​ስ​ሳል” ብሎ ምል​ክት ሰጠ። ከዚ​ህም በኋላ ንጉሡ ኢዮ​ር​ብ​ዓም የእ​ግ​ዚ​አ​ብ​ሔር ሰው በቤ​ቴል ባለው መሠ​ዊያ ላይ የተ​ና​ገ​ረ​ውን ነገር በሰማ ጊዜ፥ ንጉሡ፥ “ያዙት” ብሎ እጁን ከመ​ሠ​ዊ​ያው ላይ አነሣ። ከዚ​ህም በኋላ በእ​ርሱ ላይ የዘ​ረ​ጋት እጁ ደረ​ቀች፤ ወደ እር​ሱም ይመ​ል​ሳት ዘንድ አል​ተ​ቻ​ለ​ውም። የእ​ግ​ዚ​አ​ብ​ሔ​ርም ሰው በእ​ግ​ዚ​አ​ብ​ሔር ቃል እንደ ሰጠው ምል​ክት መሠ​ዊ​ያው ተሰ​ነ​ጠቀ፤ በው​ስ​ጡም ያለው ስብ ፈሰሰ። ንጉ​ሡም ኢዮ​ር​ብ​ዓም የእ​ግ​ዚ​አ​ብ​ሔ​ርን ሰው፥ “አሁን የአ​ም​ላ​ክ​ህን የእ​ግ​ዚ​አ​ብ​ሔ​ርን ፊት ለምን፤ እጄም ወደ እኔ ትመ​ለስ ዘንድ ስለ እኔ ጸልይ” አለው፥ የእ​ግ​ዚ​አ​ብ​ሔ​ርም ሰው እግ​ዚ​አ​ብ​ሔ​ርን ለመነ፤ የን​ጉ​ሡም እጅ ወደ እርሱ ተመ​ለ​ሰች። እንደ ቀድ​ሞም ሆነች። ንጉ​ሡም የእ​ግ​ዚ​አ​ብ​ሔ​ርን ሰው፥ “ከእኔ ጋር ወደ ቤቴ ና፥ ምሳም ብላ፥ ስጦ​ታም እሰ​ጥ​ሃ​ለሁ” አለው። የእ​ግ​ዚ​አ​ብ​ሔ​ርም ሰው ንጉ​ሡን፥ “የቤ​ት​ህን እኩ​ሌታ እን​ኳን ብት​ሰ​ጠኝ ከአ​ንተ ጋር አል​ገ​ባም፤ በዚ​ህም ስፍራ እን​ጀ​ራን አል​በ​ላም፤ ውኃም አል​ጠ​ጣም፤ እን​ጀ​ራም አት​ብላ፤ ውኃም አት​ጠጣ፤ በመ​ጣ​ህ​በት መን​ገ​ድም አት​መ​ለስ ሲል እግ​ዚ​አ​ብ​ሔር በቃሉ አዝ​ዞ​ኛ​ልና” አለው። በሌ​ላም መን​ገድ ሄደ፤ ወደ ቤቴ​ልም በመ​ጣ​በት መን​ገድ አል​ተ​መ​ለ​ሰም።

1 ነገሥት 13:1-10 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

ኢዮርብዓም መሥዋዕት ለማቅረብ በመሠዊያው አጠገብ ቆሞ ሳለ፣ በእግዚአብሔር ቃል ታዝዞ አንድ የእግዚአብሔር ሰው ከይሁዳ ወደ ቤቴል መጣ። መሠዊያውንም በእግዚአብሔር ቃል በመቃወም እንዲህ አለ፤ “አንተ መሠዊያ ሆይ! እንግዲህ እግዚአብሔር የሚለው ይህ ነው፤ ‘እነሆ፤ ኢዮስያስ የተባለ ለዳዊት ቤት ይወለዳል፤ እርሱም አሁን እዚህ መሥዋዕት የሚያቀርቡትን የኰረብታ ማምለኪያ ካህናት በላይህ ይሠዋቸዋል፤ የሰዎችም ዐጥንት በአንተ ላይ ይነድዳል።’ ” በዚያች ዕለት ያ የእግዚአብሔር ሰው፣ እንዲህ ሲል ምልክት ሰጠ፤ “እግዚአብሔር የሰጠውም ምልክት፣ ‘እነሆ፣ መሠዊያው ይሰነጠቃል፤ በላዩም ላይ ያለው ዐመድ ይፈስሳል’ ” የሚል ነው። ንጉሥ ኢዮርብዓምም ያ የእግዚአብሔር ሰው በቤቴል መሠዊያ ላይ ጮኾ የተናገረውን ሲሰማ፣ እጁን መሠዊያው ካለበት በመዘርጋት፣ “ያዙት!” አለ፤ ነገር ግን ያች የዘረጋት እጁ ደርቃ ቀረች፤ ሊመልሳትም አልቻለም እንዲሁም ያ የእግዚአብሔር ሰው በእግዚአብሔር ቃል ተመርቶ በሰጠው ምልክት መሠረት መሠዊያው ተሰነጠቀ፤ ዐመዱም ፈሰሰ። ከዚያም ንጉሡ የእግዚአብሔርን ሰው፣ “እጄ ወደ ቦታዋ እንድትመለስ ወደ አምላክህ ወደ እግዚአብሔር ለምንልኝ፤ ጸልይልኝም” አለው፤ ስለዚህም የእግዚአብሔር ሰው እግዚአብሔርን ለመነ፤ የንጉሡ እጅ ወደ ቦታዋ ተመለሰች፤ እንደ ቀድሞዋም ሆነች። ንጉሡም የእግዚአብሔርን ሰው፣ “አብረኸኝ ወደ ቤት እንሂድ፤ አንድ ነገር ቅመስ፤ ስጦታም አደርግልሃለሁ” አለው። የእግዚአብሔር ሰው ግን ለንጉሡ እንዲህ ሲል መለሰለት፤ “ግማሽ ሀብትህን ብትሰጠኝ እንኳ፣ አብሬህ አልሄድም፤ እዚህ፣ እንጀራ አልበላም፤ ውሃም አልጠጣም። በእግዚአብሔር ቃል፤ ‘እንጀራ እንዳትበላ፣ ውሃም እንዳትጠጣ፣ በሄድህበትም መንገድ እንዳትመለስ’ ተብዬ ታዝዣለሁና።” ስለዚህም በመጣበት ሳይሆን በሌላ መንገድ ወደ ቤቴል ተመለሰ።

1 ነገሥት 13:1-10 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)

ኢዮርብዓምም ዕጣን እያጠነ በመሠዊያው አጠገብ ቆሞ ሳለ፥ እነሆም፥ አንድ የእግዚአብሔር ሰው በእግዚአብሔር ቃል ከይሁዳ ወደ ቤቴል መጣ፤ በመሠዊያውም ላይ “መሠዊያ ሆይ! መሠዊያ ሆይ! እግዚአብሔር እንዲህ ይላል ‘እነሆ፥ ስሙ ኢዮስያስ የሚባል ልጅ ለዳዊት ቤት ይወለዳል፤ ዕጣንም የሚያጥኑብህን የኮረብታ መስገጃዎቹን ካህናት ይሠዋብሃል፤ የሰዎቹንም አጥንት ያቃጥልብሃል፤” ብሎ በእግዚአብሔር ቃል ጮኸ። በዚያም ቀን “እግዚአብሔር የተናገረው ምልክት ይህ ነው፤ እነሆ፥ መሠዊያው ይሰነጠቃል፤ በላዩም ያለው አመድ ይፈስሳል፤” ብሎ ምልክት ሰጠ። ንጉሡም የእግዚአብሔር ሰው በቤቴል ባለው መሠዊያ ላይ የጮኸውን ነገር በሰማ ጊዜ፥ ኢዮርብዓም እጁን ከመሠዊያው አንሥቶ “ያዙት!” አለ። በእርሱም ላይ የዘረጋት እጅ ደረቀች፤ ወደ እርሱም ይመልሳት ዘንድ አልተቻለውም። የእግዚአብሔርም ሰው በእግዚአብሔር ቃል እንደ ሰጠው ምልክት መሠዊያው ተሰነጠቀ፤ አመዱም ከመሠዊያው ፈሰሰ። ንጉሡም የእግዚአብሔርን ሰው “አሁን የአምላክህን የእግዚአብሔርን ፊት ለምን፤ እጄም ወደ እኔ ትመለስ ዘንድ ስለ እኔ ጸልይ፤” አለው። የእግዚአብሔርም ሰው እግዚአብሔርን ለመነ፤ የንጉሡም እጅ ወደ እርሱ ተመለሰች፤ እንደ ቀድሞም ሆነች። ንጉሡም የእግዚአብሔርን ሰው “ከእኔ ጋር ወደ ቤቴ ና፤ እንጀራም ብላ፤ በረከትም እሰጥሃለሁ፤” አለው። የእግዚአብሔርም ሰው ንጉሡን “የቤትህን እኩሌታ እንኳ ብትሰጠኝ ከአንተ ጋር አልገባም፤ በዚህም ስፍራ እንጀራ አልበላም፤ ውሃም አልጠጣም፤ ‘እንጀራ አትብላ፤ ውሃም አትጠጣ፤ በመጣህበትም መንገድ አትመለስ፤’ በሚል በእግዚአብሔር ቃል ታዝዤአለሁና፤” አለው። በሌላም መንገድ ሄደ፤ ወደ ቤቴልም በመጣበት መንገድ አልተመለሰም።

1 ነገሥት 13:1-10 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)

ኢዮርብዓም መሥዋዕት ለማቅረብ በመሠዊያው አጠገብ ቆሞ ሳለ በእግዚአብሔር ትእዛዝ የተላከ አንድ ነቢይ እነሆ ከይሁዳ መጥቶ እዚያ ደረሰ፤ ነቢዩም እግዚአብሔር ባዘዘው መሠረት ያንን መሠዊያ በመቃወም እንዲህ ሲል የትንቢት ቃል ተናገረበት፦ “መሠዊያ! መሠዊያ ሆይ! እግዚአብሔር ስለ አንተ የሚለው ቃል ይህ ነው፦ ‘እነሆ ለዳዊት ቤተሰብ ኢዮስያስ ተብሎ የሚጠራ ልጅ ይወለዳል፤ እርሱም በኮረብታ ላይ ለተሠራው ለአሕዛብ መሠዊያ አገልጋዮች ሆነው መሥዋዕት የሚያቀርቡብህን ካህናት በአንተው ላይ ያርዳቸዋል፤ የሰዎችንም አጥንት በአንተ ላይ ያቃጥላል። እግዚአብሔር ይህን ምልክት ይሰጣል፤ ይህ መሠዊያ ተሰባብሮ ይወድቃል፤ በእርሱ ላይ ያለውም ዐመድ ይበተናል፤ ይህንንም የትንቢት ቃል በእኔ አማካይነት የተናገረው ራሱ እግዚአብሔር መሆኑን ይህ እንደ ተፈጸመ ወዲያውኑ ትገነዘባለህ’ ” አለ። ንጉሥ ኢዮርብዓምም ይህን በሰማ ጊዜ እጁን አንሥቶ ወደ ነቢዩ በማመልከት! “ያዙት!” የሚል ትእዛዝ ሰጠ፤ የንጉሡም ክንድ ወዲያውኑ ድርቅ ብሎ ሽባ ስለ ሆነ የዘረጋውን እጁን መመለስ አልቻለም። የእግዚአብሔርም ነቢይ በእግዚአብሔር ስም በተናገረው የትንቢት ቃል መሠረት በእግዚአብሔር የተሰጠውም ምልክት ተፈጸመ፤ መሠዊያው ወዲያውኑ ተሰባብሮ ወደቀ፤ ዐመዱም መሬት ላይ ፈሰሰ። ንጉሡ ኢዮርብዓም “እባክህ እጄን ያድንልኝ ዘንድ ወደ አምላክህ ወደ እግዚአብሔር ጸልይልኝ!” ሲል የእግዚአብሔርን ነቢይ ለመነው። የእግዚአብሔርም ነቢይ ወደ እግዚአብሔር ጸልዮለት የንጉሡ እጅ ዳነች። እንደ ቀድሞም ሆነች። ከዚህም በኋላ ንጉሡ ነቢዩን “ና ከእኔ ጋር አብረህ ወደ ቤቴ ግባ፤ እህልም ቅመስ፤ ስጦታ እሰጥሃለሁ” አለው። የእግዚአብሔር ነቢይ ግን “የሀብትህን እኩሌታ ብትሰጠኝ እንኳ ወደ ቤትህ አልሄድም፤ ከአንተ ጋር እህል ውሃም አልቀምስም። ምንም ዐይነት እህል ውሃ እንዳልቀምስና ወደ ቤቴ ስመለስም በመጣሁበት መንገድ እንኳ እንዳልሄድ እግዚአብሔር አዞኛል” ሲል መለሰለት። ስለዚህም እርሱ ወደ ቤቴል የመጣበትን መንገድ በመተው በሌላ መንገድ ተመልሶ ሄደ።

1 ነገሥት 13:1-10 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)

ኢዮርብዓም መሥዋዕት ለማቅረብ በመሠዊያው አጠገብ ቆሞ ሳለ በጌታ ትእዛዝ የተላከ አንድ ነቢይ እነሆ ከይሁዳ መጥቶ እዚያ ደረሰ፤ ነቢዩም ጌታ ባዘዘው መሠረት ያንን መሠዊያ በመቃወም እንዲህ ሲል የትንቢት ቃል ተናገረበት፦ “መሠዊያ! መሠዊያ ሆይ! ጌታ ስለ አንተ የሚለው ቃል ይህ ነው፦ ‘እነሆ ለዳዊት ቤተሰብ ኢዮስያስ ተብሎ የሚጠራ ልጅ ይወለዳል፤ እርሱም በኮረብታ ላይ ለተሠራው ለአሕዛብ መሠዊያ አገልጋዮች ሆነው መሥዋዕት የሚያቀርቡብህን ካህናት በአንተው ላይ ያርዳቸዋል፤ የሰዎችንም አጥንት በአንተ ላይ ያቃጥላል። ጌታ ይህን ምልክት ይሰጣል፤ ይህ መሠዊያ ተሰባብሮ ይወድቃል፤ በእርሱ ላይ ያለውም ዐመድ ይበተናል፤ ይህንንም የትንቢት ቃል በእኔ አማካይነት የተናገረው ራሱ እግዚአብሔር መሆኑን ይህ እንደ ተፈጸመ ወዲያውኑ ትገነዘባለህ’” አለ። ንጉሡም ይህን በሰማ ጊዜ እጁን አንሥቶ ወደ ነቢዩ በማመልከት! “ያዙት!” የሚል ትእዛዝ ሰጠ፤ የንጉሡም ክንድ ወዲያውኑ ድርቅ ብሎ ሽባ ስለ ሆነ የዘረጋውን እጁን መመለስ አልቻለም። የእግዚአብሔርም ነቢይ በጌታ ስም እንደ ተናገረው መሠዊያው ወዲያውኑ ተሰባብሮ ወደቀ፤ ዐመዱም መሬት ላይ ፈሰሰ። ንጉሡ ኢዮርብዓም “እባክህ እጄን ያድንልኝ ዘንድ ወደ አምላክህ ወደ ጌታ ጸልይልኝ!” ሲል የእግዚአብሔርን ነቢይ ለመነው። የእግዚአብሔርም ነቢይ ወደ ጌታ ጸልዮለት የንጉሡ እጅ ዳነች፤ እንደ ቀድሞም ሆነች። ከዚህም በኋላ ንጉሡ ነቢዩን “ና ከእኔ ጋር አብረህ ወደ ቤቴ ግባ፤ እህልም ቅመስ፤ ስጦታ እሰጥሃለሁ” አለው። የእግዚአብሔር ነቢይ ግን “የሀብትህን እኩሌታ ብትሰጠኝ እንኳ ወደ ቤትህ አልሄድም፤ ከአንተ ጋር እህል ውሃም አልቀምስም። ምንም ዓይነት እህል ውሃ እንዳልቀምስና ወደ ቤቴ ስመለስም በመጣሁበት መንገድ እንኳ እንዳልሄድ ጌታ አዞኛል” ሲል መለሰለት። ስለዚህም እርሱ ወደ ቤቴል የመጣበትን መንገድ በመተው በሌላ መንገድ ተመልሶ ሄደ።