1ኛ መጽሐፈ ነገሥት 13
13
1ኢዮርብዓም መሥዋዕት ለማቅረብ በመሠዊያው አጠገብ ቆሞ ሳለ በጌታ ትእዛዝ የተላከ አንድ ነቢይ እነሆ ከይሁዳ መጥቶ እዚያ ደረሰ፤ 2#2ነገ. 23፥15፤16።ነቢዩም ጌታ ባዘዘው መሠረት ያንን መሠዊያ በመቃወም እንዲህ ሲል የትንቢት ቃል ተናገረበት፦ “መሠዊያ! መሠዊያ ሆይ! ጌታ ስለ አንተ የሚለው ቃል ይህ ነው፦ ‘እነሆ ለዳዊት ቤተሰብ ኢዮስያስ ተብሎ የሚጠራ ልጅ ይወለዳል፤ እርሱም በኮረብታ ላይ ለተሠራው ለአሕዛብ መሠዊያ አገልጋዮች ሆነው መሥዋዕት የሚያቀርቡብህን ካህናት በአንተው ላይ ያርዳቸዋል፤ የሰዎችንም አጥንት በአንተ ላይ ያቃጥላል። 3ጌታ ይህን ምልክት ይሰጣል፤ ይህ መሠዊያ ተሰባብሮ ይወድቃል፤ በእርሱ ላይ ያለውም ዐመድ ይበተናል፤ ይህንንም የትንቢት ቃል በእኔ አማካይነት የተናገረው ራሱ እግዚአብሔር መሆኑን ይህ እንደ ተፈጸመ ወዲያውኑ ትገነዘባለህ’” አለ።
4ንጉሡም ይህን በሰማ ጊዜ እጁን አንሥቶ ወደ ነቢዩ በማመልከት! “ያዙት!” የሚል ትእዛዝ ሰጠ፤ የንጉሡም ክንድ ወዲያውኑ ድርቅ ብሎ ሽባ ስለ ሆነ የዘረጋውን እጁን መመለስ አልቻለም። 5የእግዚአብሔርም ነቢይ በጌታ ስም እንደ ተናገረው መሠዊያው ወዲያውኑ ተሰባብሮ ወደቀ፤ ዐመዱም መሬት ላይ ፈሰሰ። 6ንጉሡ ኢዮርብዓም “እባክህ እጄን ያድንልኝ ዘንድ ወደ አምላክህ ወደ ጌታ ጸልይልኝ!” ሲል የእግዚአብሔርን ነቢይ ለመነው። የእግዚአብሔርም ነቢይ ወደ ጌታ ጸልዮለት የንጉሡ እጅ ዳነች፤ እንደ ቀድሞም ሆነች። 7ከዚህም በኋላ ንጉሡ ነቢዩን “ና ከእኔ ጋር አብረህ ወደ ቤቴ ግባ፤ እህልም ቅመስ፤ ስጦታ እሰጥሃለሁ” አለው።
8የእግዚአብሔር ነቢይ ግን “የሀብትህን እኩሌታ ብትሰጠኝ እንኳ ወደ ቤትህ አልሄድም፤ ከአንተ ጋር እህል ውሃም አልቀምስም። 9ምንም ዓይነት እህል ውሃ እንዳልቀምስና ወደ ቤቴ ስመለስም በመጣሁበት መንገድ እንኳ እንዳልሄድ ጌታ አዞኛል” ሲል መለሰለት። 10ስለዚህም እርሱ ወደ ቤቴል የመጣበትን መንገድ በመተው በሌላ መንገድ ተመልሶ ሄደ።
ሽማግሌው የቤትኤል ነቢይ
11በዚያን ጊዜ በቤትኤል የሚኖር አንድ ሽማግሌ ነቢይ ነበር፤ ወንዶች ልጆቹ ወደ እርሱ ቀርበው፥ ከይሁዳ የመጣው ነቢይ በቤትኤል ስላደረገውና በንጉሥ ኢዮርብዓምም ላይ ስለ ተናገረው ቃል ሁሉ አወሩለት። 12አባታቸውም “ታዲያ ያ የእግዚአብሔር ነቢይ ከዚያ ተነሥቶ በየትኛው መንገድ ሄደ?” ሲል ጠየቃቸው፤ እነርሱም የሄደበትን መንገድ በማመልከት አሳዩት። 13ከዚህም በኋላ እርሱ “አህያዬን ጫኑልኝ!” አላቸው፤ ልጆቹም አህያውን ጭነውለት ሽማግሌው ነቢይ በአህያው ላይ ተቀምጦ፥ 14ከይሁዳ የመጣው የእግዚአብሔር ሰው የሄደበትን መንገድ አቅጣጫ ይዞ ተከተለው፤ በአንድ የባሉጥ ዛፍ ሥር ተቀምጦም አገኘው።
ሽማግሌውም “ከይሁዳ የመጣኸው የእግዚአብሔር ሰው አንተ ነህን?” ሲል ጠየቀው።
እርሱም “አዎ እኔ ነኝ” ሲል መለሰለት።
15ሽማግሌውም “ወደ ቤቴ መጥተህ ከእኔ ጋር እህል ብላ” አለው።
16እርሱም እንዲህ ሲል መለሰለት፦ “ከአንተ ጋር አብሬ መመለስ አልችልም፤ በዚህም ከአንተ ጋር ምንም ዓይነት እህልም ውሃም አልቀምስም። 17በዚህ ቦታ ምንም ዓይነት እህል ውሃ እንዳልቀምስ በመጣሁበት መንገድ እንኳ ተመልሼ እንዳልሄድ ጌታ አዞኛል።”
18ከዚህ በኋላ ከቤትኤል የመጣው ሽማግሌ ነቢይ “እኔም እንዳንተው ነቢይ ነኝ፤ ከእኔ ጋር ወደ ቤቴ ወስጄ እንዳስተናግድህ ከጌታ የታዘዘ መልአክ ነግሮኛል” አለው፤ ነገር ግን ዋሽቶ ነበር።
19ስለዚህ እርሱም ከእርሱ ጋር አብሮት ወደ ቤቱ ሄደ፤ ከእርሱም ጋር ዳቦ በላ፥ ውሀም ጠጣ። 20በገበታም ቀርበው ሳሉ የጌታ ቃል ወደ መለሰው ነቢይ መጣ፤ 21ከይሁዳ ለመጣው ለእግዚአብሔር ሰው እንዲህ አለው፤ “ጌታ እንዲህ ይላል፦ ‘ጌታ አምላክህ ያዘዘህን ትእዛዝ ባለመታዘዝ የጌታን ቃል አላከበርክም። 22ይህን በማድረግ ፈንታ እኔ በዚያ ምንም ዓይነት እህል ውሃ እንዳትቀምስ ወዳዘዝኩህ ቦታ ተመልሰህ በላህ፤ ይህንንም በማድረግህ ምክንያት ትገደላለህ፤ ሬሳህም በቤተሰብህ መቃብር አይቀበርም።’”
23የእግዚአብሔርም ሰው በልቶና ጠጥቶ ካበቃ በኋላ፥ ያ መልሶ ያመጣዉ ነቢይ አህያውን ጫነለት። 24እርሱም በአህያው ላይ ተቀምጦ ሄደ፤ በመንገድም አንበሳ አገኘውና ገደለው፤ ሬሳውም በመንገድ ላይ ተጋደመ፤ አህያውና አንበሳውም በሬሳው አጠገብ ቆመው ነበር። 25አንዳንድ ሰዎች በዚያ በኩል ሲያልፉ አጠገቡ ከቆመው አንበሳ ጋር ሬሳው በመንገድ ላይ ተጋድሞ አዩ፤ ሽማግሌው ነቢይ ወደሚኖርበት ወደ ቤቴል ከተማ መጥተው አወሩ።
26ያም ከመንገድ የመለሰው ነቢይ ይህን በሰማ ጊዜ “ይህ የጌታን ቃል ያቀለለው ያ ጌታ ሰው ነው፤ ጌታ ባስጠነቀቀው መሠረት አሳልፎ ሰጥቶት አንበሳ ሰብሮ ገድሎታል” አለ። 27ከዚህም በኋላ ልጆቹን “አህያዬን ጫኑልኝ!” አላቸው፤ እነርሱም ጫኑለት፤ 28በአህያው ላይ ተቀምጦ ሄደ፤ የነቢዩንም ሬሳ አህያውና አንበሳው እስከ አሁን በአጠገቡ እንደ ቆሙ በመንገድ ላይ ተጋድሞ አገኘው። አንበሳውም የነቢዩን ሬሳ አልበላም፤ በአህያውም ላይ አደጋ አልጣለበትም ነበር። 29ነቢዩም ሬሳውን አንሥቶ በአህያው ላይ ጫነው፤ እንዲለቀስለትና እንዲቀበር ወደ ቤትኤል መልሶ ወሰደው፤ 30በገዛ ራሱም ቤተሰብ መቃብር ቀበረው፤ እነርሱም “ወንድሜ ሆይ! ወንድሜ ሆይ!” እያሉ አለቀሱለት። 31ከቀብሩም ሥነ ሥርዓት በኋላ ልጆቹን እንዲህ አላቸው፦ “እኔ ስሞት በዚሁ መቃብር ቅበሩኝ፤ ሬሳዬንም ከእርሱ ሬሳ አጠገብ አጋድሙት፤ 32በቤትኤል በሚገኘው መሠዊያ ላይና በሰማርያ ታናናሽ ከተሞች በየኮረብታው ባሉት የማምለኪያ ስፍራዎች ላይ ከጌታ በተሰጠው ትእዛዝ መሠረት የተናገረው የትንቢት ቃል በእርግጥ ይፈጸማልና።”
መቅሠፍትን ያስከተለ የኢዮርብዓም አስከፊ ኃጢአት
33ይህም ሁሉ ሆኖ የእስራኤል ንጉሥ ኢዮርብዓም ከሚያደርገው ክፉ ነገር ሁሉ አልተመለሰም፤ ይልቁንም እርሱ በሠራቸው መሠዊያዎች የሚያገለግሉ ከሌዊ ዘር ውጪ ከሆኑ ቤተሰቦች መምረጡን ቀጥሎ ካህን ለመሆን ከፈለገ ማንኛውንም ሰው ይሾመው ነበር፤ 34ይህም ኃጢአቱ ለሥረወ መንግሥቱ መጥፋትና በሙሉ ለመደምሰሱ ምክንያት ሆነ።
Currently Selected:
1ኛ መጽሐፈ ነገሥት 13: መቅካእኤ
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ