መጽሐፈ ነገሥት ቀዳማዊ 13
13
1እነሆም፥ አንድ የእግዚአብሔር ሰው በእግዚአብሔር ቃል ከይሁዳ ወደ ቤቴል መጣ፤ ኢዮርብዓምም መሥዋዕት ይሠዋ ዘንድ#ዕብ. “ዕጣን እያጠነ” ይላል። በመሠዊያው አጠገብ ቆሞ ነበር። 2የእግዚአብሔርም ሰው በመሠዊያው ላይ፥ “መሠዊያ ሆይ፥ መሠዊያ ሆይ፥ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ እነሆ፥ ስሙ ኢዮስያስ የሚባል ልጅ ለዳዊት ቤት ይወለዳል፤ ዕጣንም የሚያጥኑብህን የኮረብታ መስገጃዎቹን ካህናት ይሠዋብሃል፤ የሰዎቹንም አጥንት ያቃጥልብሃል” ብሎ በእግዚአብሔር ቃል ጠራ። 3በዚያም ቀን፦ እግዚአብሔር የተናገረው ቃል ይህ ነው፤ “እነሆ፥ መሠዊያው ይሰነጠቃል፤ በውስጡም ያለው ስብ ይፈስሳል” ብሎ ምልክት ሰጠ። 4ከዚህም በኋላ ንጉሡ ኢዮርብዓም የእግዚአብሔር ሰው በቤቴል ባለው መሠዊያ ላይ የተናገረውን ነገር በሰማ ጊዜ፥ ንጉሡ፥ “ያዙት” ብሎ እጁን ከመሠዊያው ላይ አነሣ። ከዚህም በኋላ በእርሱ ላይ የዘረጋት እጁ ደረቀች፤ ወደ እርሱም ይመልሳት ዘንድ አልተቻለውም። 5የእግዚአብሔርም ሰው በእግዚአብሔር ቃል እንደ ሰጠው ምልክት መሠዊያው ተሰነጠቀ፤ በውስጡም ያለው ስብ ፈሰሰ። 6ንጉሡም ኢዮርብዓም የእግዚአብሔርን ሰው፥ “አሁን የአምላክህን የእግዚአብሔርን ፊት ለምን፤ እጄም ወደ እኔ ትመለስ ዘንድ ስለ እኔ ጸልይ” አለው፥ የእግዚአብሔርም ሰው እግዚአብሔርን ለመነ፤ የንጉሡም እጅ ወደ እርሱ ተመለሰች። እንደ ቀድሞም ሆነች።
7ንጉሡም የእግዚአብሔርን ሰው፥ “ከእኔ ጋር ወደ ቤቴ ና፥ ምሳም ብላ፥ ስጦታም እሰጥሃለሁ” አለው። 8የእግዚአብሔርም ሰው ንጉሡን፥ “የቤትህን እኩሌታ እንኳን ብትሰጠኝ ከአንተ ጋር አልገባም፤ በዚህም ስፍራ እንጀራን አልበላም፤ ውኃም አልጠጣም፤ 9እንጀራም አትብላ፤ ውኃም አትጠጣ፤ በመጣህበት መንገድም አትመለስ ሲል እግዚአብሔር በቃሉ አዝዞኛልና” አለው። 10በሌላም መንገድ ሄደ፤ ወደ ቤቴልም በመጣበት መንገድ አልተመለሰም።
የቤቴሉ ሽማግሌ ነቢይ
11በቤቴልም አንድ ሽማግሌ ነቢይ ይኖር ነበር፤ ልጆቹም ወደ እርሱ መጥተው በዚያች ቀን የእግዚአብሔር ሰው በቤቴል ያደረገውን ሥራ ሁሉ ነገሩት፤ ደግሞም ለንጉሡ የተናገረውን ቃል ሁሉ ለአባታቸው ነገሩት፤ አባታቸውም ተቈጣቸው። 12አባታቸውም፥ “በየትኛው መንገድ ሄደ?” አላቸው። ልጆቹም ከይሁዳ የመጣው የእግዚአብሔር ሰው የሄደበትን መንገድ አመለከቱት። 13ልጆቹንም፥ “አህያዬን ጫኑልኝ” አላቸው፥ አህያውንም ጫኑለት ተቀመጠበትም። 14የእግዚአብሔርንም ሰው ተከትሎት ሄደ፤ ከዛፍ በታችም ተቀምጦ አገኘውና፥ “ከይሁዳ የመጣህ የእግዚአብሔር ሰው አንተ ነህን?” አለው። እርሱም፥ “አዎ፥ እኔ ነኝ” አለ። 15እርሱም፥ “ከእኔ ጋር ወደ ቤቴ ና፥ እንጀራም ብላ” አለው። 16እርሱም፥ “ከአንተ ጋር እመለስና እገባ ዘንድ አይቻለኝም፤ በዚህም ስፍራ ከአንተ ጋር እንጀራ አልበላም፤ ውኃም አልጠጣም፤ 17በዚያ እንጀራ አትብላ፥ ውኃም አትጠጣ፤ በመጣህበት መንገድም አትመለስ ብሎ እግዚአብሔር በቃሉ አዝዞኛልና” አለው። 18እርሱም፥ “እኔ ደግሞ እንዳንተ ነቢይ ነኝ፤ መልአክም፦ እንጀራ ይበላ ዘንድ ውኃም ይጠጣ ዘንድ ከአንተ ጋር ወደ ቤትህ መልሰው ብሎ በእግዚአብሔር ቃል ተናገረኝ” አለው። ዋሽቶም ተናገረው። 19መለሰውም፥ በቤቱም እንጀራ በላ፤ ውኃም ጠጣ።
20በማዕድም ተቀምጠው ሳሉ የእግዚአብሔር ቃል ወደ መለሰው ነቢይ መጣ፤ 21ከይሁዳም የመጣውን የእግዚአብሔርን ሰው እንዲህ አለው፥ “እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ በእግዚአብሔር ቃል ላይ አምፀሃልና፥ አምላክህ እግዚአብሔርም ያዘዘህን ትእዛዝ አልጠበቅህምና፥ 22ተመልሰህም፦ እንጀራ አትብላ፥ ውኃም አትጠጣ ባለህ ስፍራ እንጀራ በልተሃልና፥ ውኃም ጠጥተሃልና ሬሳህ ወደ አባቶችህ መቃብር አይገባም።” 23እንጀራም ከበላ፥ ውኃም ከጠጣ በኋላ ለተመለሰው ነቢይ አህያውን ጫኑለት። 24ተነሥቶም ሄደ፤ በመንገዱም ላይ አንበሳ አግኝቶ ገደለው፤ ሬሳውም በመንገድ ላይ ተጋድሞ ነበር፤ አህያውም በእርሱ አጠገብ ቆሞ ነበር፤ አንበሳውም ደግሞ በሬሳው አጠገብ ቆሞ ነበር። 25እነሆም፥ መንገድ አላፊ ሰዎች ሬሳውን በመንገዱ ወድቆ፥ አንበሳውም በሬሳው አጠገብ ቆሞ አዩ፤ ገብተውም ሽማግሌው ነቢይ ይኖርበት በነበረው ከተማ አወሩ።
26ያም ከመንገድ የመለሰው ነቢይ ያን ሰምቶ፥ “በእግዚአብሔር ቃል ላይ ያመፀ ያ የእግዚአብሔር ሰው ነው”#ዕብ. “እግዚአብሔር እንደተናገረው ቃል እግዚአብሔር ለአንበሳ አሳልፎ ሰጥቶታል ሰብሮም ገድሎታል” የሚል ይጨምራል። አለ። 27ልጆቹንም፥ “አህያዬን ጫኑልኝ” አላቸው፤ እነርሱም ጫኑለት። 28ሄዶም፥ ሬሳው በመንገድ ወድቆ፥ በሬሳውም አጠገብ አህያውና አንበሳው ቆመው፥ አንበሳውም ሬሳውን ሳይበላው፥ አህያውንም ሳይሰብረው አገኘ። 29ነቢዩም የእግዚአብሔርን ሰው ሬሳ አነሣ፤ በአህያውም ላይ ጫነው፤ ነቢዩም በራሱ መቃብር ይቀብረው ዘንድ ወደ ገዛ ከተማው አመጣው፤ 30ዋይ ዋይ፥ ወንድሜ ሆይ፥ እያሉም አለቀሱለት። 31ከቀበሩትም በኋላ ልጆቹን እንዲህ ብሎ ተናገራቸው፥ “በሞትሁ ጊዜ የእግዚአብሔር ሰው በተቀበረበት መቃብር ቅበሩኝ፤ አጥንቶቼ ከአጥንቶቹ ጋር ይድኑ ዘንድ አጥንቶቼን በአጥንቶቹ አጠገብ አኑሩ፤ 32በቤቴል ባለው መሠዊያ ላይ፥ በሰማርያም ከተሞች ውስጥ ባሉት በኮረብታዎቹ መስገጃዎች ላይ በእግዚአብሔር ቃል የተናገረው ነገር በእውነት ይደርሳልና።”
33ከዚህም በኋላ ኢዮርብዓም ከክፋቱ አልተመለሰም፤ ነገር ግን ለኮረብታዎቹ መስገጃዎች አብልጦ ከሕዝብ ሁሉ የጣዖት ካህናትን ሾመ፤ የሚወድደውንም ሁሉ ይቀድስ ነበር፤ እርሱም ለኮረብቶቹ መስገጃዎች ካህን ይሆን ነበር። 34ይህም ነገር ከገጸ ምድር ለመፍረስና ለመጥፋት በኢዮርብዓም ቤት ላይ ኀጢአት ሆነ።
Currently Selected:
መጽሐፈ ነገሥት ቀዳማዊ 13: አማ2000
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ