መጽሐፈ ነገሥት ቀዳማዊ 12
12
የእስራኤል መንግሥት ለሁለት እንደ ተከፈለ
(2ዜ.መ. 10፥1-19)
1እስራኤልም ሁሉ ያነግሡት ዘንድ ወደ ሰቂማ መጥተው ነበርና ሮብዓም ወደ ሰቂማ ሄደ። 2እንዲህም ሆነ፥ የናባጥ ልጅ ኢዮርብዓም ገና በግብፅ ሳለ ይህን በሰማ ጊዜ፥ ኢዮርብዓም ከንጉሡ ከሰሎሞን ፊት ኰብልሎ በግብፅ ተቀምጦ ነበረ፤ 3በግብፅም ሳለ ልከው ጠሩት፤ ኢዮርብዓምና የእስራኤል ጉባኤ ሁሉ መጥተው ሮብዓምን እንዲህ ብለው አነጋገሩት፦ 4“አባትህ ቀንበር አክብዶብን ነበር፤ አሁንም አንተ ጽኑውን የአባትህን አገዛዝ፥ በላያችንም የጫነውን የከበደውን ቀንበር አቃልልልን፤ እኛም እንገዛልሃለን።” 5እርሱም፥ “ሂዱ፥ በሦስተኛውም ቀን ወደ እኔ ተመለሱ” አላቸው። ሕዝቡም ሄዱ።
6ንጉሡም ሮብዓም፥ “ለዚህ ሕዝብ እመልስለት ዘንድ የምትመክሩኝ ምንድን ነው?” ብሎ አባቱ ሰሎሞን በሕይወቱ ሳለ በፊቱ ይቆሙ ከነበሩት ሽማግሌዎች ጋር ተማከረ። 7እነርሱም፥ “ለዚህ ሕዝብ አሁን አገልጋይ ብትሆን፥ ብትገዛላቸውም፥ መልሰህም በገርነት ብትነግራቸው፥ በዘመኑ ሁሉ አገልጋዮችህ ይሆኑልሃል” ብለው ተናገሩት። 8እርሱ ግን ሽማግሌዎች የመከሩትን ምክር ትቶ ከእርሱ ጋር ካደጉትና በፊቱ ይቆሙ ከነበሩት ብላቴኖች ጋር ተማከረ። 9እርሱም፥ “አባትህ የጫነብንን ቀንበር አቃልልልን ለሚሉኝ ሕዝብ እመልስላቸው ዘንድ የምትመክሩኝ ምንድን ነው?” አላቸው። 10ከእርሱም ጋር ያደጉት፥ በፊቱ የሚቆሙት ብላቴኖች እንዲህ አሉት፥ “አባትህ ቀንበር አክብዶብናል፥ አንተ ግን ዛሬ አቃልልልን ለሚሉህ ሕዝብ፦ ታናሺቱ ጣቴ ከአባቴ ወገብ ትወፍራለች። 11አሁንም አባቴ ከባድ ቀንበር ጭኖባችኋል፥ እኔ ግን በቀንበራችሁ ላይ እጨምራለሁ፤ አባቴ በአለንጋ ገርፎአችኋል፥ እኔ ግን በጊንጥ እገርፋችኋለሁ በላቸው።” ይህም ቃል ሮብዓምን ደስ አሰኘው።#“ይህም ቃል ሮብዓምን ደስ አሰኘው” የሚለው በግሪክ ሰባ. ሊ. እና በዕብ. የለም።
12ንጉሡም፥ “በሦስተኛው ቀን ወደ እኔ ተመለሱ” ብሎ እንደ ተናገረ ኢዮርብዓምና#“ኢዮርብዓምና” የሚለው በግሪክ ሰባ. ሊ. የለም። ሕዝቡ ሁሉ በሦስተኛው ቀን ወደ ሮብዓም መጡ። 13ንጉሡም ሽማግሌዎች የመከሩትን ምክር ትቶ ለሕዝቡ ጽኑ ምላሽ መለሰላቸው። 14እንደ ብላቴኖችም ምክር፥ “አባቴ ቀንበር አክብዶባችሁ ነበር፥ እኔ ግን በቀንበራችሁ ላይ እጨምራለሁ፤ አባቴ በአለንጋ ገርፎአችሁ ነበር፥ እኔ ግን በጊንጥ እገርፋችኋለሁ” ብሎ ተናገራቸው። 15እግዚአብሔርም በሴሎናዊው በአኪያ አፍ ለናባጥ ልጅ ለኢዮርብዓም የተናገረውን ነገር እንዲያጸና ለውጡ ከእግዚአብሔር ዘንድ ነበርና ንጉሡ ሕዝቡን አልሰማም።
16እስራኤልም ሁሉ ንጉሡ እንዳልሰማቸው ባዩ ጊዜ ሕዝቡ#ግሪክ ሰባ. ሊ. “በአንድ ድምፅ ...” ይላል። ለንጉሡ፥ “በዳዊት ዘንድ ምን ክፍል አለን? በእሴይም ልጅ ዘንድ ርስት የለንም። እስራኤል ሆይ፥ ወደ ድንኳኖቻችሁ ተመለሱ፤ ዳዊት ሆይ፥ አሁን የራስህን ቤት ተመልከት” ብለው መለሱለት። እስራኤልም ወደየቤታቸው ተመለሱ። 17በይሁዳ ከተሞች በተቀመጡት በእስራኤል ልጆች ላይ ግን ሮብዓም ነገሠ። 18ንጉሡም ሮብዓም አስገባሪውን አዶኒራምን ላከ፤ እስራኤልም ሁሉ በድንጋይ ደበደቡት፥ ሞተም። ንጉሡም ሮብዓም ፈጥኖ ወደ ሰረገላው ወጣ፤ ወደ ኢየሩሳሌምም ሸሸ። 19እስራኤልም እስከ ዛሬ ድረስ የዳዊትን ቤት ከዱት። 20ከዚህም በኋላ እስራኤል በሙሉ ኢዮርብዓም ከግብፅ እንደ ተመለሰ በሰሙ ጊዜ ልከው ወደ ሸንጎአቸው ጠሩት፤ በእስራኤልም ሁሉ ላይ አነገሡት። ከብቻው ከይሁዳና ከብንያም ነገድ በቀር የዳዊትን ቤት የተከተለ ማንም አልነበረም።
21ሮብዓም ግን ወደ ኢየሩሳሌም መጣ፤ የእስራኤልንም ቤት ወግተው መንግሥቱን ወደ ሰሎሞን ልጅ ወደ ሮብዓም ይመልሱ ዘንድ ከይሁዳ ቤት ሁሉና ከብንያም ነገድ የተመረጡትን አንድ መቶ ሃያ ሺህ#ዕብ. “መቶ ሰማንያ ሺህ” ይላል። ተዋጊዎች ሰዎችን ሰበሰበ። 22የእግዚአብሔርም ቃል ወደ እግዚአብሔር ሰው ወደ ሳማያ እንዲህ ሲል መጣ። 23ለይሁዳ ንጉሥ ለሰሎሞን ልጅ ለሮብዓምና ለይሁዳ፥ ለብንያምም ቤት ሁሉ፥ ለቀረውም ሕዝብ ሁሉ፦ እንዲህ ብለህ ንገራቸው። 24“እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ ይህ ነገር ከእኔ ዘንድ ነውና አትውጡ፤ የእስራኤልንም ልጆች ወንድሞቻችሁን አትውጉ፤ እያንዳንዱም ወደ ቤቱ ይመለስ።” እነርሱም የእግዚአብሔርን ቃል ሰሙ፤ እንደ እግዚአብሔርም ቃል ተመልሰው ሄዱ።
የኢዮርብዓም ወደ አምልኮ ጣኦት ማዘንበል
25ኢዮርብዓምም በተራራማው በኤፍሬም ሀገር ሰቂማን ሠርቶ በዚያ ተቀመጠ፤ ደግሞም ከዚያ ወጥቶ ፋኑኤልን ሠራ። 26ኢዮርብዓምም በልቡ አለ፥ “እነሆ፥ ዛሬ መንግሥት ወደ ዳዊት ቤት ይመለሳል። 27ይህ ሕዝብ በኢየሩሳሌም በእግዚአብሔር ቤት መሥዋዕትን ያቀርብ ዘንድ ቢወጣ፥ የዚህ ሕዝብ ልብ ወደ ጌታቸው ወደ ይሁዳ ንጉሥ ወደ ሮብዓም ይመለሳል፥ እኔንም ይወጉኛል።” 28ንጉሡም ተማከረ፤ ሁለትም የወርቅ ጥጆች ሠርቶ፥ “እስራኤል ሆይ፥ ወደ ኢየሩሳሌም መውጣት ይበቃችኋል፤ ከግብፅ ምድር ያወጡአችሁ አማልክቶቻችሁ እነሆ” አላቸው። 29አንዱን በቤቴል ሁለተኛውንም በዳን አኖረ። 30ይህም ኀጢአት ሆነ፥ ሕዝቡ በዳን ወዳለች ወደ አንዲቱ ጣዖት ይሄዱ ነበርና። 31በኮረብቶቹም ላይ መስገጃዎችን ሠራ፤ ከሌዊ ልጆች ካይደሉ ከማንኛውም ሕዝብ ሁሉ የጣዖት ካህናትን ሾመ። 32ኢዮርብዓምም በስምንተኛው ወር ከወሩም በዐሥራ አምስተኛው ቀን በይሁዳ እንደሚደረግ በዓል ያለ በዓል አደረገ፤ ለሠራቸውም ጥጆች ይሠዋ ዘንድ በቤቴል ወደ ሠራው መሠዊያ ወጣ፤ ለኮረብታ መስገጃዎችም የመረጣቸውን እነዚያን ካህናት በቤቴል አኖራቸው። 33በስምንተኛውም ወር በዐሥራ አምስተኛው ቀን በልቡ ባሰበው ቀን ወደ ሠራው መሠዊያ ወጣ፤ ለእስራኤልም ልጆች በዓል አደረገላቸው፤ ወደ መሠዊያውም ሊሠዋ ወጣ።
Currently Selected:
መጽሐፈ ነገሥት ቀዳማዊ 12: አማ2000
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ