1 ቆሮንቶስ 15:42-53
1 ቆሮንቶስ 15:42-53 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
የሙታን ትንሣኤም እንደዚሁ ነው፤ የሚበሰብስ አካል ይዘራል፤ የማይበሰብስ አካል ሆኖ ይነሣል፤ በውርደት ይዘራል፤ በክብር ይነሣል፤ በድካም ይዘራል በኀይል ይነሣል፤ ፍጥረታዊ አካል ይዘራል፤ መንፈሳዊ አካል ይነሣል። ፍጥረታዊ አካል ካለ መንፈሳዊ አካል ደግሞ አለ። ስለዚህ፣ “የመጀመሪያው ሰው አዳም ሕያው ነፍስ ሆነ” ተብሎ ተጽፏል፤ የኋለኛው አዳም ግን ሕይወትን የሚሰጥ መንፈስ ሆነ። ነገር ግን በመጀመሪያ የመጣው መንፈሳዊው ሳይሆን ፍጥረታዊው ነው፤ ከዚያም በኋላ መንፈሳዊው መጣ። የመጀመሪያው ሰው ከምድር የተገኘ ምድራዊ ነው፤ የኋለኛው ግን ከሰማይ ነው። ከምድር የሆኑት እንደ ምድራዊው ናቸው፤ ከሰማይ የሆኑትም እንደ ሰማያዊው ናቸው። የምድራዊውን ሰው መልክ እንደ ለበስን፣ የሰማያዊውን ሰው መልክ ደግሞ እንለብሳለን። ወንድሞች ሆይ፤ ይህን እነግራችኋለሁ፤ ሥጋና ደም የእግዚአብሔርን መንግሥት አይወርሱም፤ የሚጠፋውም የማይጠፋውን አይወርስም። እነሆ፤ አንድ ምስጢር እነግራችኋለሁ፤ ሁላችን አናንቀላፋም፤ ነገር ግን ሁላችንም እንለወጣለን፤ ይህም የሚሆነው የመጨረሻው መለከት ሲነፋ ድንገት በቅጽበተ ዐይን ነው። መለከት ይነፋል፤ ሙታን የማይበሰብሱ ሆነው ይነሣሉ፤ እኛም እንለወጣለን። የሚጠፋው የማይጠፋውን፣ የሚሞተው የማይሞተውን ሊለብስ ይገባዋልና።
1 ቆሮንቶስ 15:42-53 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
የሙታን ትንሣኤያቸው እንዲሁ ነው፥ በሚፈርስ አካል ይዘራል፤ በማይፈርስ አካል ይነሣል። በውርደት ይዘራል፤ በክብር ይነሣል፤ በድካም ይዘራል፤ በኀይል ይነሣል። ሥጋዊ አካል ይዘራል፤ መንፈሳዊ አካል ይነሣል፤ ሥጋዊ አካል አለና መንፈሳዊ አካልም ደግሞ አለ። መጽሐፍ እንዲሁ ብሎአልና የመጀመሪያው ሰው አዳም በነፍስ ሕያው ሆኖ ተፈጠረ፤ ሁለተኛው አዳም ግን ሕይወትን የሚሰጥ መንፈስ ነው። ነገር ግን አስቀድሞ ሥጋዊው፥ ቀጥሎም መንፈሳዊው ነው እንጂ፥ መንፈሳዊው መጀመሪያው አይደለም። መጀመሪያው ሰው ከመሬት የተገኘ መሬታዊ ነው፤ ሁለተኛው ሰው ከሰማይ የወረደ ሰማያዊ ነው። መሬታውያኑ እንደዚያ እንደ መሬታዊው ናቸው፤ ሰማያውያኑም እንደዚያ እንደ ሰማያዊው ናቸው። የመሬታዊውን መልክ እንደ ለበስን እንዲሁ የሰማያዊውን መልክ ደግሞ እንለብሳለን። ወንድሞቻችን ሆይ፥ ይህን እንነግራችኋለን፦ ሥጋዊና ደማዊ የእግዚአብሔርን መንግሥት አይወርስም፥ የሚፈርሰው የማይፈርሰውን አይወርስም። እነሆ፥ አንድ ምሥጢርን እነግራችኋለሁ፥ ሁላችን የምንሞት አይደለም። ነገር ግን የኋለኛው መለከት ሲነፋ ሁላችን እንደ ዐይን ጥቅሻ በአንድ ጊዜ እንለወጣለን፤ መለከት ይነፋል፤ ሙታንም የማይፈርሱ ሁነው ይነሣሉ፤ እኛም እንለወጣለን። ይህ የሚፈርሰው የማይፈርሰውን፥ ይህም የሚሞተው የማይሞተውን ይለብስ ዘንድ አለውና።
1 ቆሮንቶስ 15:42-53 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
የሙታን ትንሣኤ ደግሞ እንዲሁ ነው። በመበስበስ ይዘራል፥ ባለመበስበስ ይነሣል፤ በውርደት ይዘራል፥ በክብር ይነሣል፤ በድካም ይዘራል፥ በኃይል ይነሣል፤ ፍጥረታዊ አካል ይዘራል፥ መንፈሳዊ አካል ይነሣል። ፍጥረታዊ አካል ካለ መንፈሳዊ አካል ደግሞ አለ። እንዲሁ ደግሞ፦ ፊተኛው ሰው አዳም ሕያው ነፍስ ሆነ ተብሎ ተጽፎአል፤ ኋለኛው አዳም ሕይወትን የሚሰጥ መንፈስ ሆነ። ነገር ግን አስቀድሞ ፍጥረታዊው ቀጥሎም መንፈሳዊው ነው እንጂ መንፈሳዊው መጀመሪያ አይደለም። የፊተኛው ሰው ከመሬት መሬታዊ ነው፤ ሁለተኛው ሰው ከሰማይ ነው። መሬታዊው እንደ ሆነ መሬታውያን የሆኑት ደግሞ እንዲሁ ናቸው፥ ሰማያዊው እንደ ሆነ ሰማያውያን የሆኑት ደግሞ እንዲሁ ናቸው። የዚያንም የመሬታዊውን መልክ እንደ ለበስን የሰማያዊውን መልክ ደግሞ እንለብሳለን። ነገር ግን፥ ወንድሞች ሆይ፥ ይህን እላለሁ፦ ሥጋና ደም የእግዚአብሔርን መንግሥት ሊወርሱ አይችሉም፥ የሚበሰብሰውም የማይበሰብሰውን አይወርስም። እነሆ፥ አንድ ምሥጢር እነግራችኋለሁ፤ ሁላችን አናንቀላፋም ነገር ግን የኋለኛው መለከት ሲነፋ ሁላችን በድንገት በቅጽበት ዓይን እንለወጣለን፤ መለከት ይነፋልና ሙታንም የማይበሰብሱ ሆነው ይነሣሉ እኛም እንለወጣለን። ይህ የሚበሰብሰው የማይበሰብሰውን ሊለብስ ይህም የሚሞተው የማይሞተውን ሊለብስ ይገባዋልና።
1 ቆሮንቶስ 15:42-53 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
ከሞት የሚነሡ ሰዎች ሁኔታ ይህንኑ ይመስላል፤ የሚጠፋ ሟች አካል ሆኖ የተዘራው የማይጠፋ ሕያው አካል ሆኖ ይነሣል። በውርደት የተዘራው በክብር ይነሣል፤ ደካማ ሆኖ የተዘራው ኀይለኛ ሆኖ ይነሣል፤ ሥጋዊ አካል ሆኖ የተዘራው መንፈሳዊ አካል ሆኖ ይነሣል። ሥጋዊ አካል ካለ መንፈሳዊ አካልም አለ። ስለዚህ “የመጀመሪያው ሰው አዳም ሕያው ፍጡር ሆነ” ተብሎ ተጽፎአል፤ የኋለኛው አዳም ክርስቶስ ግን ሕይወትን የሚሰጥ መንፈስ ሆነ። ነገር ግን በመጀመሪያ የመጣው ሥጋዊው ነው እንጂ መንፈሳዊው አይደለም፤ መንፈሳዊው የመጣው ከሥጋዊው በኋላ ነው። የመጀመሪያው ሰው አዳም የተፈጠረው ከመሬት ስለ ሆነ መሬታዊ ነው፤ ሁለተኛው ሰው የመጣው ከሰማይ ነው። ከመሬት የሆኑት ከመሬት እንደተፈጠረው ናቸው፤ ከሰማይ የሆኑት ከሰማይ እንደመጣው ናቸው። የምድራዊውን ሰው መልክ እንደምንመስል የሰማያዊውንም ሰው መልክ እንመስላለን። ወንድሞች ሆይ! የምነግራችሁ ይህ ነው፤ ሥጋና ደም የእግዚአብሔርን መንግሥት አይወርሱም፤ እንዲሁም የሚጠፋው ሟች አካል የማይጠፋውን ሕያው አካል አይወርስም። እነሆ፥ አንድ ምሥጢር እነግራችኋለሁ። እኛ ሁላችንም አንሞትም፤ ነገር ግን ሁላችንም እንለወጣለን። የምንለወጠውም የመጨረሻው እምቢልታ በሚነፋበት ጊዜ እንደ ዐይን ቅጽበት በአንድ ጊዜ ነው። መለከቱ ይነፋል፤ የሞቱትም ሰዎች የማይጠፉ ሕያዋን ሆነው ይነሣሉ፤ እኛም እንለወጣለን፤ ይህ የሚጠፋው የማይጠፋውን ይህም የሚሞተው የማይሞተውን መልበስ አለበት።
1 ቆሮንቶስ 15:42-53 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
የሙታን ትንሣኤም እንደዚሁ ነው፤ የሚበሰብስ አካል ይዘራል፤ የማይበሰብስ አካል ሆኖ ይነሣል፤ በውርደት ይዘራል፤ በክብር ይነሣል፤ በድካም ይዘራል፥ በኃይል ይነሣል፤ አካላዊ ሰውነት ይዘራል፥ መንፈሳዊ አካል ይነሣል። አካላዊ ሰውነት አለ፤ መንፈሳዊ አካል ደግሞ አለ። ስለዚህ፥ “የመጀመሪያው ሰው አዳም ሕያው ነፍስ ሆነ” ተብሎ ተጽፎአል፤ የኋለኛው አዳም ግን ሕይወትን የሚሰጥ መንፈስ ሆነ። ነገር ግን በመጀመሪያ የመጣው መንፈሳዊው ሳይሆን አካላዊው ነው፤ ከዚያም በኋላ መንፈሳዊው መጣ። የመጀመሪያው ሰው ከምድር የተገኘ ምድራዊ ነው፤ የኋለኛው ግን ከሰማይ ነው። ከምድር የሆኑት እንደ ምድራዊው ናቸው፤ ከሰማይ የሆኑትም እንደ ሰማያዊው ናቸው። የምድራዊውን ሰው መልክ እንደለበስን፥ የሰማያዊውን ሰው መልክ ደግሞ እንለብሳለን። ወንድሞች ሆይ፥ ይህን እነግራችኋለሁ፤ ሥጋና ደም የእግዚአብሔርን መንግሥት አይወርሱም፤ የሚጠፋውም የማይጠፋውን አይወርስም። እነሆ፥ አንድ ምስጢር እነግራችኋለሁ! ሁላችን አናንቀላፋም፤ ነገር ግን ሁላችንም እንለወጣለን፤ የመጨረሻው መለከት ሲነፋ፥ ድንገት፥ በቅጽበተ ዐይን፥ መለከት ይነፋል፤ ሙታን የማይበሰብሱ ሆነው ይነሣሉ፤ እኛም እንለወጣለን። የሚጠፋው የማይጠፋውን፥ የሚሞተው የማይሞተውን ሊለብስ ይገባዋልና።