የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

1 ወደ ቆሮንቶስ ሰዎች 15:42-53

1 ወደ ቆሮንቶስ ሰዎች 15:42-53 አማ05

ከሞት የሚነሡ ሰዎች ሁኔታ ይህንኑ ይመስላል፤ የሚጠፋ ሟች አካል ሆኖ የተዘራው የማይጠፋ ሕያው አካል ሆኖ ይነሣል። በውርደት የተዘራው በክብር ይነሣል፤ ደካማ ሆኖ የተዘራው ኀይለኛ ሆኖ ይነሣል፤ ሥጋዊ አካል ሆኖ የተዘራው መንፈሳዊ አካል ሆኖ ይነሣል። ሥጋዊ አካል ካለ መንፈሳዊ አካልም አለ። ስለዚህ “የመጀመሪያው ሰው አዳም ሕያው ፍጡር ሆነ” ተብሎ ተጽፎአል፤ የኋለኛው አዳም ክርስቶስ ግን ሕይወትን የሚሰጥ መንፈስ ሆነ። ነገር ግን በመጀመሪያ የመጣው ሥጋዊው ነው እንጂ መንፈሳዊው አይደለም፤ መንፈሳዊው የመጣው ከሥጋዊው በኋላ ነው። የመጀመሪያው ሰው አዳም የተፈጠረው ከመሬት ስለ ሆነ መሬታዊ ነው፤ ሁለተኛው ሰው የመጣው ከሰማይ ነው። ከመሬት የሆኑት ከመሬት እንደተፈጠረው ናቸው፤ ከሰማይ የሆኑት ከሰማይ እንደመጣው ናቸው። የምድራዊውን ሰው መልክ እንደምንመስል የሰማያዊውንም ሰው መልክ እንመስላለን። ወንድሞች ሆይ! የምነግራችሁ ይህ ነው፤ ሥጋና ደም የእግዚአብሔርን መንግሥት አይወርሱም፤ እንዲሁም የሚጠፋው ሟች አካል የማይጠፋውን ሕያው አካል አይወርስም። እነሆ፥ አንድ ምሥጢር እነግራችኋለሁ። እኛ ሁላችንም አንሞትም፤ ነገር ግን ሁላችንም እንለወጣለን። የምንለወጠውም የመጨረሻው እምቢልታ በሚነፋበት ጊዜ እንደ ዐይን ቅጽበት በአንድ ጊዜ ነው። መለከቱ ይነፋል፤ የሞቱትም ሰዎች የማይጠፉ ሕያዋን ሆነው ይነሣሉ፤ እኛም እንለወጣለን፤ ይህ የሚጠፋው የማይጠፋውን ይህም የሚሞተው የማይሞተውን መልበስ አለበት።