1 ወደ ቆሮንቶስ ሰዎች 15
15
የክርስቶስ ከሞት መነሣት
1አሁን ደግሞ ወንድሞች ሆይ! ያስተማርኳችሁን የወንጌል ቃል ላስታውሳችሁ እፈልጋለሁ፤ ይህም የወንጌል ቃል እናንተ የተቀበላችሁትና ጸንታችሁ የቆማችሁበት ነው። 2እኔ ያስተማርኳችሁን የወንጌል ቃል አጥብቃችሁ ብትይዙ በእርሱ ትድናላችሁ፤ አለበለዚያ ግን ያመናችሁት በከንቱ ነው።
3እኔ የተቀበልኩትን በመጀመሪያ ደረጃ ያለውን ነገር ለእናንተ አስተላለፍኩላችሁ፤ ያስተላለፍኩላችሁም ነገር በቅዱሳት መጻሕፍት እንደ ተጻፈው ክርስቶስ ስለ ኃጢአታችን ሞተ፤ #ኢሳ. 53፥5-12። 4ተቀበረ፤ በቅዱሳት መጻሕፍት እንደ ተጻፈውም በሦስተኛው ቀን ከሞት ተነሣ የሚል ነው። #መዝ. 16፥8-10፤ ማቴ. 12፥40፤ ሐ.ሥ. 2፥24-32። 5እርሱ ለጴጥሮስ ታየ፤ ኋላም ለዐሥራ ሁለቱ ሐዋርያት ታየ፤ #ማቴ. 28፥16-17፤ ማር. 16፥14፤ ሉቃ. 24፥34፤ ዮሐ. 20፥19። 6ከአምስት መቶ ለሚበልጡ ተከታዮቹም በአንድ ጊዜ ታያቸው፤ ከእነርሱ አብዛኞቹ እስከ አሁን በሕይወት አሉ፤ አንዳንዶቹ ግን ሞተዋል። 7ከዚያም በኋላ ለያዕቆብ ታየ፤ ለሐዋርያትም ሁሉ ታያቸው።
8በመጨረሻም እንደ ጭንጋፍ ለሆንኩት ለእኔ ደግሞ ታየኝ። #ሐ.ሥ. 9፥3-6። 9እኔ የእግዚአብሔርን ቤተ ክርስቲያን ያሳደድኩ ስለ ሆነ ከሐዋርያት ሁሉ ያነስኩና ሐዋርያም ተብዬ ልጠራ የማይገባኝ ነኝ። #ሐ.ሥ. 8፥3። 10ነገር ግን እኔ አሁን የሆንኩትን ሆኜ የምገኘው በእግዚአብሔር ጸጋ ነው፤ የተሰጠኝም ጸጋ ያለ ፍሬ አልቀረም፤ እንዲያውም ከሌሎቹ ይበልጥ በሥራ ደክሜአለሁ፤ ነገር ግን ይህን ያደረገው ከእኔ ጋር ያለው የእግዚአብሔር ጸጋ ነው እንጂ እኔ አይደለሁም። 11እንግዲህ እኔም ሆንኩ እነርሱ የምናስተምረው ይህንኑ ነው፤ እናንተም ያመናችሁት ይህንኑ ነው።
የሰዎች ከሞት መነሣት
12ነገር ግን ክርስቶስ ከሞት እንደ ተነሣ የምናስተምር ከሆነ ከእናንተ አንዳንዶቹ ከሞት መነሣት የለም እንዴት ይላሉ? 13ከሞት መነሣት ከሌለ ክርስቶስ ከሞት አልተነሣም ማለት ነው፤ 14ክርስቶስ ከሞት ካልተነሣ የእኛም ትምህርት ሆነ የእናንተም እምነት ከንቱ መሆኑ ነው፤ 15ደግሞም እግዚአብሔር ክርስቶስን ከሞት አስነሥቶታል ብለን በማስተማራችን ሐሰተኞች የእግዚአብሔር ምስክሮች ሆነናል ማለት ነው፤ እንግዲህ የሞቱት ሰዎች ከሞት ካልተነሡ እግዚአብሔር ክርስቶስንም ከሞት አላስነሣውም ማለት ነው። 16የሞቱት ሰዎች ከሞት ካልተነሡ ክርስቶስም ከሞት አልተነሣም ማለት ነው። 17ክርስቶስ ከሞት ያልተነሣ ከሆነ እምነታችሁ ከንቱ ነው፤ ገና በኃጢአታችሁ ውስጥ ትኖራላችሁ ማለት ነው፤ 18በክርስቶስ አምነው የሞቱት ጠፍተዋል ማለት ነው፤ 19በክርስቶስ ተስፋ የምናደርገው ለዚህ ዓለም ሕይወት ብቻ ከሆነ ከሰዎች ሁሉ ይበልጥ የሚታዘንልን መሆናችን ነው፤
20ነገር ግን ክርስቶስ ለሞቱት ከሞት የመነሣት በኲር ሆኖ በእርግጥ ከሞት ተነሥቶአል። 21ሞት የመጣው በአንዱ ሰው በአዳም ምክንያት እንደ ሆነ ከሞት መነሣትም የሚመጣው በአንዱ ሰው በክርስቶስ ምክንያት ነው። 22በአዳም ምክንያት ሰው ሁሉ እንደሚሞት እንዲሁም በክርስቶስ ምክንያት ሰው ሁሉ ሕይወትን ያገኛል። 23ይህም የሚሆነው ለእያንዳንዱ በየተራው ነው፤ ክርስቶስ ከሞት የመነሣት የመጀመሪያው ምሳሌ ነው፤ በኋላም ክርስቶስ በሚመጣበት ጊዜ የእርሱ የሆኑት ከሞት ይነሣሉ። 24ቀጥሎም እርሱ ግዛትንና ሥልጣንን ኀይልንም ሁሉ አጥፍቶ መንግሥትን ለእግዚአብሔር አብ በሚያስረክብበት ጊዜ የዓለም ፍጻሜ ይሆናል። 25እግዚአብሔር ጠላቶቹን ሁሉ በሥልጣኑ ሥር እስኪያደርግለት ድረስ ክርስቶስ መንገሥ ይገባዋል። #መዝ. 110፥1። 26ተሸንፎ በመጨረሻ የሚደመሰሰው ጠላት ሞት ነው። 27“እግዚአብሔር ሁሉን ነገር በሥልጣኑ ሥር አድርጎለታል” የሚል ተጽፎአል፤ ነገር ግን “ሁሉ ነገር በሥልጣኑ ሥር ሆኖአል” ሲባል ሁሉን ነገር በሥልጣኑ ሥር ያደረገለትን እግዚአብሔር አብን አይጨምርም። #መዝ. 8፥6። 28ሁሉ ነገር በክርስቶስ ሥልጣን ሥር ከሆነ በኋላ እግዚአብሔር አብ ሁሉ በሁሉ ይሆን ዘንድ ወልድ ራሱ ሁሉን ነገር በሥልጣኑ ሥር በአደረገለት በእግዚአብሔር አብ ሥልጣን ሥር ይሆናል።
29እንግዲህ የሞቱ ሰዎች የማይነሡ ከሆነ ስለ ሞቱ ሰዎች የሚጠመቁ ሁሉ ትርፋቸው ምንድን ነው? የሞቱ ሰዎች ከቶ የማይነሡ ከሆነ ሰዎች በእነርሱ ምትክ ስለምን ይጠመቃሉ? 30እኛስ ብንሆን በየሰዓቱ ለአደጋ እየተጋለጥን የምንኖረው ለምንድን ነው? 31ወንድሞች ሆይ! እኔን በየቀኑ ሞት ያጋጥመኛል፤ ይህንንም የምነግራችሁ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ አማካይነት በእናንተ ላይ ያለኝ ትምክሕት እርግጠኛ ስለ ሆነ ነው። 32እንደ ሰው አስተሳሰብ እኔ በኤፌሶን ከአራዊት ጋር መታገሌ ጥቅሜ ምንድን ነው? ሙታን ከሞት የማይነሡ ከሆነማ “ነገ ስለምንሞት ኑ እንብላ፤ እንጠጣ” እንደ ተባለው መሆኑ ነው። #ኢሳ. 22፥13።
33አትታለሉ፤ “መጥፎ ጓደኛ ጥሩውን ጠባይ ያበላሻል።” 34ወደ ልቡናችሁ ተመለሱ፤ ኃጢአትም አትሥሩ፤ በእናንተ መካከል አንዳንዶች እግዚአብሔርን የማያውቁ አሉ። ይህንንም የምለው እንድታፍሩ ብዬ ነው።
ከሞት የተነሣ አካል ሁኔታ
35አንድ ሰው “የሞቱ ሰዎች የሚነሡት እንዴት ነው? ከሞት ሲነሡ የሚኖራቸው አካልስ ምን ዐይነት ነው?” ብሎ ይጠይቅ ይሆናል፤ 36አንተ ሞኝ! የምትዘራው እህል ካልሞተ ሕይወት አይኖረውም፤ 37አንተ ስትዘራም የስንዴ ዘር ወይም ሌላ እህል ብቻ ትዘራለህ እንጂ በኋላ የሚበቅለውን ተክል አይደለም። 38እግዚአብሔር ግን ለዘሩ እንደ ፈለገ አካልን ይሰጠዋል፤ ለእያንዳንዱም ዘር ልዩ ልዩ አካል ይሰጠዋል።
39ሥጋ ሁሉ አንድ ዐይነት አይደለም፤ የሰው ሥጋም አንድ ዐይነት ነው፤ የእንስሳ ሥጋ ሌላ ዐይነት ነው፤ የወፎች ሥጋ ሌላ ዐይነት ነው፤ የዓሣ ሥጋ ሌላ ዐይነት ነው።
40እንዲሁም ሰማያዊ አካል አለ፤ ምድራዊ አካልም አለ፤ ነገር ግን የሰማያዊው አካል ክብር አንድ ዐይነት ነው፤ የምድራዊውም አካል ክብር ሌላ ዐይነት ነው። 41የፀሐይ ክብር አንድ ዐይነት ነው፤ የጨረቃ ክብር ሌላ ዐይነት ነው፤ የከዋክብትም ክብር ሌላ ዐይነት ነው፤ አንዱ ኮከብ ከሌላው ኮከብ የተለየ ክብር አለው።
42ከሞት የሚነሡ ሰዎች ሁኔታ ይህንኑ ይመስላል፤ የሚጠፋ ሟች አካል ሆኖ የተዘራው የማይጠፋ ሕያው አካል ሆኖ ይነሣል። 43በውርደት የተዘራው በክብር ይነሣል፤ ደካማ ሆኖ የተዘራው ኀይለኛ ሆኖ ይነሣል፤ 44ሥጋዊ አካል ሆኖ የተዘራው መንፈሳዊ አካል ሆኖ ይነሣል። ሥጋዊ አካል ካለ መንፈሳዊ አካልም አለ። 45ስለዚህ “የመጀመሪያው ሰው አዳም ሕያው ፍጡር ሆነ” ተብሎ ተጽፎአል፤ የኋለኛው አዳም ክርስቶስ ግን ሕይወትን የሚሰጥ መንፈስ ሆነ። #ዘፍ. 2፥7። 46ነገር ግን በመጀመሪያ የመጣው ሥጋዊው ነው እንጂ መንፈሳዊው አይደለም፤ መንፈሳዊው የመጣው ከሥጋዊው በኋላ ነው። 47የመጀመሪያው ሰው አዳም የተፈጠረው ከመሬት ስለ ሆነ መሬታዊ ነው፤ ሁለተኛው ሰው የመጣው ከሰማይ ነው። 48ከመሬት የሆኑት ከመሬት እንደተፈጠረው ናቸው፤ ከሰማይ የሆኑት ከሰማይ እንደመጣው ናቸው። 49የምድራዊውን ሰው መልክ እንደምንመስል የሰማያዊውንም ሰው መልክ እንመስላለን።
50ወንድሞች ሆይ! የምነግራችሁ ይህ ነው፤ ሥጋና ደም የእግዚአብሔርን መንግሥት አይወርሱም፤ እንዲሁም የሚጠፋው ሟች አካል የማይጠፋውን ሕያው አካል አይወርስም።
51እነሆ፥ አንድ ምሥጢር እነግራችኋለሁ። እኛ ሁላችንም አንሞትም፤ ነገር ግን ሁላችንም እንለወጣለን። 52የምንለወጠውም የመጨረሻው እምቢልታ በሚነፋበት ጊዜ እንደ ዐይን ቅጽበት በአንድ ጊዜ ነው። መለከቱ ይነፋል፤ የሞቱትም ሰዎች የማይጠፉ ሕያዋን ሆነው ይነሣሉ፤ እኛም እንለወጣለን፤ #1ተሰ. 4፥15-17። 53ይህ የሚጠፋው የማይጠፋውን ይህም የሚሞተው የማይሞተውን መልበስ አለበት። 54ይህ የሚጠፋው የማይጠፋውን ይህም የሚሞተው የማይሞተውን በሚለብስበት ጊዜ “ሞት በድል ተዋጠ!” ተብሎ የተጻፈው ይፈጸማል። #ኢሳ. 25፥8። 55እንዲሁም፥
“ሞት ሆይ! ድል መንሣትህ የት ነው?
ሞት ሆይ! ሰውን የምትጐዳበት ኀይል የት ነው?” ተብሎአል። #ሆሴዕ 13፥14።
56የሞት መንደፊያ ኀይል ኃጢአት ነው፤ የኃጢአትም ኀይል ሕግ ነው። 57ነገር ግን በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ አማካይነት ድል መንሣትን ለሚሰጠን ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን!
58ስለዚህ የተወደዳችሁ ወንድሞቼ ሆይ! ጸንታችሁ ቁሙ፤ በምንም ነገር አትናወጡ፤ ለጌታ ሥራ የምትደክሙት በከንቱ አለመሆኑን ዐውቃችሁ፥ ሳታቋርጡ ዘወትር የጌታን ሥራ ለመሥራት ትጉ።
Currently Selected:
1 ወደ ቆሮንቶስ ሰዎች 15: አማ05
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ
© The Bible Society of Ethiopia, 2005
© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997