የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

1 ወደ ቆሮንቶስ ሰዎች 16

16
ለኢየሩሳሌም ምእመናን የተሰበሰበ የገንዘብ ርዳታ
1ለምእመናን ስለሚደረገው የገንዘብ መዋጮ ለገላትያ አብያተ ክርስቲያን በሰጠሁት መመሪያ መሠረት እናንተም እንዲሁ አድርጉ። #ሮም 15፥25-26። 2እኔ በምመጣበት ጊዜ የገንዘብ መዋጮ እንዳይደረግ በየሳምንቱ እሑድ ከእናንተ እያንዳንዱ በሚያገኘው ገቢ መጠን እያዋጣ ለይቶ ያስቀምጥ። 3እኔ ወደ እናንተ በምመጣበት ጊዜ እናንተ የምትመርጥዋቸውን ሰዎች ያዋጣችሁትን ገንዘብ ይዘው ወደ ኢየሩሳሌም እንዲሄዱ ከመሸኛ ደብዳቤ ጋር እልካቸዋለሁ። 4የእኔም መሄድ አስፈላጊ ሆኖ ከተገኘ፤ አብረውኝ ይሄዳሉ።
የጳውሎስ ዕቅዶች
5በመቄዶንያ በኩል ለመሄድ ስለ ዐቀድኩ በዚያ ሳልፍ እግረ መንገዴን ወደ እናንተ እመጣለሁ። #ሐ.ሥ. 19፥21። 6ወደምሄድበት ወደ ማናቸውም ስፍራ ለጒዞዬ የሚሆነኝን ርዳታ እንድታደርጉልኝ ምናልባት እናንተ ዘንድ እቈይ ይሆናል፤ ምናልባትም ክረምቱን ከእናንተ ጋር አሳልፍ ይሆናል፤ 7አሁን ሳልፍ እግረ መንገዴን ልጐበኛችሁ አልፈልግም፤ የጌታ ፈቃድ ቢሆን ጥቂት ረዘም ያለ ጊዜ ከእናንተ ጋር ለመቈየት ተስፋ አደርጋለሁ።
8ነገር ግን እስከ ጰንጠቆስጤ በዓል በኤፌሶን እቈያለሁ። #ዘሌ. 23፥15-21፤ ዘዳ. 16፥9-11። 9ብዙ ሥራ ያለበት ሰፊ በር ተከፍቶልኛል፤ ተቃዋሚዎች ግን ብዙዎች ናቸው። #ሐ.ሥ. 19፥8-10።
10ጢሞቴዎስ ወደ እናንተ በሚመጣበት ጊዜ ያለ ሥጋት ከእናንተ ጋር እንዲቀመጥ እርዱት፤ እርሱም እንደ እኔ የጌታን ሥራ ይሠራል። #1ቆሮ. 4፥17። 11ስለዚህ ማንም እንዳይንቀው፤ እርሱ ከወንድሞች ጋር ወደ እኔ እንዲመጣ ስለምጠብቀው ወደ እኔ በሰላም ተመልሶ እንዲመጣ ለጒዞው የሚያስፈልገውን እርዱት።
12ወንድማችን አጵሎስ ከሌሎች ወንድሞች ጋር እናንተን እንዲጐበኛችሁ በጥብቅ ለምኜው ነበር፤ ነገር ግን እርሱ አሁን ወደ እናንተ ለመምጣት አልፈቀደም፤ ሲመቸው ግን ይመጣል።
የመጨረሻ ምክርና ሰላምታ
13ንቁ፤ በእምነት ጸንታችሁ ቁሙ፤ በርቱ፤ ጠንክሩ። 14የምታደርጉትን ሁሉ በፍቅር አድርጉ።
15ወንድሞች ሆይ! የእስጢፋኖስ ቤተሰብ በአካይያ አገር የመጀመሪያዎቹ አማኞች እንደ ሆኑና ምእመናንን ለማገልገል ራሳቸውን አሳልፈው እንደ ሰጡ ታውቃላችሁ። #1ቆሮ. 1፥16። 16እንደእነዚህ ላሉት ሰዎችና ከእነርሱም ጋር በሥራ ለሚደክሙት ሁሉ እንድትታዘዙ አጥብቄ አሳስባችኋለሁ።
17በእስጢፋኖስና በፈርዶናጥስ በአካይቆስም ወደ እኔ መምጣት ደስ ብሎኛል፤ እናንተ ከእኔ ጋር ባለመገኘታችሁ እነርሱ በእናንተ ምትክ የጐደለኝን አሟልተውልኛል። 18እነርሱ የእኔን መንፈስና የእናንተንም መንፈስ አሳርፈዋል፤ ስለዚህ እንደእነዚህ ያሉትን ሰዎች ዕወቁአቸው።
19በእስያ ያሉ አብያተ ክርስቲያን ሰላምታ ያቀርቡላችኋል፤ አቂላና ጵርስቅላ፥ በቤታቸው የሚሰበሰቡ ክርስቲያኖችም ሁሉ ልባዊ ሰላምታ በጌታ ስም ያቀርቡላችኋል። #ሐ.ሥ. 18፥2። 20እዚህ ያሉ ክርስቲያኖች ሁሉ ሰላምታ ያቀርቡላችኋል፤ በተቀደሰ መሳሳም ሰላምታ ተሰጣጡ።
21እኔ ጳውሎስ ይህን ሰላምታ በገዛ እጄ ጽፌላችኋለሁ።
22ጌታን የማይወድ ቢኖር የተረገመ ይሁን! ጌታችን ሆይ፥ ና!
# 16፥22 ጌታችን ሆይ ና፦ በግሪኩ “ማራ ናታ” ይላል። 23የጌታ ኢየሱስ ጸጋ ከእናንተ ጋር ይሁን።
24ፍቅሬ በኢየሱስ ክርስቶስ ከሁላችሁ ጋር ይሁን፤ አሜን።

ማድመቅ

Share

Copy

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ