1ኛ ወደ ቆሮንቶስ ሰዎች 15:42-53

1ኛ ወደ ቆሮንቶስ ሰዎች 15:42-53 መቅካእኤ

የሙታን ትንሣኤም እንደዚሁ ነው፤ የሚበሰብስ አካል ይዘራል፤ የማይበሰብስ አካል ሆኖ ይነሣል፤ በውርደት ይዘራል፤ በክብር ይነሣል፤ በድካም ይዘራል፥ በኃይል ይነሣል፤ አካላዊ ሰውነት ይዘራል፥ መንፈሳዊ አካል ይነሣል። አካላዊ ሰውነት አለ፤ መንፈሳዊ አካል ደግሞ አለ። ስለዚህ፥ “የመጀመሪያው ሰው አዳም ሕያው ነፍስ ሆነ” ተብሎ ተጽፎአል፤ የኋለኛው አዳም ግን ሕይወትን የሚሰጥ መንፈስ ሆነ። ነገር ግን በመጀመሪያ የመጣው መንፈሳዊው ሳይሆን አካላዊው ነው፤ ከዚያም በኋላ መንፈሳዊው መጣ። የመጀመሪያው ሰው ከምድር የተገኘ ምድራዊ ነው፤ የኋለኛው ግን ከሰማይ ነው። ከምድር የሆኑት እንደ ምድራዊው ናቸው፤ ከሰማይ የሆኑትም እንደ ሰማያዊው ናቸው። የምድራዊውን ሰው መልክ እንደለበስን፥ የሰማያዊውን ሰው መልክ ደግሞ እንለብሳለን። ወንድሞች ሆይ፥ ይህን እነግራችኋለሁ፤ ሥጋና ደም የእግዚአብሔርን መንግሥት አይወርሱም፤ የሚጠፋውም የማይጠፋውን አይወርስም። እነሆ፥ አንድ ምስጢር እነግራችኋለሁ! ሁላችን አናንቀላፋም፤ ነገር ግን ሁላችንም እንለወጣለን፤ የመጨረሻው መለከት ሲነፋ፥ ድንገት፥ በቅጽበተ ዐይን፥ መለከት ይነፋል፤ ሙታን የማይበሰብሱ ሆነው ይነሣሉ፤ እኛም እንለወጣለን። የሚጠፋው የማይጠፋውን፥ የሚሞተው የማይሞተውን ሊለብስ ይገባዋልና።