1 ቆሮንቶስ 15:35-58

1 ቆሮንቶስ 15:35-58 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)

ሙታን እን​ዴት ይነ​ሣሉ? የሚ​ነ​ሡስ በምን አካ​ላ​ቸው ነው? የሚል አለ። አንተ ሰነፍ! አንተ የም​ት​ዘ​ራው እን​ኳን ካል​ፈ​ረሰ አይ​በ​ቅ​ልም። የም​ት​ዘ​ራ​ውም የስ​ንዴ ቢሆን፥ የሌ​ላም ቢሆን የም​ት​ዘ​ራት ቅን​ጣት ብቻ ናት እንጂ ይህ ኋላ የሚ​ገ​ኘው አገ​ዳው አይ​ደ​ለም። እግ​ዚ​አ​ብ​ሔር ግን እንደ ወደደ አገ​ዳን ይሰ​ጠ​ዋል፤ ለእ​ያ​ን​ዳ​ንዱ ዘርም አገ​ዳው እየ​ራሱ ነው። የፍ​ጥ​ረቱ ሁሉ አካል አንድ አይ​ደ​ለ​ምና፤ የሰው አካል ሌላ ነው፤ የእ​ን​ስ​ሳም አካል ሌላ ነው፤ የወፍ አካ​ልም ሌላ ነው፤ የዓሣ አካ​ልም ሌላ ነው። ሰማ​ያዊ አካል አለ፤ ምድ​ራዊ አካ​ልም አለ፤ ነገር ግን በሰ​ማይ ያለው አካል ክብሩ ልዩ ነው፤ በም​ድ​ርም ያለው አካል ክብሩ ልዩ ነው። የፀ​ሐይ ክብሩ ሌላ ነው፤ የጨ​ረ​ቃም ክብሩ ሌላ ነው፤ የከ​ዋ​ክ​ብ​ትም ክብ​ራ​ቸው ሌላ ነው፤ ኮከብ ከኮ​ከብ በክ​ብር ይበ​ል​ጣ​ልና። የሙ​ታን ትን​ሣ​ኤ​ያ​ቸው እን​ዲሁ ነው፥ በሚ​ፈ​ርስ አካል ይዘ​ራል፤ በማ​ይ​ፈ​ርስ አካል ይነ​ሣል። በው​ር​ደት ይዘ​ራል፤ በክ​ብር ይነ​ሣል፤ በድ​ካም ይዘ​ራል፤ በኀ​ይል ይነ​ሣል። ሥጋዊ አካል ይዘ​ራል፤ መን​ፈ​ሳዊ አካል ይነ​ሣል፤ ሥጋዊ አካል አለና መን​ፈ​ሳዊ አካ​ልም ደግሞ አለ። መጽ​ሐፍ እን​ዲሁ ብሎ​አ​ልና የመ​ጀ​መ​ሪ​ያው ሰው አዳም በነ​ፍስ ሕያው ሆኖ ተፈ​ጠረ፤ ሁለ​ተ​ኛው አዳም ግን ሕይ​ወ​ትን የሚ​ሰጥ መን​ፈስ ነው። ነገር ግን አስ​ቀ​ድሞ ሥጋ​ዊው፥ ቀጥ​ሎም መን​ፈ​ሳ​ዊው ነው እንጂ፥ መን​ፈ​ሳ​ዊው መጀ​መ​ሪ​ያው አይ​ደ​ለም። መጀ​መ​ሪ​ያው ሰው ከመ​ሬት የተ​ገኘ መሬ​ታዊ ነው፤ ሁለ​ተ​ኛው ሰው ከሰ​ማይ የወ​ረደ ሰማ​ያዊ ነው። መሬ​ታ​ው​ያኑ እን​ደ​ዚያ እንደ መሬ​ታ​ዊው ናቸው፤ ሰማ​ያ​ው​ያ​ኑም እን​ደ​ዚያ እንደ ሰማ​ያ​ዊው ናቸው። የመ​ሬ​ታ​ዊ​ውን መልክ እንደ ለበ​ስን እን​ዲሁ የሰ​ማ​ያ​ዊ​ውን መልክ ደግሞ እን​ለ​ብ​ሳ​ለን። ወን​ድ​ሞ​ቻ​ችን ሆይ፥ ይህን እን​ነ​ግ​ራ​ች​ኋ​ለን፦ ሥጋ​ዊና ደማዊ የእ​ግ​ዚ​አ​ብ​ሔ​ርን መን​ግ​ሥት አይ​ወ​ር​ስም፥ የሚ​ፈ​ር​ሰው የማ​ይ​ፈ​ር​ሰ​ውን አይ​ወ​ር​ስም። እነሆ፥ አንድ ምሥ​ጢ​ርን እነ​ግ​ራ​ች​ኋ​ለሁ፥ ሁላ​ችን የም​ን​ሞት አይ​ደ​ለም። ነገር ግን የኋ​ለ​ኛው መለ​ከት ሲነፋ ሁላ​ችን እንደ ዐይን ጥቅሻ በአ​ንድ ጊዜ እን​ለ​ወ​ጣ​ለን፤ መለ​ከት ይነ​ፋል፤ ሙታ​ንም የማ​ይ​ፈ​ርሱ ሁነው ይነ​ሣሉ፤ እኛም እን​ለ​ወ​ጣ​ለን። ይህ የሚ​ፈ​ር​ሰው የማ​ይ​ፈ​ር​ሰ​ውን፥ ይህም የሚ​ሞ​ተው የማ​ይ​ሞ​ተ​ውን ይለ​ብስ ዘንድ አለ​ውና። ይህ የሚ​ፈ​ር​ሰው የማ​ይ​ፈ​ር​ሰ​ውን በለ​በሰ ጊዜ፥ የሚ​ሞ​ተ​ውም የማ​ይ​ሞ​ተ​ውን በለ​በሰ ጊዜ፤ “ሞት በመ​ሸ​ነፍ ተዋጠ” ተብሎ የተ​ጻ​ፈው ያን​ጊዜ ይፈ​ጸ​ማል። “ሞት ሆይ፥ እን​ግ​ዲህ መው​ጊ​ያህ ወዴት አለ? መቃ​ብር ሆይ፥ አሸ​ና​ፊ​ነ​ትህ ወዴት አለ?” የሞት መው​ጊያ ኀጢ​አት ናት፥ የኀ​ጢ​አ​ትም ኀይ​ልዋ ኦሪት ናት። በጌ​ታ​ችን በኢ​የ​ሱስ ክር​ስ​ቶስ ድል መን​ሣ​ትን ለሰ​ጠን ለእ​ግ​ዚ​አ​ብ​ሔር ምስ​ጋና ይሁን። አሁ​ንም የተ​ወ​ደ​ዳ​ችሁ ወን​ድ​ሞ​ቻ​ችን ሆይ፥ የጸ​ና​ች​ሁና የማ​ት​ና​ወጡ ሁኑ፤ ዘወ​ትር በጎ ምግ​ባ​ርን አብ​ዝ​ታ​ችሁ ለእ​ግ​ዚ​አ​ብ​ሔር አበ​ር​ክቱ፤ ስለ ጌታ​ችን መድ​ከ​ማ​ችሁ ለከ​ንቱ እን​ዳ​ይ​ደለ ታው​ቃ​ላ​ች​ሁና።

1 ቆሮንቶስ 15:35-58 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

ነገር ግን፣ “ሙታን እንዴት ይነሣሉ? የሚመጡትስ በምን ዐይነት አካል ነው?” የሚል ሰው ሊኖር ይችላል። አንተ ሞኝ! የምትዘራው ካልሞተ ሕይወት አያገኝም። የምትዘራውም የስንዴ ወይም የሌላ ዐይነት ዘር ቅንጣት ብቻ እንጂ ወደ ፊት የምታገኘውን አካል አይደለም። እግዚአብሔር ግን እንደ ፈቀደ አካልን ይሰጠዋል፤ ለእያንዳንዱም የዘር ዐይነት የራሱን አካል ይሰጠዋል። ሥጋ ሁሉ አንድ አይደለም፤ የሰው ሥጋ አንድ ነው፤ የእንስሳት ሥጋ ሌላ ነው፤ የወፎችም ሥጋ ሌላ ነው፤ የዓሦችም ሥጋ ሌላ ነው። እንዲሁም ሰማያውያን አካላት አሉ፤ ምድራውያን አካላት አሉ፤ ነገር ግን የሰማያዊ አካላት ክብር አንድ ነው፤ የምድራዊም አካላት ክብር ሌላ ነው። የፀሓይ ክብር አንድ ዐይነት ነው፤ የጨረቃ ክብር ሌላ ነው፤ የከዋክብት ደግሞ ሌላ ነው፤ የአንዱም ኮከብ ክብር ከሌላው ኮከብ ክብር ይለያል። የሙታን ትንሣኤም እንደዚሁ ነው፤ የሚበሰብስ አካል ይዘራል፤ የማይበሰብስ አካል ሆኖ ይነሣል፤ በውርደት ይዘራል፤ በክብር ይነሣል፤ በድካም ይዘራል በኀይል ይነሣል፤ ፍጥረታዊ አካል ይዘራል፤ መንፈሳዊ አካል ይነሣል። ፍጥረታዊ አካል ካለ መንፈሳዊ አካል ደግሞ አለ። ስለዚህ፣ “የመጀመሪያው ሰው አዳም ሕያው ነፍስ ሆነ” ተብሎ ተጽፏል፤ የኋለኛው አዳም ግን ሕይወትን የሚሰጥ መንፈስ ሆነ። ነገር ግን በመጀመሪያ የመጣው መንፈሳዊው ሳይሆን ፍጥረታዊው ነው፤ ከዚያም በኋላ መንፈሳዊው መጣ። የመጀመሪያው ሰው ከምድር የተገኘ ምድራዊ ነው፤ የኋለኛው ግን ከሰማይ ነው። ከምድር የሆኑት እንደ ምድራዊው ናቸው፤ ከሰማይ የሆኑትም እንደ ሰማያዊው ናቸው። የምድራዊውን ሰው መልክ እንደ ለበስን፣ የሰማያዊውን ሰው መልክ ደግሞ እንለብሳለን። ወንድሞች ሆይ፤ ይህን እነግራችኋለሁ፤ ሥጋና ደም የእግዚአብሔርን መንግሥት አይወርሱም፤ የሚጠፋውም የማይጠፋውን አይወርስም። እነሆ፤ አንድ ምስጢር እነግራችኋለሁ፤ ሁላችን አናንቀላፋም፤ ነገር ግን ሁላችንም እንለወጣለን፤ ይህም የሚሆነው የመጨረሻው መለከት ሲነፋ ድንገት በቅጽበተ ዐይን ነው። መለከት ይነፋል፤ ሙታን የማይበሰብሱ ሆነው ይነሣሉ፤ እኛም እንለወጣለን። የሚጠፋው የማይጠፋውን፣ የሚሞተው የማይሞተውን ሊለብስ ይገባዋልና። የሚጠፋው የማይጠፋውን፣ የሚሞተውም የማይሞተውን በሚለብስበት ጊዜ፣ “ሞት በድል ተዋጠ” ተብሎ የተጻፈው ቃል ይፈጸማል። እንዲሁም፣ “ሞት ሆይ፤ ድል መንሣትህ የት አለ? ሞት ሆይ፤ መንደፊያህስ የት አለ?” የሞት መንደፊያ ኀጢአት ነው፤ የኀጢአትም ኀይል ሕግ ነው። ነገር ግን በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል ድልን ለሚሰጠን ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን። ስለዚህ የተወደዳችሁ ወንድሞቼ ሆይ፤ ጸንታችሁ ቁሙ፤ በምንም ነገር አትናወጡ። ለጌታ ሥራ ዘወትር የምትተጉ ሁኑ፤ ምክንያቱም ለጌታ የምትደክሙት በከንቱ እንዳልሆነ ታውቃላችሁ።

1 ቆሮንቶስ 15:35-58 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)

ነገር ግን ሰው፦ ሙታን እንዴት ይነሣሉ? በምንስ ዓይነት አካል ይመጣሉ? የሚል ይኖር ይሆናል። አንተ ሞኝ፥ አንተ የምትዘራው ካልሞተ ሕያው አይሆንም፤ የምትዘራውም፥ ስንዴ ቢሆን ከሌላም ዓይነት የአንዱ ቢሆን፥ ቅንጣት ብቻ ነው እንጂ የምትዘራው የሚሆነውን አካል አይደለም፤ እግዚአብሔር ግን እንደ ወደደ አካልን ይሰጠዋል ከዘሮችም ለእያንዳንዱ የገዛ አካሉን ይሰጠዋል። ሥጋ ሁሉ አንድ አይደለም፥ የሰው ሥጋ ግን አንድ ነው፥ የእንስሳም ሥጋ ሌላ ነው፥ የወፎችም ሥጋ ሌላ ነው፥ የዓሣም ሥጋ ሌላ ነው። ደግሞ ሰማያዊ አካል አለ፥ ምድራዊም አካል አለ፤ ነገር ግን የሰማያዊ አካል ክብር ልዩ ነው። የምድራዊም አካል ክብር ልዩ ነው። የፀሐይ ክብር አንድ ነው የጨረቃም ክብር ሌላ ነው የከዋክብትም ክብር ሌላ ነው፤ በክብር አንዱ ኮከብ ከሌላው ኮከብ ይለያልና። የሙታን ትንሣኤ ደግሞ እንዲሁ ነው። በመበስበስ ይዘራል፥ ባለመበስበስ ይነሣል፤ በውርደት ይዘራል፥ በክብር ይነሣል፤ በድካም ይዘራል፥ በኃይል ይነሣል፤ ፍጥረታዊ አካል ይዘራል፥ መንፈሳዊ አካል ይነሣል። ፍጥረታዊ አካል ካለ መንፈሳዊ አካል ደግሞ አለ። እንዲሁ ደግሞ፦ ፊተኛው ሰው አዳም ሕያው ነፍስ ሆነ ተብሎ ተጽፎአል፤ ኋለኛው አዳም ሕይወትን የሚሰጥ መንፈስ ሆነ። ነገር ግን አስቀድሞ ፍጥረታዊው ቀጥሎም መንፈሳዊው ነው እንጂ መንፈሳዊው መጀመሪያ አይደለም። የፊተኛው ሰው ከመሬት መሬታዊ ነው፤ ሁለተኛው ሰው ከሰማይ ነው። መሬታዊው እንደ ሆነ መሬታውያን የሆኑት ደግሞ እንዲሁ ናቸው፥ ሰማያዊው እንደ ሆነ ሰማያውያን የሆኑት ደግሞ እንዲሁ ናቸው። የዚያንም የመሬታዊውን መልክ እንደ ለበስን የሰማያዊውን መልክ ደግሞ እንለብሳለን። ነገር ግን፥ ወንድሞች ሆይ፥ ይህን እላለሁ፦ ሥጋና ደም የእግዚአብሔርን መንግሥት ሊወርሱ አይችሉም፥ የሚበሰብሰውም የማይበሰብሰውን አይወርስም። እነሆ፥ አንድ ምሥጢር እነግራችኋለሁ፤ ሁላችን አናንቀላፋም ነገር ግን የኋለኛው መለከት ሲነፋ ሁላችን በድንገት በቅጽበት ዓይን እንለወጣለን፤ መለከት ይነፋልና ሙታንም የማይበሰብሱ ሆነው ይነሣሉ እኛም እንለወጣለን። ይህ የሚበሰብሰው የማይበሰብሰውን ሊለብስ ይህም የሚሞተው የማይሞተውን ሊለብስ ይገባዋልና። ዳሩ ግን ይህ የሚበሰብሰው የማይበሰብሰውን ሲለብስ ይህም የሚሞተው የማይሞተውን ሲለብስ፥ በዚያን ጊዜ፦ ሞት ድል በመነሣት ተዋጠ ተብሎ የተጻፈው ቃል ይፈጸማል። ሞት ሆይ፥ መውጊያህ የት አለ? ሲኦል ሆይ፥ ድል መንሣትህ የት አለ? የሞት መውጊያ ኃጢአት ነው የኃጢአትም ኃይል ሕግ ነው፤ ነገር ግን በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል ድል መንሣትን ለሚሰጠን ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን። ስለዚህ፥ የተወደዳችሁ ወንድሞቼ ሆይ፥ ድካማችሁ በጌታ ከንቱ እንዳይሆን አውቃችኋልና የምትደላደሉ፥ የማትነቃነቁም፥ የጌታም ሥራ ሁልጊዜ የሚበዛላችሁ ሁኑ።

1 ቆሮንቶስ 15:35-58 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)

አንድ ሰው “የሞቱ ሰዎች የሚነሡት እንዴት ነው? ከሞት ሲነሡ የሚኖራቸው አካልስ ምን ዐይነት ነው?” ብሎ ይጠይቅ ይሆናል፤ አንተ ሞኝ! የምትዘራው እህል ካልሞተ ሕይወት አይኖረውም፤ አንተ ስትዘራም የስንዴ ዘር ወይም ሌላ እህል ብቻ ትዘራለህ እንጂ በኋላ የሚበቅለውን ተክል አይደለም። እግዚአብሔር ግን ለዘሩ እንደ ፈለገ አካልን ይሰጠዋል፤ ለእያንዳንዱም ዘር ልዩ ልዩ አካል ይሰጠዋል። ሥጋ ሁሉ አንድ ዐይነት አይደለም፤ የሰው ሥጋም አንድ ዐይነት ነው፤ የእንስሳ ሥጋ ሌላ ዐይነት ነው፤ የወፎች ሥጋ ሌላ ዐይነት ነው፤ የዓሣ ሥጋ ሌላ ዐይነት ነው። እንዲሁም ሰማያዊ አካል አለ፤ ምድራዊ አካልም አለ፤ ነገር ግን የሰማያዊው አካል ክብር አንድ ዐይነት ነው፤ የምድራዊውም አካል ክብር ሌላ ዐይነት ነው። የፀሐይ ክብር አንድ ዐይነት ነው፤ የጨረቃ ክብር ሌላ ዐይነት ነው፤ የከዋክብትም ክብር ሌላ ዐይነት ነው፤ አንዱ ኮከብ ከሌላው ኮከብ የተለየ ክብር አለው። ከሞት የሚነሡ ሰዎች ሁኔታ ይህንኑ ይመስላል፤ የሚጠፋ ሟች አካል ሆኖ የተዘራው የማይጠፋ ሕያው አካል ሆኖ ይነሣል። በውርደት የተዘራው በክብር ይነሣል፤ ደካማ ሆኖ የተዘራው ኀይለኛ ሆኖ ይነሣል፤ ሥጋዊ አካል ሆኖ የተዘራው መንፈሳዊ አካል ሆኖ ይነሣል። ሥጋዊ አካል ካለ መንፈሳዊ አካልም አለ። ስለዚህ “የመጀመሪያው ሰው አዳም ሕያው ፍጡር ሆነ” ተብሎ ተጽፎአል፤ የኋለኛው አዳም ክርስቶስ ግን ሕይወትን የሚሰጥ መንፈስ ሆነ። ነገር ግን በመጀመሪያ የመጣው ሥጋዊው ነው እንጂ መንፈሳዊው አይደለም፤ መንፈሳዊው የመጣው ከሥጋዊው በኋላ ነው። የመጀመሪያው ሰው አዳም የተፈጠረው ከመሬት ስለ ሆነ መሬታዊ ነው፤ ሁለተኛው ሰው የመጣው ከሰማይ ነው። ከመሬት የሆኑት ከመሬት እንደተፈጠረው ናቸው፤ ከሰማይ የሆኑት ከሰማይ እንደመጣው ናቸው። የምድራዊውን ሰው መልክ እንደምንመስል የሰማያዊውንም ሰው መልክ እንመስላለን። ወንድሞች ሆይ! የምነግራችሁ ይህ ነው፤ ሥጋና ደም የእግዚአብሔርን መንግሥት አይወርሱም፤ እንዲሁም የሚጠፋው ሟች አካል የማይጠፋውን ሕያው አካል አይወርስም። እነሆ፥ አንድ ምሥጢር እነግራችኋለሁ። እኛ ሁላችንም አንሞትም፤ ነገር ግን ሁላችንም እንለወጣለን። የምንለወጠውም የመጨረሻው እምቢልታ በሚነፋበት ጊዜ እንደ ዐይን ቅጽበት በአንድ ጊዜ ነው። መለከቱ ይነፋል፤ የሞቱትም ሰዎች የማይጠፉ ሕያዋን ሆነው ይነሣሉ፤ እኛም እንለወጣለን፤ ይህ የሚጠፋው የማይጠፋውን ይህም የሚሞተው የማይሞተውን መልበስ አለበት። ይህ የሚጠፋው የማይጠፋውን ይህም የሚሞተው የማይሞተውን በሚለብስበት ጊዜ “ሞት በድል ተዋጠ!” ተብሎ የተጻፈው ይፈጸማል። እንዲሁም፥ “ሞት ሆይ! ድል መንሣትህ የት ነው? ሞት ሆይ! ሰውን የምትጐዳበት ኀይል የት ነው?” ተብሎአል። የሞት መንደፊያ ኀይል ኃጢአት ነው፤ የኃጢአትም ኀይል ሕግ ነው። ነገር ግን በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ አማካይነት ድል መንሣትን ለሚሰጠን ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን! ስለዚህ የተወደዳችሁ ወንድሞቼ ሆይ! ጸንታችሁ ቁሙ፤ በምንም ነገር አትናወጡ፤ ለጌታ ሥራ የምትደክሙት በከንቱ አለመሆኑን ዐውቃችሁ፥ ሳታቋርጡ ዘወትር የጌታን ሥራ ለመሥራት ትጉ።

1 ቆሮንቶስ 15:35-58 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)

ነገር ግን አንዱ፥ “ሙታን እንዴት ይነሣሉ? የሚወጡትስ በምን ዓይነት አካል ነው?” ብሎ ቢጠይቅ። አንተ ሞኝ! የምትዘራው ካልሞተ ሕይወት አያገኝም። የምትዘራውም የስንዴ ወይም የሌላ ዘር ቅንጣት እንጂ ወደ ፊት የምታገኘውን አካል አይደለም። እግዚአብሔር ግን እንደ ፈቀደ አካልን ይሰጠዋል፤ ለእያንዳንዱም የዘር ዓይነት የራሱን አካል ይሰጠዋል። ሥጋ ሁሉ አንድ አይደለም፤ የሰው ሥጋ አንድ ነው፤ የእንሰሳት ሥጋ ሌላ ነው፤ የዓሣ ሥጋ ሌላ ዓይነት ነው። እንዲሁም ሰማያውያን አካሎች አሉ፤ ምድራውያን አካሎች አሉ፤ ነገር ግን የሰማያዊ አካሎች ክብር አንድ ነው፤ የምድራዊም አካሎች ክብር ሌላ ነው። የፀሓይ ክብር አንድ ነው፤ የጨረቃ ክብር ሌላ ነው፤ የከዋክብት ደግሞ ሌላ ነው፤ የአንዱም ኮከብ ክብር ከሌላው ኮከብ ክብር ይለያል። የሙታን ትንሣኤም እንደዚሁ ነው፤ የሚበሰብስ አካል ይዘራል፤ የማይበሰብስ አካል ሆኖ ይነሣል፤ በውርደት ይዘራል፤ በክብር ይነሣል፤ በድካም ይዘራል፥ በኃይል ይነሣል፤ አካላዊ ሰውነት ይዘራል፥ መንፈሳዊ አካል ይነሣል። አካላዊ ሰውነት አለ፤ መንፈሳዊ አካል ደግሞ አለ። ስለዚህ፥ “የመጀመሪያው ሰው አዳም ሕያው ነፍስ ሆነ” ተብሎ ተጽፎአል፤ የኋለኛው አዳም ግን ሕይወትን የሚሰጥ መንፈስ ሆነ። ነገር ግን በመጀመሪያ የመጣው መንፈሳዊው ሳይሆን አካላዊው ነው፤ ከዚያም በኋላ መንፈሳዊው መጣ። የመጀመሪያው ሰው ከምድር የተገኘ ምድራዊ ነው፤ የኋለኛው ግን ከሰማይ ነው። ከምድር የሆኑት እንደ ምድራዊው ናቸው፤ ከሰማይ የሆኑትም እንደ ሰማያዊው ናቸው። የምድራዊውን ሰው መልክ እንደለበስን፥ የሰማያዊውን ሰው መልክ ደግሞ እንለብሳለን። ወንድሞች ሆይ፥ ይህን እነግራችኋለሁ፤ ሥጋና ደም የእግዚአብሔርን መንግሥት አይወርሱም፤ የሚጠፋውም የማይጠፋውን አይወርስም። እነሆ፥ አንድ ምስጢር እነግራችኋለሁ! ሁላችን አናንቀላፋም፤ ነገር ግን ሁላችንም እንለወጣለን፤ የመጨረሻው መለከት ሲነፋ፥ ድንገት፥ በቅጽበተ ዐይን፥ መለከት ይነፋል፤ ሙታን የማይበሰብሱ ሆነው ይነሣሉ፤ እኛም እንለወጣለን። የሚጠፋው የማይጠፋውን፥ የሚሞተው የማይሞተውን ሊለብስ ይገባዋልና። የሚጠፋው የማይጠፋውን፥ የሚሞተውም የማይሞተውን በሚለብስበት ጊዜ፥ “ሞት በድል ተዋጠ!” ተብሎ የተጻፈው ቃል ይፈጸማል። “ሞት ሆይ፤ ድል መንሣትህ የት አለ? ሞት ሆይ፤ መውጊያህስ የት አለ?”። የሞት መውጊያ ኃጢአት ነው፤ የኃጢአትም ኃይል ሕግ ነው። ነገር ግን በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ አማካይነት ድልን ለሚሰጠን ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን። ስለዚህ፥ የተወደዳችሁ ወንድሞቼ ሆይ፥ ጸንታችሁ ቁሙ፤ በምንም ነገር አትናወጡ። ድካማችሁ በጌታ ከንቱ ሆኖ እንደማይቀር በማወቅ፥ ለጌታ ሥራ ዘወትር የምትተጉ ሁኑ።