1 ወደ ቆሮንቶስ ሰዎች 15:35-58

1 ወደ ቆሮንቶስ ሰዎች 15:35-58 አማ05

አንድ ሰው “የሞቱ ሰዎች የሚነሡት እንዴት ነው? ከሞት ሲነሡ የሚኖራቸው አካልስ ምን ዐይነት ነው?” ብሎ ይጠይቅ ይሆናል፤ አንተ ሞኝ! የምትዘራው እህል ካልሞተ ሕይወት አይኖረውም፤ አንተ ስትዘራም የስንዴ ዘር ወይም ሌላ እህል ብቻ ትዘራለህ እንጂ በኋላ የሚበቅለውን ተክል አይደለም። እግዚአብሔር ግን ለዘሩ እንደ ፈለገ አካልን ይሰጠዋል፤ ለእያንዳንዱም ዘር ልዩ ልዩ አካል ይሰጠዋል። ሥጋ ሁሉ አንድ ዐይነት አይደለም፤ የሰው ሥጋም አንድ ዐይነት ነው፤ የእንስሳ ሥጋ ሌላ ዐይነት ነው፤ የወፎች ሥጋ ሌላ ዐይነት ነው፤ የዓሣ ሥጋ ሌላ ዐይነት ነው። እንዲሁም ሰማያዊ አካል አለ፤ ምድራዊ አካልም አለ፤ ነገር ግን የሰማያዊው አካል ክብር አንድ ዐይነት ነው፤ የምድራዊውም አካል ክብር ሌላ ዐይነት ነው። የፀሐይ ክብር አንድ ዐይነት ነው፤ የጨረቃ ክብር ሌላ ዐይነት ነው፤ የከዋክብትም ክብር ሌላ ዐይነት ነው፤ አንዱ ኮከብ ከሌላው ኮከብ የተለየ ክብር አለው። ከሞት የሚነሡ ሰዎች ሁኔታ ይህንኑ ይመስላል፤ የሚጠፋ ሟች አካል ሆኖ የተዘራው የማይጠፋ ሕያው አካል ሆኖ ይነሣል። በውርደት የተዘራው በክብር ይነሣል፤ ደካማ ሆኖ የተዘራው ኀይለኛ ሆኖ ይነሣል፤ ሥጋዊ አካል ሆኖ የተዘራው መንፈሳዊ አካል ሆኖ ይነሣል። ሥጋዊ አካል ካለ መንፈሳዊ አካልም አለ። ስለዚህ “የመጀመሪያው ሰው አዳም ሕያው ፍጡር ሆነ” ተብሎ ተጽፎአል፤ የኋለኛው አዳም ክርስቶስ ግን ሕይወትን የሚሰጥ መንፈስ ሆነ። ነገር ግን በመጀመሪያ የመጣው ሥጋዊው ነው እንጂ መንፈሳዊው አይደለም፤ መንፈሳዊው የመጣው ከሥጋዊው በኋላ ነው። የመጀመሪያው ሰው አዳም የተፈጠረው ከመሬት ስለ ሆነ መሬታዊ ነው፤ ሁለተኛው ሰው የመጣው ከሰማይ ነው። ከመሬት የሆኑት ከመሬት እንደተፈጠረው ናቸው፤ ከሰማይ የሆኑት ከሰማይ እንደመጣው ናቸው። የምድራዊውን ሰው መልክ እንደምንመስል የሰማያዊውንም ሰው መልክ እንመስላለን። ወንድሞች ሆይ! የምነግራችሁ ይህ ነው፤ ሥጋና ደም የእግዚአብሔርን መንግሥት አይወርሱም፤ እንዲሁም የሚጠፋው ሟች አካል የማይጠፋውን ሕያው አካል አይወርስም። እነሆ፥ አንድ ምሥጢር እነግራችኋለሁ። እኛ ሁላችንም አንሞትም፤ ነገር ግን ሁላችንም እንለወጣለን። የምንለወጠውም የመጨረሻው እምቢልታ በሚነፋበት ጊዜ እንደ ዐይን ቅጽበት በአንድ ጊዜ ነው። መለከቱ ይነፋል፤ የሞቱትም ሰዎች የማይጠፉ ሕያዋን ሆነው ይነሣሉ፤ እኛም እንለወጣለን፤ ይህ የሚጠፋው የማይጠፋውን ይህም የሚሞተው የማይሞተውን መልበስ አለበት። ይህ የሚጠፋው የማይጠፋውን ይህም የሚሞተው የማይሞተውን በሚለብስበት ጊዜ “ሞት በድል ተዋጠ!” ተብሎ የተጻፈው ይፈጸማል። እንዲሁም፥ “ሞት ሆይ! ድል መንሣትህ የት ነው? ሞት ሆይ! ሰውን የምትጐዳበት ኀይል የት ነው?” ተብሎአል። የሞት መንደፊያ ኀይል ኃጢአት ነው፤ የኃጢአትም ኀይል ሕግ ነው። ነገር ግን በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ አማካይነት ድል መንሣትን ለሚሰጠን ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን! ስለዚህ የተወደዳችሁ ወንድሞቼ ሆይ! ጸንታችሁ ቁሙ፤ በምንም ነገር አትናወጡ፤ ለጌታ ሥራ የምትደክሙት በከንቱ አለመሆኑን ዐውቃችሁ፥ ሳታቋርጡ ዘወትር የጌታን ሥራ ለመሥራት ትጉ።