ሙታን እንዴት ይነሣሉ? የሚነሡስ በምን አካላቸው ነው? የሚል አለ። አንተ ሰነፍ! አንተ የምትዘራው እንኳን ካልፈረሰ አይበቅልም። የምትዘራውም የስንዴ ቢሆን፥ የሌላም ቢሆን የምትዘራት ቅንጣት ብቻ ናት እንጂ ይህ ኋላ የሚገኘው አገዳው አይደለም። እግዚአብሔር ግን እንደ ወደደ አገዳን ይሰጠዋል፤ ለእያንዳንዱ ዘርም አገዳው እየራሱ ነው። የፍጥረቱ ሁሉ አካል አንድ አይደለምና፤ የሰው አካል ሌላ ነው፤ የእንስሳም አካል ሌላ ነው፤ የወፍ አካልም ሌላ ነው፤ የዓሣ አካልም ሌላ ነው። ሰማያዊ አካል አለ፤ ምድራዊ አካልም አለ፤ ነገር ግን በሰማይ ያለው አካል ክብሩ ልዩ ነው፤ በምድርም ያለው አካል ክብሩ ልዩ ነው። የፀሐይ ክብሩ ሌላ ነው፤ የጨረቃም ክብሩ ሌላ ነው፤ የከዋክብትም ክብራቸው ሌላ ነው፤ ኮከብ ከኮከብ በክብር ይበልጣልና። የሙታን ትንሣኤያቸው እንዲሁ ነው፥ በሚፈርስ አካል ይዘራል፤ በማይፈርስ አካል ይነሣል። በውርደት ይዘራል፤ በክብር ይነሣል፤ በድካም ይዘራል፤ በኀይል ይነሣል። ሥጋዊ አካል ይዘራል፤ መንፈሳዊ አካል ይነሣል፤ ሥጋዊ አካል አለና መንፈሳዊ አካልም ደግሞ አለ። መጽሐፍ እንዲሁ ብሎአልና የመጀመሪያው ሰው አዳም በነፍስ ሕያው ሆኖ ተፈጠረ፤ ሁለተኛው አዳም ግን ሕይወትን የሚሰጥ መንፈስ ነው። ነገር ግን አስቀድሞ ሥጋዊው፥ ቀጥሎም መንፈሳዊው ነው እንጂ፥ መንፈሳዊው መጀመሪያው አይደለም። መጀመሪያው ሰው ከመሬት የተገኘ መሬታዊ ነው፤ ሁለተኛው ሰው ከሰማይ የወረደ ሰማያዊ ነው። መሬታውያኑ እንደዚያ እንደ መሬታዊው ናቸው፤ ሰማያውያኑም እንደዚያ እንደ ሰማያዊው ናቸው። የመሬታዊውን መልክ እንደ ለበስን እንዲሁ የሰማያዊውን መልክ ደግሞ እንለብሳለን። ወንድሞቻችን ሆይ፥ ይህን እንነግራችኋለን፦ ሥጋዊና ደማዊ የእግዚአብሔርን መንግሥት አይወርስም፥ የሚፈርሰው የማይፈርሰውን አይወርስም። እነሆ፥ አንድ ምሥጢርን እነግራችኋለሁ፥ ሁላችን የምንሞት አይደለም። ነገር ግን የኋለኛው መለከት ሲነፋ ሁላችን እንደ ዐይን ጥቅሻ በአንድ ጊዜ እንለወጣለን፤ መለከት ይነፋል፤ ሙታንም የማይፈርሱ ሁነው ይነሣሉ፤ እኛም እንለወጣለን። ይህ የሚፈርሰው የማይፈርሰውን፥ ይህም የሚሞተው የማይሞተውን ይለብስ ዘንድ አለውና። ይህ የሚፈርሰው የማይፈርሰውን በለበሰ ጊዜ፥ የሚሞተውም የማይሞተውን በለበሰ ጊዜ፤ “ሞት በመሸነፍ ተዋጠ” ተብሎ የተጻፈው ያንጊዜ ይፈጸማል። “ሞት ሆይ፥ እንግዲህ መውጊያህ ወዴት አለ? መቃብር ሆይ፥ አሸናፊነትህ ወዴት አለ?” የሞት መውጊያ ኀጢአት ናት፥ የኀጢአትም ኀይልዋ ኦሪት ናት። በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ድል መንሣትን ለሰጠን ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን። አሁንም የተወደዳችሁ ወንድሞቻችን ሆይ፥ የጸናችሁና የማትናወጡ ሁኑ፤ ዘወትር በጎ ምግባርን አብዝታችሁ ለእግዚአብሔር አበርክቱ፤ ስለ ጌታችን መድከማችሁ ለከንቱ እንዳይደለ ታውቃላችሁና።
ወደ ቆሮንቶስ ሰዎች 1 15 ያንብቡ
ያዳምጡ ወደ ቆሮንቶስ ሰዎች 1 15
ያጋሩ
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: ወደ ቆሮንቶስ ሰዎች 1 15:35-58
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
ቤት
መጽሐፍ ቅዱስ
እቅዶች
ቪዲዮዎች