ወደ ሮም ሰዎች 11:11-24

ወደ ሮም ሰዎች 11:11-24 አማ54

እንግዲህ፦ የተሰናከሉ እስኪወድቁ ድረስ ነውን? እላለሁ። አይደለም፤ ነገር ግን እነርሱን ያስቀናቸው ዘንድ በእነርሱ በደል መዳን ለአሕዛብ ሆነ። ዳሩ ግን በደላቸው ለዓለም ባለ ጠግነት መሸነፋቸውም ለአሕዛብ ባለ ጠግነት ከሆነ፥ ይልቁንስ መሙላታቸው እንዴት ይሆን? ለእናንተም ለአሕዛብ እናገራለሁ። እኔ የአሕዛብ ሐዋርያ በሆንሁ መጠን ሥጋዬ የሆኑትን አስቀንቼ ምናልባት ከእነርሱ አንዳንዱን አድን እንደሆነ አገልግሎቴን አከብራለሁ። የእነርሱ መጣል ለዓለም መታረቅ ከሆነ ከሙታን ከሚመጣ ሕይወት በቀር መመለሳቸው ምን ይሆን? በኵራቱም ቅዱስ ከሆነ ብሆው ደግሞ ቅዱስ ነው፤ ሥሩም ቅዱስ ከሆነ ቅርንጫፎቹ ደግሞ ቅዱሳን ናቸው። ነገር ግን ከቅርንጫፎች አንዳንዱ ቢሰበሩ አንተም የበረሀ ወይራ የሆንህ በመካከላቸው ገብተህ ከእነርሱ ጋር የወይራ ዘይት ከሚወጣው ሥር ተካፋይ ከሆንህ፥ በቅርንጫፎች ላይ አትመካ፤ ብትመካባቸው ግን ሥሩ አንተን ይሸከምሃል እንጂ ሥሩን የምትሸከም አንተ አይደለህም። እንግዲህ፦ እኔ እንድገባ ቅርንጫፎች ተሰበሩ ትል ይሆናል። መልካም፤ እነርሱ ከአለማመን የተነሣ ተሰበሩ አንተም ከእምነት የተነሣ ቆመሃል። ፍራ እንጂ የትዕቢትን ነገር አታስብ። እግዚአብሔር እንደ ተፈጠሩት ለነበሩት ቅርንጫፎች የራራላቸው ካልሆነ ለአንተ ደግሞ አይራራልህምና። እንግዲህ የእግዚአብሔርን ቸርነትና ጭከና ተመልከት፤ ጭከናው በወደቁት ላይ ነው፥ በቸርነቱ ግን ጸንተህ ብትኖር የእግዚአብሔር ቸርነት በአንተ ላይ ነው፤ ያለዚያ አንተ ደግሞ ትቆረጣለህ። እነዚያም ደግሞ በአለማመናቸው ጸንተው ባይኖሩ በዛፉ ውስጥ ይገባሉ፤ እግዚአብሔር መልሶ ሊያገባቸው ይችላልና። አንተ በፍጥረቱ የበረሀ ከነበረ ወይራ ተቆርጠህ እንደ ፍጥረትህ ሳትሆን በመልካም ወይራ ከገባህ፥ ይልቁንስ እነዚያ በፍጥረታቸው ያሉት ቅርንጫፎች በራሳቸው ወይራ እንዴት አይገቡም?