ሮሜ 11:11-24

ሮሜ 11:11-24 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)

እን​ግ​ዲህ እላ​ለሁ፤ ሊወ​ድቁ ተሰ​ና​ከ​ሉን? አይ​ደ​ለም፤ ነገር ግን እስ​ራ​ኤል ይቀኑ ዘንድ እነ​ርሱ በመ​ሰ​ና​ከ​ላ​ቸው ለአ​ሕ​ዛብ ድኅ​ነት ሆነ። የእ​ነ​ርሱ መሰ​ና​ከል ለዓ​ለም ባለ​ጸ​ግ​ነት፥ በደ​ላ​ቸ​ውም ለአ​ሕ​ዛብ ባለ​ጸ​ግ​ነት ከሆነ ፍጹ​ም​ነ​ታ​ቸ​ውማ እን​ዴት በሆነ ነበር? ለእ​ና​ንተ ለአ​ሕ​ዛብ እና​ገ​ራ​ለሁ፤ እኔ ለአ​ሕ​ዛብ ሐዋ​ር​ያ​ቸው እንደ መሆኔ መጠን መል​እ​ክ​ቴን አከ​ብ​ራ​ታ​ለሁ። ይህም በዚህ ዘመ​ዶ​ችን አስ​ቀ​ና​ቸው እንደ ሆነ፥ ከእ​ነ​ርሱ ወገን የሆ​ኑ​ት​ንም አድን እንደ ሆነ ነው። የእ​ነ​ርሱ መው​ጣት ለዓ​ለም ዕርቅ ከሆነ ይል​ቁ​ንም መመ​ለ​ሳ​ቸው ምን ይሆን? ከሙ​ታን በመ​ነ​ሣት የሚ​ገኝ ሕይ​ወት ነው። እር​ሾው ቅዱስ ከሆነ ቡሆ​ውም እን​ዲሁ ቅዱስ ነው፤ ሥርዋ ቅዱስ ከሆ​ነም ቅር​ን​ጫ​ፎ​ችዋ እን​ዲሁ ቅዱ​ሳን ይሆ​ናሉ። ከቅ​ር​ን​ጫ​ፎ​ችዋ አን​ዳ​ን​ዶቹ ቢሰ​በሩ የዱር ወይራ የሆ​ንህ አን​ተን በእ​ነ​ርሱ ፋንታ ተከሉ፤ የእ​ነ​ር​ሱ​ንም ሥር​ነት አገ​ኘህ፤ እንደ እነ​ር​ሱም ዘይት ሆንኽ። በቅ​ር​ን​ጫ​ፎች ላይ አት​ኵራ፤ ብት​ኰራ ግን ሥሩ አን​ተን ይሸ​ከ​ም​ሃል እንጂ አንተ ሥሩን የም​ት​ሸ​ከ​መው አይ​ደ​ለም። ቅር​ን​ጫ​ፎ​ችዋ ተሰ​በሩ፤ በእ​ነ​ር​ሱም ፋንታ “እኔ የዘ​ይት ቅር​ን​ጫፍ ሆንሁ” ትል ይሆ​ናል። አላ​መ​ኑ​ምና ተሰ​በሩ፤ አንተ ግን ስለ አመ​ንህ ቆመ​ሃል፤ እን​ግ​ዲህ ፈር​ተህ ኑር እንጂ ራስ​ህን ከፍ ከፍ አታ​ድ​ርግ። እግ​ዚ​አ​ብ​ሔር በተ​ፈ​ጥ​ሮ​አ​ቸው ቅር​ን​ጫ​ፎች ለነ​በሩ ለእ​ነ​ዚያ ከአ​ል​ራ​ራ​ላ​ቸው ለአ​ን​ተም አይ​ራ​ራ​ል​ህም፤ እን​ግ​ዲህ የእ​ግ​ዚ​አ​ብ​ሔ​ርን ርኅ​ራ​ኄ​ው​ንና ጭካ​ኔ​ውን አስ​ተ​ውል፤ የወ​ደ​ቁ​ትን ቀጣ​ቸው፤ አን​ተን ግን ይቅር እን​ዳ​ለህ ብት​ኖር ማረህ፤ ያለ​ዚያ ግን አን​ተም ትቈ​ረ​ጣ​ለህ። እነ​ር​ሱም ባለ​ማ​መ​ና​ቸው ጸን​ተው ባይ​ኖሩ ይተ​ከ​ላሉ። እግ​ዚ​አ​ብ​ሔር ዳግ​መና ሊተ​ክ​ላ​ቸው ይች​ላ​ልና። አንተ የዱር ወይራ፥ አን​ተን ስንኳ ከበ​ቀ​ል​ህ​በት ቈርጦ ባል​በ​ቀ​ል​ህ​በት በመ​ል​ካሙ ዘይት ስፍራ ከተ​ከ​ለህ፥ ይል​ቁን ጥን​ቱን ዘይት የነ​በ​ሩ​ትን እነ​ዚ​ያን በበ​ቀ​ሉ​በት ስፍራ እን​ዴት አብ​ልጦ ሊተ​ክ​ላ​ቸው አይ​ች​ልም?

ሮሜ 11:11-24 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

ተመልሰው እስከማይድኑ ድረስ ተሰናከሉን? ብዬ እንደ ገና እጠይቃለሁ፤ ከቶ አይሆንም! ይልቁንም እስራኤልን ለማስቀናት ሲባል በእነርሱ መተላለፍ ምክንያት ድነት ለአሕዛብ መጥቷል። ነገር ግን የእነርሱ መተላለፍ ለዓለም በረከት ከሆነ፣ ውድቀታቸውም ለአሕዛብ በረከት ከሆነ፣ ሙላታቸው ምን ያህል ታላቅ በረከት ያመጣ ይሆን? አሕዛብ ሆይ፤ ለእናንተ እናገራለሁ፤ የአሕዛብ ሐዋርያ እንደ መሆኔ መጠን አገልግሎቴን በትጋት እፈጽማለሁ፤ ይኸውም የገዛ ወገኖቼን እንዲቀኑ አነሣሥቼ ከእነርሱ ጥቂቱን ለማዳን ተስፋ በማድረግ ነው። የእነርሱ መተው ለዓለም ዕርቅን ካስገኘ፣ ተቀባይነት ማግኘታቸውማ ከሞት መነሣት ነው ከማለት በቀር ሌላ ምን ሊሆን ይችላል? በኵር ሆኖ የቀረበው የቡሖው ክፍል ቅዱስ ከሆነ፣ ቡሖው ደግሞ ቅዱስ ነው፤ ሥሩ ቅዱስ ከሆነ፣ ቅርንጫፎቹም ቅዱሳን ናቸው። ከቅርንጫፎቹ አንዳንዶቹ ቢሰበሩ፣ አንተም የበረሓ ወይራ ሆነህ ሳለ በሌሎቹ መካከል ገብተህ ከተጣበቅህና ከወይራው ዘይት ሥር የሚገኘውን በረከት ተካፋይ ከሆንህ፣ በእነዚያ ቅርንጫፎች ላይ አትኵራራ። ብትኰራ ግን ይህን አስተውል፤ አንተ ሥሩን አትሸከምም፤ ሥሩ አንተን ይሸከምሃል እንጂ። እንግዲህ፣ “ቅርንጫፎች የተሰበሩት እኔ እንድገባ ነው” ትል ይሆናል። ትክክል ነው፤ እነርሱ የተሰበሩት ካለማመን የተነሣ ነው፤ አንተም በእምነት ቆመሃል፤ ፍራ እንጂ ትዕቢተኛ አትሁን። እግዚአብሔር በተፈጥሮ ቅርንጫፎች ለሆኑት ካልራራላቸው፣ ለአንተም አይራራልህምና። እንግዲህ የእግዚአብሔርን ቸርነትና ጭካኔ ተመልከት፤ ጭካኔውም በወደቁት ላይ ነው፤ ቸርነቱ ግን በቸርነቱ ውስጥ እስካለህ ድረስ ለአንተ ነው፤ አለዚያ ግን አንተም ትቈረጣለህ። እነርሱም ባለማመናቸው ጸንተው ባይኖሩ፣ ተመልሰው ይገባሉ፤ እግዚአብሔር መልሶ ሊያስገባቸው ይችላልና። የበረሓ ከሆነው የወይራ ዛፍ የተቈረጥህና ተፈጥሮህ ወዳልሆነው ወደ መልካሙ ወይራ የገባህ ከሆንህ፣ በተፈጥሯቸው ቅርንጫፎቹ የሆኑት እነዚህ ወደ ራሳቸው ወይራ ዛፍ መግባታቸውማ ምን ያህል ይሆን?

ሮሜ 11:11-24 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)

እንግዲህ፦ የተሰናከሉ እስኪወድቁ ድረስ ነውን? እላለሁ። አይደለም፤ ነገር ግን እነርሱን ያስቀናቸው ዘንድ በእነርሱ በደል መዳን ለአሕዛብ ሆነ። ዳሩ ግን በደላቸው ለዓለም ባለ ጠግነት መሸነፋቸውም ለአሕዛብ ባለ ጠግነት ከሆነ፥ ይልቁንስ መሙላታቸው እንዴት ይሆን? ለእናንተም ለአሕዛብ እናገራለሁ። እኔ የአሕዛብ ሐዋርያ በሆንሁ መጠን ሥጋዬ የሆኑትን አስቀንቼ ምናልባት ከእነርሱ አንዳንዱን አድን እንደሆነ አገልግሎቴን አከብራለሁ። የእነርሱ መጣል ለዓለም መታረቅ ከሆነ ከሙታን ከሚመጣ ሕይወት በቀር መመለሳቸው ምን ይሆን? በኵራቱም ቅዱስ ከሆነ ብሆው ደግሞ ቅዱስ ነው፤ ሥሩም ቅዱስ ከሆነ ቅርንጫፎቹ ደግሞ ቅዱሳን ናቸው። ነገር ግን ከቅርንጫፎች አንዳንዱ ቢሰበሩ አንተም የበረሀ ወይራ የሆንህ በመካከላቸው ገብተህ ከእነርሱ ጋር የወይራ ዘይት ከሚወጣው ሥር ተካፋይ ከሆንህ፥ በቅርንጫፎች ላይ አትመካ፤ ብትመካባቸው ግን ሥሩ አንተን ይሸከምሃል እንጂ ሥሩን የምትሸከም አንተ አይደለህም። እንግዲህ፦ እኔ እንድገባ ቅርንጫፎች ተሰበሩ ትል ይሆናል። መልካም፤ እነርሱ ከአለማመን የተነሣ ተሰበሩ አንተም ከእምነት የተነሣ ቆመሃል። ፍራ እንጂ የትዕቢትን ነገር አታስብ። እግዚአብሔር እንደ ተፈጠሩት ለነበሩት ቅርንጫፎች የራራላቸው ካልሆነ ለአንተ ደግሞ አይራራልህምና። እንግዲህ የእግዚአብሔርን ቸርነትና ጭከና ተመልከት፤ ጭከናው በወደቁት ላይ ነው፥ በቸርነቱ ግን ጸንተህ ብትኖር የእግዚአብሔር ቸርነት በአንተ ላይ ነው፤ ያለዚያ አንተ ደግሞ ትቆረጣለህ። እነዚያም ደግሞ በአለማመናቸው ጸንተው ባይኖሩ በዛፉ ውስጥ ይገባሉ፤ እግዚአብሔር መልሶ ሊያገባቸው ይችላልና። አንተ በፍጥረቱ የበረሀ ከነበረ ወይራ ተቆርጠህ እንደ ፍጥረትህ ሳትሆን በመልካም ወይራ ከገባህ፥ ይልቁንስ እነዚያ በፍጥረታቸው ያሉት ቅርንጫፎች በራሳቸው ወይራ እንዴት አይገቡም?

ሮሜ 11:11-24 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)

እስቲ፥ እንደገና ልጠይቅ፤ አይሁድ የወደቁት ዳግመኛ እንደማይነሡ ሆነው ነውን? አይደለም! በአይሁድ በደል ምክንያት አሕዛብ መዳንን አገኙ፤ ይህም የሆነው አይሁድ በአሕዛብ እንዲቀኑ ለማድረግ ነው። የአይሁድ በደል ለዓለም ብዙ በረከት አስገኝቶአል፤ የእነርሱም ውድቀት ለአሕዛብ በረከት ሆኖአል፤ አይሁድ ቢድኑማ ኖሮ በረከቱ ምን ያኽል ብዙ በሆነ ነበር! አሁን እንግዲህ የምናገረው ለእናንተ ለአሕዛብ ነው፤ የአሕዛብም ሐዋርያ እንደ መሆኔ መጠን በአገልግሎቴ ክብር ይሰማኛል፤ ይህንንም ማድረጌ የሥጋ ዘመዶቼ የሆኑትን አይሁድ ለማስቀናት ነው፤ በዚህም ሁኔታ ምናልባት ከእነርሱ አንዳንዶቹን ለማዳን እችል ይሆናል በማለት ነው። እግዚአብሔር እነርሱን በጣላቸው ጊዜ ሌላው የዓለም ሕዝብ ከእግዚአብሔር ጋር ከታረቀ እግዚአብሔር እነርሱን በሚቀበላቸው ጊዜ ምን የሚሆን ይመስላችኋል? ይህማ ከሞት እንደ መነሣት ያኽል ነው! ከአንድ ዐይነት ሊጥ የመጀመሪያው ክፍል የተቀደሰ ከሆነ ሊጡ በሙሉ የተቀደሰ ይሆናል፤ እንዲሁም የአንድ ዛፍ ሥሩ የተቀደሰ ከሆነ ቅርንጫፎቹም የተቀደሱ ይሆናሉ። እንደ ጓሮ የወይራ ዛፍ ቅርንጫፎች የሆኑ አይሁድ ተቈርጠው ቢወድቁና እናንተ እንደ ዱር የወይራ ዛፍ ቅርንጫፎች የሆናችሁ አሕዛብ በቦታቸው ተተክታችሁ የእነርሱን ሀብትና በረከት ተካፋዮች ብትሆኑ፥ እናንተ አሕዛብ እንደ ቅርንጫፍ ተቈርጠው በወደቁት አይሁድ ላይ አትታበዩ፤ ብትታበዩ ግን እናንተ ቅርንጫፎች ብቻ በመሆናችሁ ሥሩ እናንተን ይሸከማችኋል እንጂ እናንተ ሥሩን የማትሸከሙ መሆናችሁን አስታውሱ። ነገር ግን “ቅርንጫፎች ተሰብረው የወደቁት እኔ በቦታቸው እንድተካ ነው” ትሉ ይሆናል። አባባላችሁስ ልክ ነው፤ ነገር ግን እነርሱ ተቈርጠው የወደቁት ባለማመናቸው ሲሆን እናንተ ጸንታችሁ የቆማችሁት በማመናችሁ ነው፤ ታዲያ፥ መፍራት እንጂ መታበይ አይገባችሁም። እግዚአብሔር በተፈጥሮ ቅርንጫፎች ለሆኑት አይሁድ ካልራራላቸው ለእናንተም አይራራላችሁም። እንግዲህ የእግዚአብሔርን ቸርነትና አስፈሪነት ተመልከቱ፤ አስፈሪነቱን የሚያሳየው በወደቁት ላይ ሲሆን ቸርነቱን የሚያሳየው ግን ለእናንተ ነው፤ ይህንንም የሚያደርገው እርሱን በማመን ጸንታችሁ ብትኖሩ ነው፤ ባትጸኑ ግን እናንተም ተቈርጣችሁ ትወድቃላችሁ። አይሁድ አለማመናቸውን ቢያስወግዱ ወደ ቀድሞው ቦታቸው ይመለሳሉ፤ እግዚአብሔር ወደ ቀድሞው ቦታቸው ሊመልሳቸው ይችላል። እናንተ አሕዛብ ግን በተፈጥሮ የዱር የወይራ ዛፍ ቅርንጫፎች ሆናችሁ ሳለ ያለ ቦታችሁ በጓሮ የወይራ ዛፍ ላይ መተከል ከቻላችሁ እነዚህ በተፈጥሮአቸው የጓሮ የወይራ ዛፍ ቅርንጫፎች የሆኑት አይሁድማ ወደ ቀድሞው ቦታቸው ተመልሰው መተከል እንዴት አይቻላቸውም!

ሮሜ 11:11-24 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)

ተመልሰው መዳን እስከማይችሉ ድረስ ተሰናከሉን? ብዬ እጠይቃለሁ፤ በጭራሽ! ነገር ግን እነርሱን ለማስቀናት፥ በእነርሱ በደል፥ መዳን ለአሕዛብ ሆነ። ነገር ግን በደላቸው ለዓለም ባለጠግነት ውድቀታቸውም ለአሕዛብ ባለጠግነት ከሆነ፥ ይልቁንስ መሙላታቸው እንዴት ይሆን? አሁን አሕዛብ ለሆናችሁ ለእናንተ እናገራለሁ፤ እኔ የአሕዛብ ሐዋርያ እንደመሆኔ አገልግሎቴን አከብራለሁ፤ ይህም ሥጋዬ የሆኑትን አስቀንቼ ምናልባት ከእነርሱ አንዳንዱን አድን እንደሆነ ነው። የእነርሱ መጣል ለዓለም እርቅን ካስገኘ፥ ተቀባይነት ማግኘታቸውማ ከሞት መነሣት ነው ከማለት በቀር ምን መሆን ይችላል? በኩራቱም ቅዱስ ከሆነ ብኮው ደግሞ ቅዱስ ነው፤ ሥሩም ቅዱስ ከሆነ ቅርንጫፎቹ ደግሞ ቅዱሳን ናቸው። ነገር ግን ከቅርንጫፎቹ አንዳንዱ ቢሰበሩ አንተም የበረሃ ወይራ የሆንህ በመካከላቸው ገብተህ ከእነርሱ ጋር የወይራ ዘይት ከሚወጣው ሥር ተካፋይ ከሆንህ፥ በቅርንጫፎች ላይ አትመካ፤ ብትመካባቸው ግን ሥሩ አንተን ይሸከምሃል እንጂ ሥሩን አንተ አትሸከመውም። እንግዲህ “እኔ እንድገባ ቅርንጫፎች ተሰበሩ፤” ትል ይሆናል። መልካም፤ እነርሱ ከአለማመን የተነሣ ተሰበሩ፤ አንተ ግን ከእምነት የተነሣ ቆመሃል። ፍራ እንጂ የትዕቢትን ነገር አታስብ። እግዚአብሔር በተፈጥሮ ቅርንጫፎች ለሆኑት ካልራራላቸው ለአንተም አይራራልህምና። እንግዲህ የእግዚአብሔርን ቸርነትና ጭከና ተመልከት፤ ጭከናው በወደቁት ላይ ነው፤ በቸርነቱ ግን ጸንተህ ብትኖር የእግዚአብሔር ቸርነት በአንተ ላይ ነው፤ ያለዚያ አንተ ደግሞ ትቆረጣለህ። እነዚያም ደግሞ በአለማመናቸው ጸንተው ባይኖሩ በዛፉ ውስጥ ይገባሉ፤ እግዚአብሔር መልሶ ሊያገባቸው ይችላልና። አንተ በተፈጥሮ የበረሃ ከነበረ የወይራ ዛፍ ተቆርጠህ እንደ አፈጣጠርህ ሳትሆን በመልካም የወይራ ዛፍ ከገባህ፥ ይልቁንስ እነዚያ በተፈጥሮአቸው ቅርንጫፎች የሆኑት በራሳቸው የወይራ ዛፍ እንዴት አይገቡም?