ወደ ሮም ሰዎች 11:11-24

ወደ ሮም ሰዎች 11:11-24 አማ05

እስቲ፥ እንደገና ልጠይቅ፤ አይሁድ የወደቁት ዳግመኛ እንደማይነሡ ሆነው ነውን? አይደለም! በአይሁድ በደል ምክንያት አሕዛብ መዳንን አገኙ፤ ይህም የሆነው አይሁድ በአሕዛብ እንዲቀኑ ለማድረግ ነው። የአይሁድ በደል ለዓለም ብዙ በረከት አስገኝቶአል፤ የእነርሱም ውድቀት ለአሕዛብ በረከት ሆኖአል፤ አይሁድ ቢድኑማ ኖሮ በረከቱ ምን ያኽል ብዙ በሆነ ነበር! አሁን እንግዲህ የምናገረው ለእናንተ ለአሕዛብ ነው፤ የአሕዛብም ሐዋርያ እንደ መሆኔ መጠን በአገልግሎቴ ክብር ይሰማኛል፤ ይህንንም ማድረጌ የሥጋ ዘመዶቼ የሆኑትን አይሁድ ለማስቀናት ነው፤ በዚህም ሁኔታ ምናልባት ከእነርሱ አንዳንዶቹን ለማዳን እችል ይሆናል በማለት ነው። እግዚአብሔር እነርሱን በጣላቸው ጊዜ ሌላው የዓለም ሕዝብ ከእግዚአብሔር ጋር ከታረቀ እግዚአብሔር እነርሱን በሚቀበላቸው ጊዜ ምን የሚሆን ይመስላችኋል? ይህማ ከሞት እንደ መነሣት ያኽል ነው! ከአንድ ዐይነት ሊጥ የመጀመሪያው ክፍል የተቀደሰ ከሆነ ሊጡ በሙሉ የተቀደሰ ይሆናል፤ እንዲሁም የአንድ ዛፍ ሥሩ የተቀደሰ ከሆነ ቅርንጫፎቹም የተቀደሱ ይሆናሉ። እንደ ጓሮ የወይራ ዛፍ ቅርንጫፎች የሆኑ አይሁድ ተቈርጠው ቢወድቁና እናንተ እንደ ዱር የወይራ ዛፍ ቅርንጫፎች የሆናችሁ አሕዛብ በቦታቸው ተተክታችሁ የእነርሱን ሀብትና በረከት ተካፋዮች ብትሆኑ፥ እናንተ አሕዛብ እንደ ቅርንጫፍ ተቈርጠው በወደቁት አይሁድ ላይ አትታበዩ፤ ብትታበዩ ግን እናንተ ቅርንጫፎች ብቻ በመሆናችሁ ሥሩ እናንተን ይሸከማችኋል እንጂ እናንተ ሥሩን የማትሸከሙ መሆናችሁን አስታውሱ። ነገር ግን “ቅርንጫፎች ተሰብረው የወደቁት እኔ በቦታቸው እንድተካ ነው” ትሉ ይሆናል። አባባላችሁስ ልክ ነው፤ ነገር ግን እነርሱ ተቈርጠው የወደቁት ባለማመናቸው ሲሆን እናንተ ጸንታችሁ የቆማችሁት በማመናችሁ ነው፤ ታዲያ፥ መፍራት እንጂ መታበይ አይገባችሁም። እግዚአብሔር በተፈጥሮ ቅርንጫፎች ለሆኑት አይሁድ ካልራራላቸው ለእናንተም አይራራላችሁም። እንግዲህ የእግዚአብሔርን ቸርነትና አስፈሪነት ተመልከቱ፤ አስፈሪነቱን የሚያሳየው በወደቁት ላይ ሲሆን ቸርነቱን የሚያሳየው ግን ለእናንተ ነው፤ ይህንንም የሚያደርገው እርሱን በማመን ጸንታችሁ ብትኖሩ ነው፤ ባትጸኑ ግን እናንተም ተቈርጣችሁ ትወድቃላችሁ። አይሁድ አለማመናቸውን ቢያስወግዱ ወደ ቀድሞው ቦታቸው ይመለሳሉ፤ እግዚአብሔር ወደ ቀድሞው ቦታቸው ሊመልሳቸው ይችላል። እናንተ አሕዛብ ግን በተፈጥሮ የዱር የወይራ ዛፍ ቅርንጫፎች ሆናችሁ ሳለ ያለ ቦታችሁ በጓሮ የወይራ ዛፍ ላይ መተከል ከቻላችሁ እነዚህ በተፈጥሮአቸው የጓሮ የወይራ ዛፍ ቅርንጫፎች የሆኑት አይሁድማ ወደ ቀድሞው ቦታቸው ተመልሰው መተከል እንዴት አይቻላቸውም!