ወደ ተራራም ወጣ፥ ራሱም የወደዳቸውን ወደ እርሱ ጠራ፥ ወደ እርሱም ሄዱ። ከእርሱም ጋር እንዲኖሩና ለመስበክ እንዲልካቸው፥ ድውዮችንም ሊፈውሱ አጋንንትንም ሊያወጡ ሥልጣን ይሆንላቸው ዘንድ አሥራ ሁለት አደረገ፤ ስምዖንንም ጴጥሮስ ብሎ ሰየመው፤ የዘብዴዎስንም ልጅ ያዕቆብን የያዕቆብንም ወንድም ዮሐንስን ቦአኔርጌስ ብሎ ሰየማቸው፥ የነጎድጓድ ልጆች ማለት ነው፤ እንድርያስንም ፊልጶስንም በርተሎሜውስንም ማቴዎስንም ቶማስንም የእልፍዮስን ልጅ ያዕቆብንም ታዴዎስንም ቀነናዊውንም ስምዖንን፥ አሳልፎ የሰጠውንም የአስቆሮቱን ይሁዳን። ወደ ቤትም መጡ፤ እንጀራም መብላት ስንኳ እስኪሳናቸው ድረስ እንደ ገና ብዙ ሰዎች ተሰበሰቡ። ዘመዶቹም ሰምተው፦ አበደ ብለዋልና ሊይዙት ወጡ። ከኢየሩሳሌም የወረዱ ጻፎችም፦ ብዔል ዜቡል አለበት፤ ደግሞ፦ በአጋንንት አለቃ አጋንንትን ያወጣል ብለው ተናገሩ። እነርሱንም ወደ እርሱ ጠርቶ በምሳሌ አላቸው፦ ሰይጣን ሰይጣንን ሊያወጣው እንዴት ይችላል? መንግሥትም እርስ በርስዋ ከተለያየች ያች መንግሥት ልትቆም አትችልም፤ ቤትም እርስ በርሱ ከተለያየ ያ ቤት ሊቆም አይችልም። ሰይጣንም ራሱን ተቃውሞ ከተለያየ፥ መጨረሻ ይሆንበታል እንጂ ሊቆም አይችልም። ነገር ግን አስቀድሞ ኃይለኛውን ሳያስር ወደ ኃይለኛው ቤት ገብቶ ዕቃውን ሊበዘብዝ የሚችል የለም ከዚያም ወዲያ ቤቱን ይበዘብዛል። እውነት እላችኋለሁ፥ ለሰው ልጆች ኃጢአት ሁሉ የሚሳደቡትም ስድብ ሁሉ ይሰረይላቸዋል፤ በመንፈስ ቅዱስ ላይ የሚሳደብ ሁሉ ግን የዘላለም ኃጢአት ዕዳ ይሆንበታል እንጂ ለዘላለም አይሰረይለትም። ርኵስ መንፈስ አለበት ይሉ ነበርና። እናቱና ወንድሞቹም መጡ በውጭም ቆመው ወደ እርሱ ልከው አስጠሩት። ብዙ ሰዎችም በዙሪያው ተቀምጠው ነበሩና፦ እነሆ፥ እናትህ ወንድሞችህም በውጭ ቆመው ይፈልጉሃል አሉት። መልሶም፦ እናቴ ማን ናት? ወንድሞቼስ እነ ማን ናቸው? አላቸው። በዙሪያው ተቀምጠው ወደ ነበሩትም ተመለከተና፦ እነሆ እናቴ ወንድሞቼም። የእግዚአብሔርን ፈቃድ የሚያደርግ ሁሉ፥ እርሱ ወንድሜ ነው እኅቴም እናቴም አለ።
የማርቆስ ወንጌል 3 ያንብቡ
Share
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: የማርቆስ ወንጌል 3:13-35
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
Home
Bible
Plans
Videos