የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

ማርቆስ 3:13-35

ማርቆስ 3:13-35 NASV

ኢየሱስም ወደ ተራራ ወጥቶ የሚፈልጋቸውን ወደ እርሱ እንዲመጡ ጠራቸው፤ እነርሱም ወደ እርሱ መጡ። ከርሱ ጋራ እንዲሆኑ፣ ለስብከትም እንዲልካቸው ዐሥራ ሁለቱን ሾማቸው፤ ሐዋርያትም ብሎ ጠራቸው፤ አጋንንትን እንዲያስወጡም ሥልጣን ሰጣቸው። የሾማቸውም ዐሥራ ሁለቱ እነዚህ ናቸው፤ ጴጥሮስ ብሎ የጠራው ስምዖን፣ ቦአኔርጌስ ይኸውም፣ “የነጐድጓድ ልጆች” ብሎ የጠራው የዘብዴዎስ ልጅ ያዕቆብና ወንድሙ ዮሐንስ፤ እንድርያስ፣ ፊልጶስ፣ በርተሎሜዎስ፣ ማቴዎስ፣ ቶማስ፣ የእልፍዮስ ልጅ ያዕቆብ፣ ታዴዎስ፣ ቀነናዊው ስምዖን፣ እንዲሁም አሳልፎ የሰጠው የአስቆሮቱ ይሁዳ። ከዚያም ኢየሱስ ወደ አንድ ቤት ገባ፤ እርሱና ደቀ መዛሙርቱ ምግብ መብላት እንኳ እስኪሳናቸው ድረስ ሕዝቡ እንደ ገና በብዛት ተሰበሰበ። ሁኔታውን የሰሙ ዘመዶቹም፣ “አእምሮውን ስቷል” በማለት ይዘውት ለመሄድ ወዳለበት መጡ። ከኢየሩሳሌም የመጡ ጸሐፍትም፣ “ብዔልዜቡል ዐድሮበታል! አጋንንትን የሚያወጣው በአጋንንት አለቃ ነው” አሉ። እርሱም ጠራቸውና በምሳሌ እንዲህ አላቸው፤ “ሰይጣን ሰይጣንን እንዴት ሊያስወጣ ይችላል? እርስ በርሱ የሚከፋፈል መንግሥት ሊጸና አይችልም፤ ቤትም እርስ በርሱ ከተከፋፈለ ሊቆም አይችልም። እንደዚሁም ሰይጣን እርስ በርሱ የሚፃረርና የሚከፋፈል ከሆነ ሊቆም አይችልም፤ ያበቃለታል። ከዚህም የተነሣ አንድ ሰው አስቀድሞ ኀይለኛውን ሰው ሳያስር ወደ ኀይለኛው ሰው ቤት ሊገባና ንብረቱን ሊዘርፍ አይችልም፤ ቤቱን መዝረፍ የሚቻለው ኀይለኛውን ሰው ሲያስር ብቻ ነው። እውነት እላችኋለሁ፤ የሰው ልጆች ኀጢአትና የሚሳደቡት ስድብ ሁሉ ይሰረይላቸዋል፤ ነገር ግን በመንፈስ ቅዱስ ላይ የስድብ ቃል የሚናገር ሁሉ የዘላለም ኀጢአት ዕዳ ይሆንበታል እንጂ ለዘላለም አይሰረይለትም።” ይህንም ያለው፣ “ርኩስ መንፈስ አለበት” ስላሉት ነበር። ከዚህ በኋላ እናቱና ወንድሞቹ መጡ፤ በውጭ ቆመውም ሰው ልከውበት አስጠሩት። በዙሪያው የተቀመጡ ብዙ ሰዎችም፣ “እነሆ፤ እናትህና ወንድሞችህ ውጭ ይፈልጉሃል” አሉት። እርሱም መልሶ፣ “እናቴ ማን ናት፣ ወንድሞቼስ እነማን ናቸው?” አላቸው። በዙሪያው ወደ ተቀመጡትም በመመልከት፣ እንዲህ አለ፤ “እናቴና ወንድሞቼ እነዚህ ናቸው! የእግዚአብሔርን ፈቃድ የሚያደርግ ሁሉ እርሱ ወንድሜ፣ እኅቴ፣ እናቴም ነውና።”

ተዛማጅ ቪዲዮዎች