ኢየሱስ ወደ ተራራ በወጣ ጊዜ እነዚያን የፈለጋቸውን ወደ እርሱ ጠራ፤ እነርሱም ወደ እርሱ ቀረቡ። ከእርሱ ጋር እንዲሆኑ፥ ለማስተማርም እንዲልካቸው ዐሥራ ሁለቱን መርጦ “ሐዋርያት” ብሎ ሰየማቸው። አጋንንትን እንዲያስወጡም ሥልጣን ሰጣቸው። የተመረጡትም ዐሥራ ሁለቱ ሐዋርያት እነዚህ ናቸው፦ ጴጥሮስ ብሎ የሠየመው ስምዖን፥ ቦአኔርጌስ ወይም የነጐድጓድ ልጆች ብሎ የሠየማቸው፥ የዘብዴዎስ ልጆች ያዕቆብና ዮሐንስ፥ እንድርያስ፥ ፊልጶስ፥ በርቶሎሜዎስ፥ ማቴዎስ፥ ቶማስ፥ የእልፍዮስ ልጅ ያዕቆብ፥ ታዴዎስ፥ ተቀናቃኙ ስምዖን፥ ኢየሱስን አሳልፎ የሰጠውም አስቆሮታዊው ይሁዳ። ከዚህም በኋላ ኢየሱስ ወደ ቤት ገባ። ኢየሱስና ደቀ መዛሙርቱ ምግብ መብላት እንኳ እስኪያቅታቸው ድረስ እንደገና ብዙ ሰዎች ተሰበሰቡ። “ኢየሱስ አብዶአል” ሲባል በመስማታቸው ዘመዶቹ ሊይዙት ወደ እርሱ መጡ። ከኢየሩሳሌም የወረዱ የሕግ መምህራን፥ “እርሱ ብዔልዜቡል አለበት! አጋንንትንም የሚያወጣው በዚሁ የአጋንንት አለቃ በሆነው በብዔልዜቡል አማካይነት ነው!” እያሉ አወሩ። ኢየሱስም እነርሱን ወደ እርሱ ጠርቶ በምሳሌ እንዲህ አላቸው፦ “ሰይጣን እንዴት ሰይጣንን ሊያስወጣ ይችላል? አንድ መንግሥት ተከፋፍሎ እርስ በርሱ የሚጋጭ ከሆነ ያ መንግሥት ጸንቶ መቆም አይችልም። እንዲሁም አንድ ቤተሰብ እርስ በርሱ ከተለያየ ጸንቶ መኖር አይችልም፤ ስለዚህ ሰይጣን እርስ በርሱ ከተለያየ ይጠፋል እንጂ መኖር አይችልም። “እንዲሁም ወደ አንድ ኀይለኛ ሰው ቤት ገብቶ አስቀድሞ ኀይለኛውን ሰው ሳያስር ንብረቱን መዝረፍ የሚችል የለም። “በእውነት እላችኋለሁ፤ ሰዎች የሚሠሩት ኃጢአትና የሚናገሩት ስድብ ሁሉ ይቅር ይባልላቸዋል። ነገር ግን በመንፈስ ቅዱስ ላይ የስድብ ቃል የሚናገር ሁሉ የዘለዓለም ዕዳ ይሆንበታል እንጂ ከቶ ኃጢአቱ ይቅር አይባልለትም።” ኢየሱስ ይህን የተናገረው፥ “ርኩስ መንፈስ አለበት፤” በማለታቸው ነበር። የኢየሱስ እናትና ወንድሞቹ ወደ እርሱ መጡ፤ በውጪም ቆመው ወደ እርሱ ሰው ላኩና አስጠሩት። በዙሪያውም ተቀምጠው የነበሩ ሰዎች፥ “እነሆ! እናትህና ወንድሞችህ በውጪ ቆመው ይፈልጉሃል” ብለው ነገሩት። እርሱም “እናቴ ማን ናት? ወንድሞቼስ እነማን ናቸው?” ሲል መለሰ። በዙሪያው ተቀምጠው ወደነበሩት እየተመለከተ፥ “እነሆ! እናቴና ወንድሞቼ እነዚህ ናቸው! የእግዚአብሔርን ፈቃድ የሚፈጽም ሁሉ፥ እርሱ ወንድሜም፥ እኅቴም እናቴም ነው።” አለ።
የማርቆስ ወንጌል 3 ያንብቡ
Share
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: የማርቆስ ወንጌል 3:13-35
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
Home
Bible
Plans
Videos