ሲነጋም የካህናት አለቆችና የሕዝቡ ሽማግሎች ሁሉ ሊገድሉት በኢየሱስ ላይ ተማከሩ፤ አስረውም ወሰዱት፥ ለገዢው ለጴንጤናዊው ጲላጦስም አሳልፈው ሰጡት። በዚያን ጊዜ አሳልፎ የሰጠው ይሁዳ እንደ ተፈረደበት አይቶ ተጸጸተ፥ ሠላሳውንም ብር ለካህናት አለቆችና ለሽማግሎች መልሶ፦ ንጹሕ ደም አሳልፌ በመስጠቴ በድያለሁ አለ። እነርሱ ግን፦ እኛስ ምን አግዶን? አንተው ተጠንቀቅ አሉ። ብሩንም በቤተ መቅደስ ጥሎ ሄደና ታንቆ ሞተ። የካህናት አለቆችም ብሩን አንሥተው፦ የደም ዋጋ ነውና ወደ መባ ልንጨምረው አልተፈቀደም አሉ። ተማክረውም የሸክላ ሠሪውን መሬት ለእንግዶች መቃብር ገዙበት። ስለዚህ ያ መሬት እስከ ዛሬ ድረስ የደም መሬት ተባለ። በዚያን ጊዜ በነቢዩ በኤርምያስ የተባለው፦ ከእስራኤል ልጆችም አንዳንዶቹ የገመቱትን፥ የተገመተውን ዋጋ ሠላሳ ብር ያዙ፥ ጌታም እንዳዘዘኝ ስለ ሸክላ ሠሪ መሬት ሰጡት። የሚል ተፈጸመ። ኢየሱስም በገዢው ፊት ቆመ፤ ገዢውም፦ የአይሁድ ንጉሥ አንተ ነህን? ብሎ ጠየቀው፤ ኢየሱስም፦ አንተ አልህ አለው። የካህናት አለቆችም ሽማግሎችም ሲከሱት ምንም አልመለሰም። በዚያን ጊዜ ጲላጦስ፦ ስንት ያህል እንዲመሰክሩብህ አትሰማምን? አለው። ገዢውም እጅግ እስኪደነቅ ድረስ አንዲት ቃል ስንኳ አልመለሰለትም። በዚያም በዓል ሕዝቡ የወደዱትን አንድ እስረኛ ሊፈታላቸው ለገዢው ልማድ ነበረው። በዚያን ጊዜም በርባን የሚባል በጣም የታወቀ እስረኛ ነበራቸው። እንግዲህ እነርሱ ተሰብስበው ሳሉ ጲላጦስ፦ በርባንን ወይስ ክርስቶስ የተባለውን ኢየሱስን ማንኛውን ልፈታላችሁ ትወዳላችሁ? አላቸው፤ በቅንዓት አሳልፈው እንደ ሰጡት ያውቅ ነበርና። እርሱም በፍርድ ወንበር ተቀምጦ ሳለ ሚስቱ፦ ስለ እርሱ ዛሬ በሕልም እጅግ መከራ ተቀብያለሁና በዚያ ጻድቅ ሰው ምንም አታድርግ ብላ ላከችበት። የካህናት አለቆችና ሽማግሎች ግን በርባንን እንዲለምኑ ኢየሱስን ግን እንዲያጠፉ ሕዝቡን አባበሉ። ገዢውም መልሶ፦ ከሁለቱ ማንኛውን ልፈታላችሁ ትወዳላችሁ? አላቸው፤ እነርሱም፦ በርባንን አሉ። ጲላጦስ፦ ክርስቶስ የተባለውን ኢየሱስን እንግዲህ ምን ላድርገው? አላቸው፤ ሁሉም፦ ይሰቀል አሉ። ገዢውም፦ ምን ነው? ያደረገው ክፋት ምንድር ነው? አለ፤ እነርሱ ግን፦ ይሰቀል እያሉ ጩኸት አበዙ። ጲላጦስም ሁከት እንዲጀመር እንጂ አንዳች እንዳይረባ ባየ ጊዜ፥ ውኃ አንሥቶ፦ እኔ ከዚህ ጻድቅ ሰው ደም ንጹሕ ነኝ፤ እናንተ ተጠንቀቁ ሲል በሕዝቡ ፊት እጁን ታጠበ። ሕዝቡም ሁሉ መልሰው፦ ደሙ በእኛና በልጆቻችን ላይ ይሁን አሉ። በዚያን ጊዜ በርባንን ፈታላቸው፥ ኢየሱስን ግን ገርፎ ሊሰቀል አሳልፎ ሰጠ። በዚያን ጊዜ የገዢው ወታደሮች ኢየሱስን ወደ ገዢው ግቢ ውስጥ ወሰዱት ጭፍራውንም ሁሉ ወደ እርሱ አከማቹ። ልብሱንም ገፈው ቀይ ልብስ አለበሱት፥ ከእሾህም አክሊል ጎንጉነው በራሱ ላይ፥ በቀኝ እጁም መቃ አኖሩ፥ በፊቱም ተንበርክከው፦ የአይሁድ ንጉሥ ሆይ፥ ሰላም ለአንተ ይሁን እያሉ ዘበቱበት፤ ተፉበትም መቃውንም ይዘው ራሱን መቱት። ከዘበቱበትም በኋላ ቀዩን ልብስ ገፈፉት፥ ልብሱንም አለበሱት ሊሰቅሉትም ወሰዱት።
የማቴዎስ ወንጌል 27 ያንብቡ
ያጋሩ
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: የማቴዎስ ወንጌል 27:1-31
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
ቤት
መጽሐፍ ቅዱስ
እቅዶች
ቪዲዮዎች