ማቴዎስ 27:1-31

ማቴዎስ 27:1-31 NASV

ጧት በማለዳ ላይ፣ የካህናት አለቆችና የሕዝብ ሽማግሌዎች ሁሉ ኢየሱስ ስለሚገደልበት ሁኔታ ተመካከሩ፤ ካሰሩትም በኋላ ወስደው ለገዢው ለጲላጦስ አሳልፈው ሰጡት። አሳልፎ የሰጠው ይሁዳም ኢየሱስ እንደ ተፈረደበት ባየ ጊዜ ተጸጸተ፤ የወሰደውን ሠላሳ ጥሬ ብር ለካህናት አለቆችና ለሕዝቡ ሽማግሌዎች መልሶ በመስጠት፣ “ንጹሕ ደም አሳልፌ በመስጠቴ በድያለሁ” አለ። እነርሱም፣ “ታዲያ እኛ ምን አገባን፤ የራስህ ጕዳይ ነው!” አሉት። ስለዚህ ይሁዳ ብሩን በቤተ መቅደስ ውስጥ ወርውሮ ወጣ፤ ሄዶም ራሱን ሰቅሎ ሞተ። የካህናት አለቆች ብሩን አንሥተው፣ “የደም ዋጋ ስለ ሆነ ወደ መባ ልንጨምረው አይፈቀድም” አሉ፤ ተመካክረውም ለእንግዶች የመቃብር ስፍራ እንዲሆን በገንዘቡ የሸክላ ሠሪውን ቦታ ገዙበት። ስለዚህም ያ ቦታ እስከ ዛሬ ድረስ “የደም መሬት” ተብሎ ይጠራል። በዚህም በነቢዩ ኤርምያስ እንዲህ ተብሎ የተነገረው ተፈጸመ፤ “ለርሱ ዋጋ ይሆን ዘንድ የእስራኤል ልጆች የገመቱትን ሠላሳ ጥሬ ብር ተቀበሉ፤ ጌታም ባዘዘኝ መሠረት ለሸክላ ሠሪው ቦታ ከፈሉ።” በዚህ ጊዜ ኢየሱስ አገረ ገዥው ፊት ቀረበ፤ አገረ ገዥውም፣ “አንተ የአይሁድ ንጉሥ ነህን?” በማለት ጠየቀው። ኢየሱስም፣ “አንተው እንዳልኸው ነው” ሲል መለሰለት። የካህናት አለቆችና ሽማግሌዎች ሲከስሱት ግን ምንም መልስ አልሰጠም። በዚህ ጊዜ ጲላጦስ፣ “ስንት ነገር አቅርበው እንደሚከስሱህ አትሰማምን?” አለው። እርሱ ግን አገረ ገዥው እስኪገረም ድረስ ለቀረበበት ክስ አንዲት ቃል እንኳ አልመለሰም። አገረ ገዥው ሕዝቡ በበዓሉ እንዲፈታላቸው የሚጠይቁትን አንድ እስረኛ የመፍታት ልማድ ነበረው። በዚያ ጊዜ በዐመፅ የታወቀ በርባን የሚባል እስረኛ ነበር። ሕዝቡ እንደ ተሰበሰቡ ጲላጦስ፣ “ከበርባንና ክርስቶስ ከሚባለው ከኢየሱስ፣ ማንን እንድፈታላችሁ ትፈልጋላችሁ?” አላቸው፤ ጲላጦስም በቅናት አሳልፈው እንደ ሰጡት ያውቅ ነበርና። በፍርድ ወንበር ላይ ተቀምጦ ሳለ ሚስቱ፣ “በርሱ ምክንያት ዛሬ በሕልም ብዙ ስለ ተሠቃየሁ፣ በዚያ ንጹሕ ሰው ላይ ምንም ነገር እንዳታደርግ” የሚል መልእክት ላከችበት። ነገር ግን የካህናት አለቆችና ሽማግሌዎች በርባን እንዲፈታላቸው ኢየሱስ ግን እንዲገደል ይለምኑ ዘንድ ሕዝቡን ያግባቡ ነበር። አገረ ገዥውም፣ “ከሁለቱ ማንን እንድፈታላችሁ ትፈልጋላችሁ?” በማለት ጠየቀ። እነርሱም፤ “በርባንን” በማለት መለሱ። ጲላጦስም፣ “ታዲያ ክርስቶስ የተባለውን ኢየሱስንስ ምን ላድርገው?” አላቸው። ሁሉም፣ “ይሰቀል!” አሉ። ጲላጦስም፣ “ለምን? ምን ክፉ ነገር አድርጓል?” በማለት ጠየቃቸው። እነርሱ ግን አብዝተው እየጮኹ፣ “ይሰቀል!” አሉ። ጲላጦስ ሁኔታው ሽብር ከማስነሣት በቀር ምንም ፋይዳ የሌለው መሆኑን ተመልክቶ፣ “እኔ ከዚህ ሰው ደም ንጹሕ ነኝ፤ ከእንግዲህ ኀላፊነቱ የራሳችሁ ነው” በማለት ውሃ አስመጥቶ በሕዝቡ ፊት እጆቹን ታጠበ። ሕዝቡም በሙሉ፣ “ደሙ በእኛና በልጆቻችን ላይ ይሁን!” ብለው መለሱ። በዚህ ጊዜ በርባንን ፈታላቸው፤ ኢየሱስን ግን ካስገረፈው በኋላ እንዲሰቀል አሳልፎ ሰጠው። ከዚያም የአገረ ገዥው ወታደሮች ኢየሱስን ወደ ገዥው ግቢ ወሰዱት፤ ሰራዊቱንም ሁሉ በዙሪያው አሰባሰቡ። ልብሱን ገፍፈው ቀይ ልብስ አጠለቁለት፤ እሾኽ ጐንጕነው አክሊል በመሥራት ራሱ ላይ ደፉበት፤ የሸንበቆ በትር በቀኝ እጁ በማስያዝ በፊቱ ተንበርክከው፣ “የአይሁድ ንጉሥ ሆይ፤ ሰላም ለአንተ ይሁን” በማለት አሾፉበት፤ ተፉበትም፤ የሸንበቆ በትሩን ከእጁ ወስደው ራሱን መቱት፤ ካሾፉበት በኋላም ቀዩን ልብስ ገፍፈው የራሱን ልብስ አለበሱት፤ ሊሰቅሉትም ይዘውት ሄዱ።

ተዛማጅ ቪዲዮዎች