የማቴዎስ ወንጌል 27:1-31

የማቴዎስ ወንጌል 27:1-31 አማ05

ጠዋት በማለዳ የካህናት አለቆችና የሕዝብ ሽማግሌዎች ሁሉ በኢየሱስ ላይ የሞት ፍርድ ለማስፈረድ ተማከሩ። ከዚህ በኋላ ኢየሱስን አስረው ወሰዱና ለገዥው ለጲላጦስ አሳልፈው ሰጡት። ኢየሱስ እንደተፈረደበት ባየ ጊዜ አሳልፎ የሰጠው ይሁዳ ተጸጸተ፤ ሠላሳውንም ጥሬ ብር ለካህናት አለቆችና ሽማግሌዎች እንዲህ በማለት መልሶ ሰጣቸው፤ “ንጹሑን ሰው ለሞት አሳልፌ በመስጠቴ በድዬአለሁ።” እነርሱ ግን “ታዲያ፥ እኛ ምን ቸገረን! የራስህ ጉዳይ ነው!” አሉት። እርሱም ሠላሳውን ጥሬ ብር በቤተ መቅደስ ውስጥ በትኖ፥ ትቶአቸው ወጣ፤ ሄዶም ታንቆ ሞተ። የካህናት አለቆች ሠላሳውን ጥሬ ብር አንሥተው “ይህ ገንዘብ የደም ዋጋ ስለ ሆነ ከቤተ መቅደስ መባ ጋር ልንቀላቅለው አይፈቀድም” አሉ። ስለዚህ ከተመካከሩ በኋላ ለእንግዶች የመቃብር ቦታ እንዲሆን የሸክላ ሠሪውን መሬት ገዙበት። በዚህ ምክንያት ያ መሬት እስከ ዛሬ ድረስ “የደም መሬት” እየተባለ ይጠራል። በዚህ ሁኔታ “የእስራኤል ልጆች የገመቱትን ለእርሱ ዋጋ የሚሆን ሠላሳ ጥሬ ብር ወሰዱ፤ ጌታም እንዳዘዘኝ ስለ ሸክላ ሠሪው መሬት ከፈሉት” ተብሎ በነቢዩ ዘካርያስ የተነገረው ትንቢት ተፈጸመ። በዚያን ጊዜ ኢየሱስ ወደ ገዢው ወደ ጲላጦስ ፊት ቀረበ፤ ገዢውም “አንተ የአይሁድ ንጉሥ ነህን?” ሲል ጠየቀው፤ ኢየሱስም “አንተ እንዳልከው ነው” ሲል መለሰ። ነገር ግን የካህናት አለቆችና ሽማግሌዎች ሲወነጅሉት ምንም መልስ አልሰጠም። ከዚህ በኋላ ጲላጦስ “በስንት ነገር ሲወነጅሉህ አትሰማምን?” አለው። ኢየሱስ ግን ገዢው እስኪደነቅ ድረስ ለአንዲት ክስ እንኳ ቃል አልመለሰለትም። ገዢው በየዓመቱ በአይሁድ ፋሲካ በዓል ጊዜ እንዲፈታላቸው ሕዝቡ የጠየቁትን አንድ እስረኛ ፈቶ መልቀቅ አስለምዶ ነበር። በዚያን ጊዜ “በርባን” የተባለ በዓመፀኛነቱ የታወቀ እስረኛ ነበረ። ስለዚህ ሰዎቹ በተሰበሰቡ ጊዜ ጲላጦስ፥ “ማንን እንድፈታላችሁ ትፈልጋላችሁ? በርባንን ነውን ወይስ መሲሕ የተባለውን ኢየሱስን?” ሲል ጠየቃቸው። ይህን ያለበት ምክንያት ኢየሱስን በቅናት አሳልፈው እንደ ሰጡት ያውቅ ስለ ነበር ነው። ከዚህም በላይ ጲላጦስ በፍርድ ወንበር ተቀምጦ ሳለ ሚስቱ፦ “በእርሱ ምክንያት ዛሬ ሌሊት በሕልም ብዙ ተሠቃይቻለሁና በዚያ በንጹሕ ሰው ላይ ምንም እንዳታደርግ” ስትል ላከችበት። በዚያን ጊዜ የካህናት አለቆችና ሽማግሌዎች “በርባን ይለቀቅ! ኢየሱስ ይገደል!” ብለው እንዲጠይቁ ሕዝቡን አግባቡ። ገዢውም “ከሁለቱ የትኛውን እንድፈታላችሁ ትፈልጋላችሁ?” ሲል ሕዝቡን እንደገና ጠየቀ። እነርሱም “በርባንን እንድትፈታልን እንፈልጋለን” ሲሉ መለሱ። ጲላጦስም “ታዲያ፥ መሲሕ የተባለውን ኢየሱስን ምን ላድርገው?” አላቸው። ሁሉም “ይሰቀል!” ሲሉ መለሱ። ገዢውም ለምን? “እርሱ ያደረገው በደል ምንድን ነው?” አላቸው። እነርሱ ግን “ይሰቀል!” እያሉ አብዝተው ጮኹ። ስለዚህ ጲላጦስ ይህ ነገር ሁከት እንደሚያስነሣ እንጂ ሌላ ምንም እንደማይጠቅም ባየ ጊዜ ውሃ አስመጥቶ “እኔ ለዚህ ሰው ሞት ኀላፊ አይደለሁም፤ ኀላፊነቱ የእናንተ ነው!” ብሎ በሕዝቡ ፊት እጁን ታጠበ። ሕዝቡም ሁሉ “በእርሱ ሞት ምክንያት የሚመጣው ቅጣት በእኛና በልጆቻችን ላይ ይሁን” አሉ። በዚያን ጊዜ ጲላጦስ በርባንን ፈቶ ለቀቀላቸው፤ ኢየሱስን ግን ካስገረፈው በኋላ እንዲሰቀል አሳልፎ ሰጣቸው። በዚያን ጊዜ የገዢው ወታደሮች ኢየሱስን ወደ ገዢው ግቢ ወሰዱት፤ ወታደሮቹንም ሁሉ በኢየሱስ ዙሪያ ሰበሰቡ። ልብሱንም ገፈው ቀይ ልብስ አለበሱት። የእሾኽ አክሊልም ጐንጒነው በራሱ ላይ ደፉበት፤ በቀኝ እጁም የመቃ ዘንግ አስያዙት፤ በፊቱም እየተንበረከኩ “የአይሁድ ንጉሥ ሆይ! ሰላም ለአንተ ይሁን!” እያሉ ያፌዙበት ነበር፤ ምራቃቸውንም ይተፉበት ነበር፤ ዘንጉንም ከእጁ ወስደው ራስ ራሱን ይመቱት ነበር። ካፌዙበት በኋላ ቀዩን ልብስ አውልቀው የራሱን ልብስ አለበሱት፤ ሊሰቅሉትም ይዘውት ሄዱ።

ተዛማጅ ቪዲዮዎች