ኢየሱስም ከመቅደስ ወጥቶ ሄደ፥ ደቀ መዛሙርቱም የመቅደሱን ግንቦች ሊያሳዩት ቀረቡ። እርሱ ግን መልሶ፦ ይህን ሁሉ ታያላችሁን? እውነት እላችኋለሁ፥ ድንጋይ በድንጋይ ላይ ሳይፈርስ በዚህ አይቀርም አላቸው። እርሱም በደብረ ዘይት ተቀምጦ ሳለ፥ ደቀ መዛሙርቱ ለብቻቸው ወደ እርሱ ቀርበው፦ ንገረን፥ ይህ መቼ ይሆናል? የመምጣትህና የዓለም መጨረሻ ምልክቱስ ምንድር ነው? አሉት። ኢየሱስም መልሶ እንዲህ አላቸው፦ ማንም እንዳያስታችሁ ተጠንቀቁ። ብዙዎች፦ እኔ ክርስቶስ ነኝ እያሉ በስሜ ይመጣሉና፤ ብዙዎችንም ያስታሉ። ጦርንም የጦርንም ወሬ ትሰሙ ዘንድ አላችሁ፤ ይህ ሊሆን ግድ ነውና ተጠበቁ፥ አትደንግጡ፤ ዳሩ ግን መጨረሻው ገና ነው። ሕዝብ በሕዝብ ላይ መንግሥትም በመንግሥት ላይ ይነሣልና፥ ራብም ቸነፈርም የምድርም መናወጥ በልዩ ልዩ ስፍራ ይሆናል፤ እነዚህም ሁሉ የምጥ ጣር መጀመሪያ ናቸው። በዚያን ጊዜ ለመከራ አሳልፈው ይሰጡአችኋል ይገድሉአችሁማል፥ ስለ ስሜም በአሕዛብ ሁሉ የተጠላችሁ ትሆናላችሁ። በዚያን ጊዜም ብዙዎች ይሰናከላሉ እርስ በርሳቸውም አሳልፈው ይሰጣጣሉ እርስ በርሳቸውም ይጣላሉ፤ ብዙ ሐሰተኞች ነቢያትም ይነሣሉ ብዙዎችንም ያስታሉ፤ ከዓመፃም ብዛት የተነሣ የብዙ ሰዎች ፍቅር ትቀዘቅዛለች። እስከ መጨረሻ የሚጸና ግን እርሱ ይድናል። ለአሕዛብም ሁሉ ምስክር እንዲሆን ይህ የመንግሥት ወንጌል በዓለም ሁሉ ይሰበካል፥ በዚያን ጊዜም መጨረሻው ይመጣል። እንግዲህ በነቢዩ በዳንኤል የተባለውን የጥፋትን ርኩሰት በተቀደሰችው ስፍራ ቆሞ ስታዩ፥ አንባቢው ያስተውል፥ በዚያን ጊዜ በይሁዳ ያሉት ወደ ተራራዎች ይሽሹ፥ በሰገነትም ያለ በቤቱ ያለውን ሊወስድ አይውረድ፥ በእርሻም ያለ ልብሱን ይወስድ ዘንድ ወደ ኋላው አይመለስ። በዚያችም ወራት ለርጉዞችና ለሚያጠቡ ወዮላቸው። ነገር ግን ሽሽታችሁ በክረምት ወይም በሰንበት እንዳይሆን ጸልዩ፤ በዚያን ጊዜ ከዓለም መጀመሪያ ጀምሮ እስከ ዛሬ ድረስ ያልሆነ እንግዲህም ከቶ የማይሆን ታላቅ መከራ ይሆናልና። እነዚያ ቀኖችስ ባያጥሩ ሥጋ የለበሰ ሁሉ ባልዳነም ነበር፤ ነገር ግን እነዚያ ቀኖች ስለ ተመረጡት ሰዎች ያጥራሉ። በዚያን ጊዜ ማንም፦ እነሆ፥ ክርስቶስ ከዚህ አለ ወይም፦ ከዚያ አለ ቢላችሁ አትመኑ፤ ሐሰተኞች ክርስቶሶችና ሐሰተኞች ነቢያት ይነሣሉና፥ ቢቻላቸውስ የተመረጡትን እንኳ እስኪያስቱ ድረስ ታላላቅ ምልክትና ድንቅ ያሳያሉ። እነሆ፥ አስቀድሜ ነገርኋችሁ። እንግዲህ፦ እነሆ፥ በበረሀ ነው ቢሉአችሁ፥ አትውጡ፤ እነሆ፥ በእልፍኝ ነው ቢሉአችሁ፥ አትመኑ፤ መብረቅ ከምሥራቅ ወጥቶ እስከ ምዕራብ እንደሚታይ፥ የሰው ልጅ መምጣት እንዲሁ ይሆናልና፤ በድን ወዳለበት በዚያ አሞራዎች ይሰበሰባሉ። ከዚያች ወራትም መከራ በኋላ ወዲያው ፀሐይ ይጨልማል፥ ጨረቃም ብርሃንዋን አትሰጥም፥ ከዋክብትም ከሰማይ ይወድቃሉ፥ የሰማያትም ኃይላት ይናወጣሉ። በዚያን ጊዜም የሰው ልጅ ምልክት በሰማይ ይታያል፥ በዚያን ጊዜም የምድር ወገኖች ሁሉ ዋይ ዋይ ይላሉ፥ የሰው ልጅንም በኃይልና በብዙ ክብር በሰማይ ደመና ሲመጣ ያዩታል፤
የማቴዎስ ወንጌል 24 ያንብቡ
ያጋሩ
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: የማቴዎስ ወንጌል 24:1-30
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
ቤት
መጽሐፍ ቅዱስ
እቅዶች
ቪዲዮዎች