ኢየሱስ ከቤተ መቅደስ ወጥቶ ሲሄድ ደቀ መዛሙርቱ የቤተ መቅደሱን ሕንጻ ሊያሳዩት ወደ እርሱ ቀረቡ። እርሱ ግን “ይህን ሁሉ ታያላችሁን? በእውነት እላችኋለሁ፤ አንዳችም ድንጋይ በድንጋይ ላይ ተነባብሮ ሳይፈርስ የሚቀር የለም” አላቸው። ኢየሱስ በደብረ ዘይት ተራራ ላይ ተቀምጦ ሳለ ደቀ መዛሙርቱ ብቻቸውን ወደ እርሱ ቀርበው፦ “ይህ ሁሉ ነገር የሚሆነው መቼ ነው? የመምጫህና የዘመኑ መጨረሻ ምልክትስ ምንድን ነው?” ሲሉ ጠየቁት። ኢየሱስ እንዲህ ሲል መለሰላቸው፦ “ማንም ሰው እንዳያሳስታችሁ ተጠንቀቁ! ብዙዎች ‘እኔ መሲሕ ነኝ!’ እያሉ በስሜ ይመጣሉ፤ ብዙ ሰዎችንም ያሳስታሉ። የጦርነትን ድምፅና የጦርነትን ወሬ ትሰማላችሁ፤ ይህ ሁሉ መሆን ስላለበት አትደንግጡ፤ መጨረሻው ግን ገና ነው። ሕዝብ በሕዝብ ላይ፥ መንግሥትም በመንግሥት ላይ በጦርነት ይነሣል፤ በልዩ ልዩ ስፍራ ራብና የምድር መናወጥ ይሆናል። ይህም ሁሉ እንደ ምጥ ጣር ያለ የጭንቅ መጀመሪያ ይሆናል። በዚያን ጊዜ ሰዎች ለመከራ አሳልፈው ይሰጡአችኋል፤ ይገድሉአችኋል፤ ስለ ስሜም በሕዝቦች ሁሉ ዘንድ የተጠላችሁ ትሆናላችሁ። በዚያን ጊዜ ብዙዎች ሃይማኖታቸውን በመካድ ይሰናከላሉ፤ አንዱ ሌላውን አሳልፎ ይሰጣል፤ ሰዎችም እርስ በርሳቸው ይጣላሉ። ብዙ ሐሰተኞች ነቢያት ይነሣሉ፤ ብዙዎችንም ያሳስታሉ፤ ከክፋት ብዛት የተነሣ የብዙ ሰዎች ፍቅር ትቀዘቅዛለች። እስከ መጨረሻ በትዕግሥት የሚጸና ግን ይድናል። ለሕዝቦች ሁሉ ምስክር እንዲሆን ይህ የእግዚአብሔር መንግሥት ወንጌል በመላው ዓለም ይሰበካል፤ በዚያን ጊዜ መጨረሻው ይመጣል። “ነቢዩ ዳንኤል በተናገረው መሠረት የሚያረክሰውን አጸያፊ ነገር በተቀደሰ ስፍራ ቆሞ ባያችሁ ጊዜ አንባቢው ያስተውል! በዚያን ጊዜ በይሁዳ አገር ያሉ ወደ ተራራዎች ይሽሹ። በጣራ ላይ ያለ ከቤቱ አንዳች ነገር ለመውሰድ አይውረድ። በእርሻም ያለ ልብሱን ለመውሰድ ወደ ኋላው አይመለስ፤ በዚያን ጊዜ ለነፍሰጡሮችና ለሚያጠቡ እመጫቶች ወዮላቸው! ሽሽታችሁ በክረምት ወይም በሰንበት ቀን እንዳይሆን ጸልዩ! በዚያን ጊዜ ዓለም ከተፈጠረ ጀምሮ እስከ ዛሬ ድረስ ያልሆነ፥ ወደፊትም እርሱን የሚመስል ከቶ የማይሆን፥ ታላቅ መከራ ይሆናል። እነዚያ ቀኖች ባያጥሩማ ኖሮ አንድም ሰው መዳን ባልቻለ ነበር፤ ነገር ግን ስለ ተመረጡት ሰዎች እነዚያ ቀኖች ያጥራሉ። “በዚያን ጊዜ ማንም ሰው ‘እነሆ፥ መሲሕ እዚህ አለ!’ ወይም ‘እዚያ አለ!’ ቢላችሁ አትመኑ። ሐሰተኞች መሲሖችና ሐሰተኞች ነቢያት ይነሣሉ፤ እነርሱ ቢቻላቸውስ የእግዚአብሔርን ምርጦች እንኳ ለማሳሳት ታላላቅ ተአምራትንና ድንቅ ነገሮችን ያሳያሉ። “እንግዲህ ይህን ሁሉ ነገር አስቀድሜ ነግሬአችኋለሁ፤ ስለዚህ ‘እነሆ፥ በበረሓ አለ!’ ቢሉአችሁ አትውጡ፤ ‘እነሆ፥ በስውር ቦታ አለ!’ ቢሉአችሁ አትመኑ። መብረቅ በሰማይ ብልጭ ብሎ ከምሥራቅ እስከ ምዕራብ እንደሚታይ፥ የሰው ልጅ መምጣትም እንዲሁ ይሆናል። በድን ወደአለበት ቦታ አሞሮች ይሰበሰባሉ። “ከነዚያ ከመከራ ቀኖች በኋላ ወዲያውኑ ፀሐይ ትጨልማለች፤ ጨረቃም ብርሃንዋን አትሰጥም፤ ከዋክብትም ከሰማይ ይወድቃሉ፤ የሰማያት ኀይሎችም ይናወጣሉ። ከዚህም በኋላ የሰው ልጅ ምልክት በሰማይ ላይ ይታያል፤ በዚያን ጊዜ በዓለም ላይ ያሉ ሕዝቦች ሁሉ ያለቅሳሉ። የሰው ልጅም በኀይልና በታላቅ ክብር በደመና ላይ ሆኖ ሲመጣ ያዩታል፤
የማቴዎስ ወንጌል 24 ያንብቡ
ያጋሩ
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: የማቴዎስ ወንጌል 24:1-30
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
ቤት
መጽሐፍ ቅዱስ
እቅዶች
ቪዲዮዎች