ኢየሱስ ከቤተ መቅደስ ወጥቶ ሲሄድ፣ ደቀ መዛሙርቱ የቤተ መቅደሱን ሕንጻ ሊያሳዩት ወደ እርሱ ቀረቡ። እርሱ ግን፣ “ይህን ሁሉ ታያላችሁ? እውነት እላችኋለሁ፤ ድንጋይ በድንጋይ ላይ ተክቦ የምታዩት፣ ሳይፈርስ እንዲሁ እንዳለ የሚቀር አንድ ድንጋይ እንኳ አይኖርም” አላቸው። በደብረ ዘይት ተራራ ላይ ተቀምጦ ሳለ፣ ደቀ መዛሙርቱ ለብቻቸው ወደ እርሱ ቀርበው “እስኪ ንገረን፤ የምትለው ሁሉ መቼ ይሆናል? የመምጣትህና የዓለም መጨረሻ ምልክትስ ምንድን ነው?” አሉት። ኢየሱስም መልሶ እንዲህ አላቸው፤ “ማንም እንዳያስታችሁ ተጠንቀቁ፤ ብዙዎች፣ ‘እኔ ክርስቶስ ነኝ’ በማለት በስሜ ይመጣሉና፤ ብዙዎችንም ያስታሉ። ስለ ጦርነትና ጦርነትን የሚያናፍስ ወሬ ትሰማላችሁ፤ እነዚህ ነገሮች የግድ መፈጸም አለባቸው፤ ሆኖም መጨረሻው ገና ስለ ሆነ በዚህ እንዳትደናገጡ ተጠንቀቁ። ሕዝብ በሕዝብ ላይ፣ መንግሥትም በመንግሥት ላይ ይነሣል፤ በተለያየ ስፍራም ራብና የመሬት መንቀጥቀጥ ይሆናል፤ ይህ ሁሉ ግን የምጡ መጀመሪያ ነው። “በዚያ ጊዜ ለመከራ አሳልፈው ይሰጧችኋል፤ ይገድሏችኋል፤ በስሜ ምክንያት በሕዝብ ሁሉ ዘንድ የተጠላችሁ ትሆናላችሁ። በዚያ ጊዜ ብዙዎች ይሰናከላሉ፤ እርስ በርስ አሳልፈው ይሰጣጣሉ፤ ይጠላላሉም። ብዙዎች ሐሰተኛ ነቢያት ይነሣሉ፤ ብዙዎችን ያስታሉ። ክፋት ስለሚገንን የብዙ ሰዎች ፍቅር ይቀዘቅዛል፤ እስከ መጨረሻ የሚጸና ግን እርሱ ይድናል። ለሕዝብ ሁሉ ምስክር እንዲሆን፣ ይህ የመንግሥት ወንጌል በዓለም ሁሉ ይሰበካል፤ ከዚያም መጨረሻው ይመጣል። “እንግዲህ በነቢዩ በዳንኤል የተነገረው፣ ‘የጥፋት ርኩሰት’ በተቀደሰው ስፍራ ቆሞ ስታዩ፣ አንባቢው ያስተውል። በዚያ ጊዜ በይሁዳ ያሉ ወደ ተራሮች ይሽሹ፤ በቤቱ ጣራ ላይ የሚገኝ ማንም ሰው ዕቃውን ከቤቱ ለማውጣት አይውረድ፤ በዕርሻ ቦታው የሚገኝ ማንም ሰው ልብሱን ለመውሰድ አይመለስ። በእነዚያ ቀናት ለነፍሰ ጡሮችና ለሚያጠቡ ወዮላቸው! እንግዲህ ሽሽታችሁ በክረምት ወይም በሰንበት ቀን እንዳይሆን ጸልዩ፤ በዚያ ጊዜ፣ ከዓለም መጀመሪያ እስከ ዛሬ ድረስ ሆኖ የማያውቅ፣ ከዚህም በኋላ ከቶ የማይሆን ታላቅ መከራ ይሆናል። “ቀኖቹ ባያጥሩ ኖሮ ሥጋ ለባሽ ሁሉ ባልተረፈ ነበረ፤ ስለ ተመረጡት ሲባል ግን እነዚያ ቀኖች ያጥራሉ። በዚያ ጊዜ ማንም፣ ‘ይኸውላችሁ ክርስቶስ እዚህ አለ’ ወይም ‘እዚያ አለ’ ቢላችሁ አትመኑ፤ ሐሰተኛ ክርስቶሶችና ሐሰተኛ ነቢያት ይነሣሉና፤ ቢቻል የተመረጡትን ለማሳት ሲሉ ታላላቅ ምልክቶችንና ታምራትን ያደርጋሉ። እነሆ፤ አስቀድሜ ነግሬአችኋለሁ። “ስለዚህ፣ ‘ያውላችሁ፤ በረሓው ውስጥ አለላችሁ’ ቢሏችሁ ወደዚያ አትውጡ፤ ‘ይኸውላችሁ እልፍኝ ውስጥ አለላችሁ’ ቢሏችሁ አትመኑ፤ መብረቅ ከምሥራቅ ወጥቶ ምዕራብ ድረስ እንደሚያበራ፣ የሰው ልጅ አመጣጥም እንደዚሁ ይሆናል። በድን ባለበት ስፍራ ሁሉ አሞሮች ይሰበሰባሉ። “ወዲያውኑ ከእነዚያ ከመከራው ቀናት በኋላ፣ “ ‘ፀሓይ ትጨልማለች፤ ጨረቃ ብርሃኗን ትከለክላለች፤ ከዋክብት ከሰማይ ይረግፋሉ፤ የሰማይ ኀይላትም ይናጋሉ።’ “በዚህ ጊዜ የሰው ልጅ ምልክት በሰማይ ላይ ይታያል፤ የምድር ወገኖች ሁሉ ያለቅሳሉ፤ የሰው ልጅም በሰማይ ደመና ሆኖ በኀይልና በታላቅ ክብር ሲመጣ ያዩታል፤
ማቴዎስ 24 ያንብቡ
ያዳምጡ ማቴዎስ 24
ያጋሩ
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: ማቴዎስ 24:1-30
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
ቤት
መጽሐፍ ቅዱስ
እቅዶች
ቪዲዮዎች