በዚያን ጊዜ ኢየሱስ ለሕዝቡና ለደቀ መዛሙርቱ እንዲህ ብሎ ነገራቸው፦ ጻፎችና ፈሪሳውያን በሙሴ ወንበር ተቀምጠዋል። ስለዚህ ያዘዙአችሁን ሁሉ አድርጉ ጠብቁትም፥ ነገር ግን እየተናገሩ አያደርጉትምና እንደ ሥራቸው አታድርጉ። ከባድና አስቸጋሪ ሸክም ተብትበው በሰው ትከሻ ይጭናሉ፥ እነርሱ ግን በጣታቸው ስንኳ ሊነኩት አይወዱም። ለሰውም እንዲታዩ ሥራቸውን ሁሉ ያደርጋሉ፤ ስለዚህ አሽንክታባቸውን ያሰፋሉ ዘርፉንም ያስረዝማሉ፥ በምሳም የከበሬታ ስፍራ፥ በምኵራብም የከበሬታ ወንበር፥ በገበያም ሰላምታና፦ መምህር ሆይ መምህር ሆይ ተብለው እንዲጠሩ ይወዳሉ። እናንተ ግን፦ መምህር ተብላችሁ አትጠሩ፤ መምህራችሁ አንድ ስለ ሆነ እናንተም ሁላችሁ ወንድማማች ናችሁ። አባታችሁ አንዱ እርሱም የሰማዩ ነውና በምድር ላይ ማንንም፦ አባት ብላችሁ አትጥሩ። ሊቃችሁ አንድ እርሱም ክርስቶስ ነውና፦ ሊቃውንት ተብላችሁ አትጠሩ። ከእናንተም የሚበልጠው አገልጋያችሁ ይሆናል። ራሱን ከፍ የሚያደርግ ሁሉ ይዋረዳል፥ ራሱንም የሚያዋርድ ሁሉ ከፍ ይላል። እናንተ ግብዞች ጻፎችና ፈሪሳውያን፥ መንግሥተ ሰማያትን በሰው ፊት ስለምትዘጉ፥ ወዮላችሁ እናንተ አትገቡም የሚገቡትንም እንዳይገቡ ትከለክላላችሁ። እናንተ ግብዞች ጻፎችና ፈሪሳውያን፥ በጸሎት ርዝመት እያመካኛችሁ የመበለቶችን ቤት ስለምትበሉ፥ ወዮላችሁ፤ ስለዚህ የባሰ ፍርድ ትቀበላላችሁ። እናንተ ግብዞች ጻፎችና ፈሪሳውያን፥ አንድ ሰው ልታሳምኑ በባሕርና በደረቅ ስለምትዞሩ፥ በሆነም ጊዜ ከእናንተ ይልቅ ሁለት እጥፍ የባሰ የገሃነም ልጅ ስለምታደርጉት፥ ወዮላችሁ። እናንተ፦ ማንም በቤተ መቅደስ የሚምል ምንም የለበትም፤ ማንም በቤተ መቅደስ ወርቅ የሚምል ግን በመሐላው ይያዛል የምትሉ፥ ዕውሮች መሪዎች፥ ወዮላችሁ። እናንተ ደንቆሮዎችና ዕውሮች፥ ማናቸው ይበልጣል? ወርቁ ነውን? ወይስ ወርቁን የቀደሰው ቤተ መቅደስ? ደግማችሁም፦ ማንም በመሠዊያው የሚምል ምንም የለበትም፤ ማንም በላዩ ባለው መባ የሚምል ግን በመሐላው ይያዛል ትላላችሁ። እናንተ ደንቆሮዎችና ዕውሮች፥ ማናቸው ይበልጣል? መባው ነውን? ወይስ መባውን የሚቀድሰው መሠዊያው? እንግዲህ በመሠዊያው የሚምለው በእርሱና በእርሱ ላይ ባለው ሁሉ ይምላል፤ በቤተ መቅደስም የሚምለው በእርሱና በእርሱ በሚኖረው ይምላል፤ በሰማይም የሚምለው በእግዚአብሔር ዙፋንና በእርሱ ላይ በተቀመጠው ይምላል።
የማቴዎስ ወንጌል 23 ያንብቡ
ያጋሩ
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: የማቴዎስ ወንጌል 23:1-22
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
ቤት
መጽሐፍ ቅዱስ
እቅዶች
ቪዲዮዎች