የማቴዎስ ወንጌል 23:1-22

የማቴዎስ ወንጌል 23:1-22 አማ05

ከዚህ በኋላ ኢየሱስ ለሕዝቡና ለደቀ መዛሙርቱ እንዲህ ሲል ተናገረ፦ “የሕግ መምህራንና ፈሪሳውያን ለማስተማር በሙሴ ወንበር ተቀምጠዋል። ስለዚህ እነርሱ የሚሉአችሁን ሁሉ አድርጉ፤ ጠብቁም፤ እነርሱ የሚያደርጉትን ግን አታድርጉ፤ እነርሱ የሚናገሩትን በሥራ ላይ አያውሉትም፤ ከባድና አስቸጋሪ ሸክም አስረው በሰው ትከሻ ላይ ይጭናሉ፤ ራሳቸው ግን በጣታቸው እንኳ ሊነኩት አይፈልጉም። ሥራቸውን ሁሉ የሚያደርጉት ሰው እንዲያይላቸው ብለው ነው፤ አሸንክታባቸውን ያሰፋሉ፤ የጸሎት ልብሳቸውን ዘርፍ ያስረዝማሉ፤ በግብዣ ላይ የክብር ቦታን፥ በምኲራብም የመጀመሪያ መቀመጫን መያዝ ይወዳሉ። በየአደባባዩም ሰው ሁሉ እጅ እንዲነሣቸውና ‘መምህር ሆይ!’ ብሎ እንዲጠራቸው ይፈልጋሉ፤ እናንተ ግን መምህራችሁ አንድ ብቻ ስለ ሆነና ሁላችሁም ወንድማማቾች ስለ ሆናችሁ፥ ‘መምህር’ ተብላችሁ አትጠሩ። ደግሞም እናንተ ያላችሁ በሰማይ አንድ አባት ብቻ ስለ ሆነ በምድር ላይ ማንንም ‘አባት’ ብላችሁ አትጥሩ። ሊቃችሁ ክርስቶስ ብቻ ስለ ሆነ ‘ሊቃውንት’ ተብላችሁ አትጠሩ። ከእናንተ መካከል ታላቅ የሆነው የእናንተ አገልጋይ ይሁን። ራሱን ከፍ የሚያደርግ ይዋረዳል፤ ራሱንም ዝቅ የሚያደርግ ከፍ ይላል።” “ሰው ወደ መንግሥተ ሰማይ እንዳይገባ፥ በሩን የምትዘጉ እናንተ ግብዞች፥ የሕግ መምህራንና ፈሪሳውያን! ወዮላችሁ! እናንተ ራሳችሁ አትገቡበትም፤ መግባት የሚፈልጉትንም እንዳይገቡ ትከለክላላችሁ!” [ “ለታይታ በምታቀርቡት ረዥም ጸሎት እያመካኛችሁ ባሎቻቸው የሞቱባቸውን ሴቶች መተዳደሪያ የምትጨርሱ እናንተ ግብዞች የሕግ መምህራንና ፈሪሳውያን ወዮላችሁ! ስለዚህ እናንተ የባሰ ፍርድ ይደርስባችኋል።] “እናንተ ግብዞች፥ የሕግ መምህራንና ፈሪሳውያን! ወዮላችሁ! አንድን ሰው የእምነታችሁ ተከታይ ለማድረግ በባሕርና በየብስ ትዞራላችሁ፤ ባስገባችሁትም ጊዜ፥ ከእናንተ በሁለት እጥፍ ይብስ ለገሃነም የተዘጋጀ ታደርጉታላችሁ! “እናንተ ዕውሮች መሪዎች! ወዮላችሁ! ‘ሰው በቤተ መቅደስ ቢምል፥ ምንም አይደለም’ ትላላችሁ፤ ‘በቤተ መቅደሱ ወርቅ ቢምል ግን በመሐላው ይያዛል’ ትላላችሁ፤ እናንተ ሞኞችና ዕውሮች! ከወርቁና ወርቁን ከሚቀድሰው ቤተ መቅደስ የቱ ይበልጣል? እንዲሁም ‘ሰው በመሠዊያው ቢምል ምንም አይደለም’፤ ‘በመሠዊያው ላይ ባለው መባ ቢምል ግን በመሐላው ይያዛል’ ትላላችሁ። እናንተ ዕውሮች! ከመባውና መባውን ከሚቀድሰው መሠዊያ የቱ ይበልጣል? ስለዚህ በመሠዊያው የሚምል፥ በመሠዊያውና በመሠዊያው ላይ ባለው ነገር ሁሉ ይምላል። በቤተ መቅደስም የሚምል፥ በቤተ መቅደሱና በቤተ መቅደሱ ውስጥ በሚኖረው ይምላል። በሰማይ የሚምልም በእግዚአብሔር ዙፋንና በዙፋኑ ላይ በሚቀመጠው ይምላል።

ተዛማጅ ቪዲዮዎች