ማቴዎስ 23:1-22

ማቴዎስ 23:1-22 NASV

ከዚያም ኢየሱስ ለሕዝቡና ለደቀ መዛሙርቱ እንዲህ ሲል ተናገረ፤ “የኦሪት ሕግ መምህራንና ፈሪሳውያን በሙሴ ወንበር ላይ ተቀምጠዋል። ስለዚህ የሚነግሯችሁን ሁሉ አድርጉ፤ ጠብቁትም፤ ነገር ግን እንደሚናገሩት አያደርጉምና ተግባራቸውን አትከተሉ። እንዲሁም ለመሸከም የማይቻል ከባድ ሸክም አስረው በሰዎች ትከሻ ላይ ይጭናሉ፤ ራሳቸው ግን በጣታቸው እንኳ አይነኩትም። “ለመታየት ሲሉ የሚያደርጉትን ሁሉ በሰው ፊት ያደርጋሉ፤ አሸንክታባቸውን ያሰፋሉ፤ የቀሚሳቸውን ዘርፍ ያስረዝማሉ። በግብዣ ቦታ የከበሬታ ስፍራ፣ በምኵራብም የመጀመሪያውን መቀመጫ መያዝ፣ እንዲሁም በገበያ ስፍራ የአክብሮት ሰላምታና በሰዎች አንደበት ‘መምህር’ ተብለው መጠራትን ይወድዳሉ። “እናንተ ግን ‘መምህር’ ተብላችሁ አትጠሩ፤ አስተማሪያችሁ አንድ ብቻ ነው፤ እናንተ ሁላችሁም ወንድማማቾች ናችሁና። በሰማይ ያለ አንድ አባት ስላላችሁ፣ በምድር ማንንም ‘አባት’ ብላችሁ አትጥሩ። መምህራችሁ አንዱ ክርስቶስ ስለ ሆነ፣ ‘መምህር’ ተብላችሁ አትጠሩ። ከመካከላችሁ ከሁላችሁ የሚበልጠው አገልጋያችሁ ይሆናል፤ ራሱን ከፍ ከፍ የሚያደርግ ይዋረዳል፣ ራሱን ዝቅ ዝቅ የሚያደርግ ግን ይከበራል። “እናንተ ግብዞች የኦሪት ሕግ መምህራንና ፈሪሳውያን ወዮላችሁ! ሰዎች ወደ መንግሥተ ሰማይ እንዳይገቡ በሩን ስለምትዘጉባቸው እናንተ ራሳችሁ አትገቡም፤ መግባት የሚፈልጉትንም አታስገቡም። [“እናንተ ግብዞች የኦሪት ሕግ መምህራንና ፈሪሳውያን፤ ወዮላችሁ! የመበለቶችን ቤት እያራቈታችሁ፣ ለሰው ይምሰል ረዥም ጸሎት ስለምታደርጉ የከፋ ፍርድ ትቀበላላችሁ።] “እናንተ ግብዞች የኦሪት ሕግ መምህራንና ፈሪሳውያን፤ አንድን ሰው ወደ አይሁድ ሃይማኖት ለማስገባት በባሕርና በየብስ ስለምትጓዙ፣ ባመነም ጊዜ ከእናንተ በዕጥፍ የባሰ የገሃነም ልጅ ስለምታደርጉት ወዮላችሁ። “እናንተ ዕውር መሪዎች፤ ወዮላችሁ! ‘ማንም በቤተ መቅደስ ቢምል ምንም አይደለም፤ ነገር ግን በቤተ መቅደሱ ውስጥ ባለው ወርቅ ቢምል መሐላው ይደርስበታል’ ትላላችሁ። እናንተ የታወራችሁ ተላላዎች! ከወርቁና ወርቁን ከቀደሰው ቤተ መቅደስ የቱ ይበልጣል? እንዲሁም፣ ‘ማንም በመሠዊያው ቢምል ምንም አይደለም፤ ነገር ግን በላዩ ላይ ባለው መባ ቢምል መሐላው ይደርስበታል’ ትላላችሁ፤ እናንተ ዕውሮች፤ ከመባውና መባውን ከቀደሰው መሠዊያ የቱ ይበልጣል? ስለዚህ፣ በመሠዊያው የማለ፣ በመሠዊያውና በላዩ ላይ ባለው ሁሉ ይምላል። እንዲሁም በቤተ መቅደሱ የማለ፣ በቤተ መቅደሱና በውስጡ በሚያድረው ይምላል። በሰማይ የማለም በእግዚአብሔር ዙፋንና በዙፋኑ ላይ በተቀመጠው ይምላል።

ተዛማጅ ቪዲዮዎች