የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

የሉቃስ ወንጌል 22:1-38

የሉቃስ ወንጌል 22:1-38 አማ54

ፋሲካም የሚባለው የቂጣ በዓል ቀረበ። የካህናት አለቆችና ጻፎችም እንዴት እንዲያጠፉት ይፈልጉ ነበር፤ ሕዝቡን ይፈሩ ነበርና። ሰይጣንም ከአሥራ ሁለቱ ቍጥር አንዱ በነበረው የአስቆሮቱ በሚባለው በይሁዳ ገባ፤ ሄዶም እንዴት አሳልፎ እንዲሰጣቸው ከካህናት አለቆችና ከመቅደስ አዛዦች ጋር ተነጋገረ። እነርሱም ደስ አላቸው፥ ገንዘብም ሊሰጡት ተዋዋሉ። እሺም አለ፥ ሕዝብም በሌለበት አሳልፎ እንዲሰጣቸው ምቹ ጊዜ ይፈልግ ነበር። ፋሲካንም ሊያርዱበት የሚገባው የቂጣ በዓል ደረሰ፤ ጴጥሮስንና ዮሐንስንም፦ ፋሲካን እንድንበላ ሄዳችሁ አዘጋጁልን ብሎ ላካቸው። እነርሱም፦ ወዴት እናዘጋጅ ዘንድ ትወዳለህ? አሉት። እርሱም አላቸው፦ እነሆ፥ ወደ ከተማ ስትገቡ ማድጋ ውኃ የተሸከመ ሰው ይገናኛችኋል፤ ወደ ሚገባበት ቤት ተከተሉት፤ ለባለቤቱም፦ መምህሩ፦ ከደቀ መዛሙርቴ ጋር ፋሲካን የምበላበት የእንግዳ ቤት ክፍል ወዴት ነው? ይልሃል በሉት፤ ያም በደርብ ላይ ያለውን የተነጠፈ ታላቅ አዳራሽ ያሳያችኋል፤ በዚያም አሰናዱልን። ሄደውም እንዳላቸው አገኙና ፋሲካን አሰናዱ። ሰዓቱም በደረሰ ጊዜ ከአሥራ ሁለቱ ሐዋርያት ጋር በማዕድ ተቀመጠ። እርሱም፦ ከመከራዬ በፊት ከእናንተ ጋር ይህን ፋሲካ ልበላ እጅግ እመኝ ነበር፤ እላችኋለሁና፥ በእግዚአብሔር መንግሥት እስኪፈጸም ድረስ፥ ወደ ፊት ከዚህ አልበላም አላቸው። ጽዋንም ተቀበለ አመስግኖም፦ ይህን እንካችሁ በመካከላችሁም ተካፈሉት፤ እላችኋለሁና፥ የእግዚአብሔር መንግሥት እስክትመጣ ድረስ ከአሁን ጀምሮ ከወይኑ ፍሬ አልጠጣም አለ። እንጀራንም አንሥቶ አመሰገነ ቆርሶም ሰጣቸውና፦ ስለ እናንተ የሚሰጠው ሥጋዬ ይህ ነው፤ ይህን ለመታሰቢያዬ አድርጉት አለ። እንዲሁም ከእራት በኋላ ጽዋውን አንሥቶ እንዲህ አለ፦ ይህ ጽዋ ስለ እናንተ በሚፈሰው በደሜ የሚሆን አዲስ ኪዳን ነው። ነገር ግን አሳልፎ የሚሰጠኝ እጅ እነሆ በማዕድ ከእኔ ጋር ናት። የሰው ልጅስ እንደ ተወሰነው ይሄዳል፥ ነገር ግን አልፎ ለሚሰጥበት ለዚያ ሰው ወዮለት። ከእነርሱም ይህን ሊያደርግ ያለው ማን እንደ ሆነ እርስ በርሳቸው ይጠያየቁ ጀመር። ደግሞም ማናቸውም ታላቅ ሆኖ እንዲቈጠር በመካከላቸው ክርክር ሆነ። እንዲህም አላቸው፦ የአሕዛብ ነገሥታት ይገዙአቸዋል፥ በላያቸውም የሚሠለጥኑት ቸርነት አድራጊዎች ይባላሉ። እናንተ ግን እንዲህ አትሁኑ፤ ነገር ግን ከእናንተ ታላቅ የሆነ በመካከላችሁ እንደ ታናሽ፥ የሚገዛም እንደሚያገለግል ይሁን። በማዕድ የተቀመጠ ወይስ የሚያገለግል ማናቸው ታላቅ ነው? የተቀመጠው አይደለምን? እኔ ግን በመካከላችሁ እንደሚያገለግል ነኝ። ነገር ግን እናንተ በፈተናዎቼ ከእኔ ጋር ጸንታችሁ የኖራችሁ ናችሁ፤ አባቴ እኔን እንደ ሾመኝ እኔ ደግሞ በመንግሥቴ ከማዕዴ ትበሉና ትጠጡ ዘንድ፥ በአሥራ ሁለቱ በእስራኤል ነገድ ስትፈርዱ በዙፋኖች ትቀመጡ ዘንድ ለመንግሥት እሾማችኋለሁ። ጌታም፦ ስምዖን ስምዖን ሆይ፥ እነሆ፥ ሰይጣን እንደ ስንዴ ሊያበጥራችሁ ለመነ፤ እኔ ግን እምነትህ እንዳይጠፋ ስለ አንተ አማለድሁ፤ አንተም በተመለስህ ጊዜ ወንድሞችህን አጽና አለ። እርሱም፦ ጌታ ሆይ፥ ወደ ወኅኒም ወደ ሞትም ከአንተ ጋር ለመሄድ የተዘጋጀሁ ነኝ አለው። እርሱ ግን፦ ጴጥሮስ ሆይ፥ እልሃለሁ፥ እንዳታውቀኝ ሦስት ጊዜ እስክትክደኝ ድረስ ዛሬ ዶሮ አይጮኽም አለው። ደግሞም፦ ያለ ኮረጆና ያለ ከረጢት ያለ ጫማም በላክኋችሁ ጊዜ፥ አንዳች ጐደለባችሁን? አላቸው። እነርሱም፦ አንዳች እንኳ አሉ። እርሱም፦ አሁን ግን ኮረጆ ያለው ከእርሱ ጋር ይውሰድ፥ ከረጢትም ያለው እንዲሁ፤ የሌለውም ልብሱን ሽጦ ሰይፍ ይግዛ። እላችኋለሁና፥ ይህ፦ ከዓመፀኞች ጋር ተቈጠረ ተብሎ የተጻፈው በእኔ ሊፈጸም ግድ ነው፤ አዎን፥ ስለ እኔ የሚሆነው አሁን ይፈጸማልና አላቸው። እነርሱም፦ ጌታ ሆይ፥ እነሆ፥ በዚህ ሁለት ሰይፎች አሉ አሉት። እርሱም፦ ይበቃል አላቸው።