የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

ሉቃስ 22:1-38

ሉቃስ 22:1-38 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

በዚህ ጊዜ ፋሲካ የተባለው የቂጣ በዓል ተቃርቦ ነበር። የካህናት አለቆችና ጸሐፍትም ሕዝቡን ይፈሩ ስለ ነበር፣ እንዴት አድርገው ኢየሱስን እንደሚያስወግዱት መንገድ ይፈልጉ ነበር። ሰይጣንም ከዐሥራ ሁለቱ አንዱ የሆነው የአስቆሮቱ ይሁዳ በተባለው ገባበት፤ ይሁዳም ወደ ካህናት አለቆችና ወደ ቤተ መቅደሱ ሹሞች ሄዶ ኢየሱስን እንዴት አሳልፎ እንደሚሰጣቸው ተነጋገረ። እነርሱም በዚህ ደስ አላቸው፣ ገንዘብ ሊሰጡትም ተዋዋሉ። እርሱም በነገሩ ተስማማ፤ አሳልፎ ሊሰጣቸውም ሕዝብ የማይገኝበትን ምቹ ጊዜ ይፈልግ ጀመር። ከዚህ በኋላ የፋሲካ በግ የሚታረድበት የቂጣ በዓል ደረሰ። ኢየሱስም፣ “የፋሲካን እራት እንድንበላ ሄዳችሁ አዘጋጁልን” ብሎ ጴጥሮስንና ዮሐንስን ላካቸው። እነርሱም፣ “የት እንድናሰናዳ ትፈልጋለህ?” አሉት። እርሱም እንዲህ አላቸው፤ “እነሆ፤ ወደ ከተማ ስትገቡ የውሃ እንስራ የተሸከመ ሰው ያገኛችኋል፤ እርሱ ወደሚገባበት ቤት ድረስ ተከተሉት፤ ለቤቱም ባለቤት፣ ‘መምህሩ፣ ከደቀ መዛሙርቴ ጋራ የፋሲካን እራት የምበላበት የእንግዳ ክፍል ወዴት ነው? ይልሃል’ በሉት። እርሱም በሰገነት ላይ የተሰናዳ ሰፊ አዳራሽ ያሳያችኋል፤ እዚያ አዘጋጁ።” እነርሱም ሄደው ልክ ኢየሱስ እንደ ነገራቸው ሆኖ አገኙት፤ ፋሲካንም በዚያ አዘጋጁ። ሰዓቱም በደረሰ ጊዜ ኢየሱስ ከሐዋርያቱ ጋራ በማእድ ተቀመጠ፤ እንዲህም አላቸው፤ “መከራ ከመቀበሌ በፊት ይህን ፋሲካ አብሬያችሁ ለመብላት በጣም ስመኝ ነበር፤ እላችኋለሁ፤ በእግዚአብሔር መንግሥት የዚህ ትርጕም እስኪፈጸም ድረስ ይህን ፋሲካ ዳግመኛ አልበላም።” ጽዋውን ተቀብሎ ካመሰገነ በኋላ እንዲህ አላቸው፤ “ዕንካችሁ፤ ሁላችሁ ከዚህ ተካፈሉ፤ እላችኋለሁ፤ የእግዚአብሔር መንግሥት እስከምትመጣ ድረስ ከወይን ፍሬ አልጠጣም።” እንጀራንም አንሥቶ አመሰገነ፤ ቈርሶም ሰጣቸውና፣ “ይህ ስለ እናንተ የሚሰጥ ሥጋዬ ነው፤ ይህን ለመታሰቢያዬ አድርጉት” አለ። እንደዚሁም ከእራት በኋላ ጽዋውን አንሥቶ እንዲህ አለ፤ “ይህ ጽዋ ስለ እናንተ በሚፈስሰው ደሜ የሚመሠረት አዲስ ኪዳን ነው። ነገር ግን አሳልፎ የሚሰጠኝ ሰው እጅ በማእድ ከእኔ ጋራ ናት። የሰው ልጅስ አስቀድሞ በተወሰነው መሠረት ይሄዳል፤ ነገር ግን እርሱን አሳልፎ ለሚሰጠው ለዚያ ሰው ወዮለት!” እነርሱም ከመካከላቸው ይህን የሚያደርግ ማን ሊሆን እንደሚችል እርስ በርሳቸው ይጠያየቁ ጀመር። ደግሞም ከመካከላቸው ማን የሚበልጥ ሆኖ እንደሚቈጠር በእነርሱ ዘንድ ክርክር ተነሣ። እንዲህ አላቸው፤ “የአሕዛብ ነገሥታት ሕዝቦቻቸውን በኀይል ይገዛሉ፤ በእነርሱ ላይ ሥልጣን ያላቸውም በጎ አድራጊዎች ተብለው ይጠራሉ። በእናንተ ዘንድ ግን እንዲህ አይሁን፤ ይልቁን ከእናንተ ታላቅ የሆነ እንደ ታናሽ፣ ገዥ የሆነም እንደ አገልጋይ ይሁን። ለመሆኑ፣ በማእድ ከተቀመጠና ቆሞ ከሚያስተናግድ ማን ይበልጣል? በማእድ የተቀመጠው አይደለምን? እኔ ግን በመካከላችሁ ያለሁት እንደ አንድ አገልጋይ ነው። እናንተም ሳትለዩኝ በመከራዬ ጊዜ በአጠገቤ የቆማችሁ ናችሁ፤ አባቴ እኔን እንደ ሾመኝ እኔም ደግሞ በመንግሥቴ እሾማችኋለሁ፤ ይኸውም በመንግሥቴ ከማእዴ እንድትበሉና እንድትጠጡ፣ ደግሞም በዙፋን ላይ ተቀምጣችሁ በዐሥራ ሁለቱ የእስራኤል ነገድ ላይ እንድትፈርዱ ነው።” ደግሞም ኢየሱስ እንዲህ አለ፤ “ስምዖን፣ ስምዖን ሆይ፤ እነሆ፤ ሰይጣን እንደ ስንዴ ሊያበጥራችሁ ለመነ፤ እኔ ግን እምነትህ እንዳይጠፋ ስለ አንተ ጸለይሁ፤ አንተም በተመለስህ ጊዜ ወንድሞችህን አበርታ።” ስምዖንም፣ “ጌታ ሆይ፤ እኔ ከአንተ ጋራ ወህኒ ለመውረድም፣ ለመሞትም ዝግጁ ነኝ” አለው። ኢየሱስም፣ “ጴጥሮስ ሆይ፤ እልሃለሁ፤ ዛሬ ዶሮ ሳይጮኽ፣ አላውቀውም ብለህ ሦስት ጊዜ ትክደኛለህ” አለው። ከዚያም ኢየሱስ፣ “ያለ ኰረጆ፣ ያለ ከረጢትና ያለ ጫማ በላክኋችሁ ጊዜ የጐደለባችሁ ነገር ነበርን?” ብሎ ጠየቃቸው። እነርሱም፣ “ምንም አልጐደለብንም” አሉ። እርሱም እንዲህ አላቸው፤ “አሁን ግን ኰረጆም፣ ከረጢትም ያለው ሰው ይያዝ፤ ሰይፍ የሌለውም ልብሱን ሽጦ ይግዛ። እላችኋለሁና፤ ‘ከዐመፀኞች ጋራ ተቈጠረ’ ተብሎ የተጻፈው በእኔ መፈጸም አለበት፤ ስለ እኔ የተጻፈው ፍጻሜው በርግጥ ደርሷል።” ደቀ መዛሙርቱም፣ “ጌታ ሆይ፤ እነሆ፤ ሁለት ሰይፎች እዚህ አሉ” አሉት። እርሱም፣ “ይበቃል” አላቸው።

ሉቃስ 22:1-38 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)

ፋሲካም የሚባለው የቂጣ በዓል ቀረበ። የካህናት አለቆችና ጻፎችም እንዴት እንዲያጠፉት ይፈልጉ ነበር፤ ሕዝቡን ይፈሩ ነበርና። ሰይጣንም ከአሥራ ሁለቱ ቍጥር አንዱ በነበረው የአስቆሮቱ በሚባለው በይሁዳ ገባ፤ ሄዶም እንዴት አሳልፎ እንዲሰጣቸው ከካህናት አለቆችና ከመቅደስ አዛዦች ጋር ተነጋገረ። እነርሱም ደስ አላቸው፥ ገንዘብም ሊሰጡት ተዋዋሉ። እሺም አለ፥ ሕዝብም በሌለበት አሳልፎ እንዲሰጣቸው ምቹ ጊዜ ይፈልግ ነበር። ፋሲካንም ሊያርዱበት የሚገባው የቂጣ በዓል ደረሰ፤ ጴጥሮስንና ዮሐንስንም፦ ፋሲካን እንድንበላ ሄዳችሁ አዘጋጁልን ብሎ ላካቸው። እነርሱም፦ ወዴት እናዘጋጅ ዘንድ ትወዳለህ? አሉት። እርሱም አላቸው፦ እነሆ፥ ወደ ከተማ ስትገቡ ማድጋ ውኃ የተሸከመ ሰው ይገናኛችኋል፤ ወደ ሚገባበት ቤት ተከተሉት፤ ለባለቤቱም፦ መምህሩ፦ ከደቀ መዛሙርቴ ጋር ፋሲካን የምበላበት የእንግዳ ቤት ክፍል ወዴት ነው? ይልሃል በሉት፤ ያም በደርብ ላይ ያለውን የተነጠፈ ታላቅ አዳራሽ ያሳያችኋል፤ በዚያም አሰናዱልን። ሄደውም እንዳላቸው አገኙና ፋሲካን አሰናዱ። ሰዓቱም በደረሰ ጊዜ ከአሥራ ሁለቱ ሐዋርያት ጋር በማዕድ ተቀመጠ። እርሱም፦ ከመከራዬ በፊት ከእናንተ ጋር ይህን ፋሲካ ልበላ እጅግ እመኝ ነበር፤ እላችኋለሁና፥ በእግዚአብሔር መንግሥት እስኪፈጸም ድረስ፥ ወደ ፊት ከዚህ አልበላም አላቸው። ጽዋንም ተቀበለ አመስግኖም፦ ይህን እንካችሁ በመካከላችሁም ተካፈሉት፤ እላችኋለሁና፥ የእግዚአብሔር መንግሥት እስክትመጣ ድረስ ከአሁን ጀምሮ ከወይኑ ፍሬ አልጠጣም አለ። እንጀራንም አንሥቶ አመሰገነ ቆርሶም ሰጣቸውና፦ ስለ እናንተ የሚሰጠው ሥጋዬ ይህ ነው፤ ይህን ለመታሰቢያዬ አድርጉት አለ። እንዲሁም ከእራት በኋላ ጽዋውን አንሥቶ እንዲህ አለ፦ ይህ ጽዋ ስለ እናንተ በሚፈሰው በደሜ የሚሆን አዲስ ኪዳን ነው። ነገር ግን አሳልፎ የሚሰጠኝ እጅ እነሆ በማዕድ ከእኔ ጋር ናት። የሰው ልጅስ እንደ ተወሰነው ይሄዳል፥ ነገር ግን አልፎ ለሚሰጥበት ለዚያ ሰው ወዮለት። ከእነርሱም ይህን ሊያደርግ ያለው ማን እንደ ሆነ እርስ በርሳቸው ይጠያየቁ ጀመር። ደግሞም ማናቸውም ታላቅ ሆኖ እንዲቈጠር በመካከላቸው ክርክር ሆነ። እንዲህም አላቸው፦ የአሕዛብ ነገሥታት ይገዙአቸዋል፥ በላያቸውም የሚሠለጥኑት ቸርነት አድራጊዎች ይባላሉ። እናንተ ግን እንዲህ አትሁኑ፤ ነገር ግን ከእናንተ ታላቅ የሆነ በመካከላችሁ እንደ ታናሽ፥ የሚገዛም እንደሚያገለግል ይሁን። በማዕድ የተቀመጠ ወይስ የሚያገለግል ማናቸው ታላቅ ነው? የተቀመጠው አይደለምን? እኔ ግን በመካከላችሁ እንደሚያገለግል ነኝ። ነገር ግን እናንተ በፈተናዎቼ ከእኔ ጋር ጸንታችሁ የኖራችሁ ናችሁ፤ አባቴ እኔን እንደ ሾመኝ እኔ ደግሞ በመንግሥቴ ከማዕዴ ትበሉና ትጠጡ ዘንድ፥ በአሥራ ሁለቱ በእስራኤል ነገድ ስትፈርዱ በዙፋኖች ትቀመጡ ዘንድ ለመንግሥት እሾማችኋለሁ። ጌታም፦ ስምዖን ስምዖን ሆይ፥ እነሆ፥ ሰይጣን እንደ ስንዴ ሊያበጥራችሁ ለመነ፤ እኔ ግን እምነትህ እንዳይጠፋ ስለ አንተ አማለድሁ፤ አንተም በተመለስህ ጊዜ ወንድሞችህን አጽና አለ። እርሱም፦ ጌታ ሆይ፥ ወደ ወኅኒም ወደ ሞትም ከአንተ ጋር ለመሄድ የተዘጋጀሁ ነኝ አለው። እርሱ ግን፦ ጴጥሮስ ሆይ፥ እልሃለሁ፥ እንዳታውቀኝ ሦስት ጊዜ እስክትክደኝ ድረስ ዛሬ ዶሮ አይጮኽም አለው። ደግሞም፦ ያለ ኮረጆና ያለ ከረጢት ያለ ጫማም በላክኋችሁ ጊዜ፥ አንዳች ጐደለባችሁን? አላቸው። እነርሱም፦ አንዳች እንኳ አሉ። እርሱም፦ አሁን ግን ኮረጆ ያለው ከእርሱ ጋር ይውሰድ፥ ከረጢትም ያለው እንዲሁ፤ የሌለውም ልብሱን ሽጦ ሰይፍ ይግዛ። እላችኋለሁና፥ ይህ፦ ከዓመፀኞች ጋር ተቈጠረ ተብሎ የተጻፈው በእኔ ሊፈጸም ግድ ነው፤ አዎን፥ ስለ እኔ የሚሆነው አሁን ይፈጸማልና አላቸው። እነርሱም፦ ጌታ ሆይ፥ እነሆ፥ በዚህ ሁለት ሰይፎች አሉ አሉት። እርሱም፦ ይበቃል አላቸው።

ሉቃስ 22:1-38 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)

ፋሲ​ካም የሚ​ባ​ለው የቂጣ በዓል ቀረበ። የካ​ህ​ናት አለ​ቆ​ችና ጻፎ​ችም ሊገ​ድ​ሉት ይሹ ነበር፤ ነገር ግን ሕዝ​ቡን ይፈ​ሩ​አ​ቸው ነበር። ቍጥሩ ከዐ​ሥራ ሁለቱ በነ​በ​ረው በአ​ስ​ቆ​ሮቱ ይሁዳ ልብ ሰይ​ጣን አደረ። ሄዶም ከካ​ህ​ናት አለ​ቆ​ችና ከታ​ላ​ላ​ቆች ጋር እር​ሱን አሳ​ልፎ እን​ዲ​ሰ​ጣ​ቸው ተነ​ጋ​ገረ። ደስ ብሏ​ቸ​ውም ሠላሳ ብር ሊሰ​ጡት ተስ​ማሙ። እር​ሱም እሺ አለ፤ ሰው ሳይ​ኖ​ርም እር​ሱን አሳ​ልፎ ሊሰ​ጣ​ቸው ምቹ ጊዜ ይሻ ነበር። የፋ​ሲ​ካን በግ የሚ​ያ​ር​ዱ​ባት የቂጣ በዓ​ልም ደረ​ሰች። ጌታ​ችን ኢየ​ሱ​ስም ጴጥ​ሮ​ስ​ንና ዮሐ​ን​ስን፥ “ሂዱና የም​ን​በ​ላ​ውን የፋ​ሲካ በግ አዘ​ጋ​ጁ​ልን” አላ​ቸው። እነ​ር​ሱም፥ “ወዴት ልና​ዘ​ጋ​ጅ​ልህ ትወ​ዳ​ለህ?” አሉት። እን​ዲ​ህም አላ​ቸው፥ “ወደ ከተማ በገ​ባ​ችሁ ጊዜ፥ የውኃ ማድጋ የተ​ሸ​ከመ ሰው ታገ​ኛ​ላ​ችሁ፤ ወደ​ሚ​ገ​ባ​በ​ትም ቤት እር​ሱን ተከ​ተ​ሉት። የዚ​ያን ቤት ጌታ፦ መም​ህር ከደቀ መዛ​ሙ​ርቴ ጋር የፋ​ሲ​ካን በግ የም​በ​ላ​በት ቤት ወዴት ነው? ብሎ​ሃል በሉት። እር​ሱም በሰ​ገ​ነት ላይ የተ​ነ​ጠፈ ታላቅ አዳ​ራሽ ያሳ​ያ​ች​ኋል፤ በዚያ አዘ​ጋ​ጁ​ልን።” በሄ​ዱም ጊዜ እን​ዳ​ላ​ቸው አገኙ፤ የፋ​ሲ​ካ​ው​ንም በግ አዘ​ጋጁ። ሰዓ​ቱም በደ​ረሰ ጊዜ ጌታ​ችን ኢየ​ሱስ በማ​ዕድ ተቀ​መጠ፤ ዐሥራ ሁለቱ ደቀ መዛ​ሙ​ር​ቱም ከእ​ርሱ ጋር ተቀ​መጡ። እር​ሱም እን​ዲህ አላ​ቸው፥ “ከመ​ከ​ራዬ አስ​ቀ​ድሞ ይህን ፋሲካ ከእ​ና​ንተ ጋር ልበላ እጅግ ወደ​ድሁ። ነገር ግን፤ በእ​ግ​ዚ​አ​ብ​ሔር መን​ግ​ሥት እስ​ኪ​ፈ​ጸም ድረስ እን​ግ​ዲህ ከእ​ርሱ እን​ደ​ማ​ል​በላ እነ​ግ​ራ​ች​ኋ​ለሁ” አላ​ቸው። ጽዋ​ው​ንም ተቀ​ብሎ አመ​ሰ​ገነ፤ እን​ዲ​ህም አለ፥ “ይህን እንኩ ሁላ​ች​ሁም ተካ​ፈ​ሉት። እላ​ች​ኋ​ለሁ፥ የእ​ግ​ዚ​አ​ብ​ሔር መን​ግ​ሥት እስ​ክ​ት​መጣ ድረስ፤ እን​ግ​ዲህ ወዲህ ከዚህ የወ​ይን ፍሬ አል​ጠ​ጣም።” ኅብ​ስ​ቱ​ንም አነሣ፤ አመ​ስ​ገነ፤ ፈት​ቶም ሰጣ​ቸው፤ እን​ዲ​ህም አላ​ቸው፥ “ስለ እና​ንተ ቤዛ ሆኖ የሚ​ሰጥ ሥጋዬ ይህ ነው፤ ይህ​ንም ለመ​ታ​ሰ​ቢ​ያዬ አድ​ር​ጉት፤” እን​ዲ​ሁም ከእ​ራት በኋላ ጽዋ​ዉን አን​ሥቶ እን​ዲህ አላ​ቸው፥ “ይህ ጽዋ ስለ እና​ንተ በሚ​ፈ​ስ​ሰው ደሜ የሚ​ሆን አዲስ ኪዳን ነው። “ነገር ግን አሳ​ልፎ የሚ​ሰ​ጠኝ ሰው እጅ እነሆ፥ በማ​ዕድ ከእኔ ጋር ነው። የሰው ልጅስ ስለ እርሱ እንደ ተጻፈ ይሄ​ዳል፤ ነገር ግን የሰው ልጅ በእጁ ለሚ​ሰ​ጥ​በት ለዚያ ሰው ወዮ​ለት።” ደቀ መዛ​ሙ​ር​ቱም ከእ​ነ​ርሱ ይህን የሚ​ያ​ደ​ርግ ማን እንደ ሆነ እርስ በር​ሳ​ቸው ተነ​ጋ​ገሩ። ከዚ​ህም በኋላ ከእ​ነ​ርሱ ማን እን​ደ​ሚ​በ​ልጥ እርስ በር​ሳ​ቸው ተከ​ራ​ከሩ። እር​ሱም እን​ዲህ አላ​ቸው፥ “አሕ​ዛ​ብን ንጉ​ሦ​ቻ​ቸው ይገ​ዙ​አ​ቸ​ዋል፤ በላ​ያ​ቸ​ውም ሥል​ጣን ያላ​ቸው ቸር​ነት አድ​ራ​ጊ​ዎች ይባ​ላሉ። ለእ​ና​ንተ ግን እን​ዲህ አይ​ደ​ለም፤ ነገር ግን ከእ​ና​ንተ ታላቁ እንደ ታናሽ ይሁ​ና​ችሁ፤ አለ​ቃ​ውም እንደ አገ​ል​ጋይ ይሁን። የሚ​በ​ልጥ ማን​ኛው ነው? በማ​ዕድ ላይ የተ​ቀ​መ​ጠው ነው? ወይስ የሚ​ላ​ላ​ከው? በማ​ዕድ ላይ የተ​ቀ​መ​ጠው አይ​ደ​ለ​ምን? እነሆ፥ እኔ በመ​ካ​ከ​ላ​ችሁ እንደ አገ​ል​ጋይ ነኝ። ነገር ግን ስለ እኔ የታ​ገ​ሣ​ችሁ እና​ንተ በመ​ከ​ራዬ ከእኔ ጋር ናችሁ። አባቴ ለእኔ እንደ ሰጠኝ፥ እኔም ለእ​ና​ንተ መን​ግ​ሥ​ትን አዘ​ጋ​ጅ​ላ​ች​ኋ​ለሁ፤ በመ​ን​ግ​ሥቴ በማ​ዕዴ ትበ​ሉና ትጠጡ ዘንድ፥ በወ​ን​በ​ሮ​ችም ተቀ​ም​ጣ​ችሁ በዐ​ሥራ ሁለቱ ነገደ እስ​ራ​ኤል ትፈ​ርዱ ዘንድ።” ጌታ​ችን ኢየ​ሱ​ስም እን​ዲህ አለ፥ “ስም​ዖን፥ ስም​ዖን ሆይ፥ ሰይ​ጣን እንደ አጃ ሊያ​በ​ጥ​ራ​ችሁ አሁን ልመ​ናን ለመነ። እኔ ግን ሃይ​ማ​ኖ​ታ​ችሁ እን​ዳ​ይ​ደ​ክም ስለ እና​ንተ ጸለ​ይሁ፤ አን​ተም ተመ​ል​ሰህ ወን​ድ​ሞ​ች​ህን አጽ​ና​ቸው።” እር​ሱም፥ “አቤቱ፥ እኔ ለመ​ታ​ሰ​ርም ቢሆን፥ ለሞ​ትም ቢሆን እንኳ ከአ​ንተ ጋራ ለመ​ሄድ የተ​ዘ​ጋ​ጀሁ ነኝ” አለው። እርሱ ግን፥ “ጴጥ​ሮስ ሆይ፥ እል​ሃ​ለሁ፥ ዛሬ ዶሮ ሳይ​ጮኽ እን​ደ​ማ​ታ​ው​ቀኝ ሦስት ጊዜ ትክ​ደ​ኛ​ለህ” አለው። ደግ​ሞም፥ “ያለ ስልቻ፥ ያለ ከረ​ጢ​ትና ያለ ጫማ በላ​ክ​ኋ​ችሁ ጊዜ በውኑ የተ​ቸ​ገ​ራ​ች​ሁት ነገር ነበ​ርን?” አላ​ቸው፤ እነ​ር​ሱም፥ “የለም” አሉት። እር​ሱም እን​ዲህ አላ​ቸው፥ “አሁን ግን ኮሮጆ ያለው ኮሮ​ጆ​ውን ይያዝ፤ ከረ​ጢ​ትም ያለው እን​ዲሁ ያድ​ርግ፤ ሰይፍ የሌ​ለ​ውም ልብ​ሱን ሸጦ ሰይፍ ይግዛ። እላ​ች​ኋ​ለሁ፥ ከኃ​ጥ​ኣን ጋር ተቈ​ጠረ ተብሎ የተ​ጻ​ፈው በእኔ ይደ​ር​ሳል፤ ስለ እኔ የተ​ጻ​ፈ​ውም ሁሉ ይፈ​ጸ​ማል።” እነ​ር​ሱም፥ “አቤቱ፥ እነሆ፥ እዚህ በእኛ ዘንድ ሁለት ሰይ​ፎች አሉ” አሉት፤ እር​ሱም፥ “እን​ግ​ዲ​ያስ ይበ​ቃ​ች​ኋል” አላ​ቸው።

ሉቃስ 22:1-38 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)

ፋሲካ የተባለው የቂጣ በዓል የሚከበርበት ቀን ተቃርቦ ነበር፤ የካህናት አለቆችና የሕግ መምህራን ሕዝቡን ስለ ፈሩ ኢየሱስን ይዘው የሚገድሉበትን ዘዴ በስውር ይፈልጉ ነበር። በዚያን ጊዜ ከዐሥራ ሁለቱ ሐዋርያት አንዱ በሆነው በአስቆሮታዊው ይሁዳ ሰይጣን ገባበት። ስለዚህ ይሁዳ ወደ ካህናት አለቆችና ወደ ቤተ መቅደስ ዘብ አዛዦች ሄዶ ኢየሱስን እንዴት አሳልፎ እንደሚሰጣቸው ከእነርሱ ጋር ተነጋገረ። እነርሱም በነገሩ ተደስተው ገንዘብ ሊሰጡት ተዋዋሉ። በውሉ ተስማምቶ ሕዝቡ ሳያውቅ ኢየሱስን አሳልፎ ለመስጠት ምቹ ጊዜ ይፈልግ ነበር። ከዚህ በኋላ የፋሲካ በግ የሚታረድበት የቂጣ በዓል ደረሰ። ኢየሱስ “የፋሲካውን ራት እንድንበላ ሄዳችሁ አዘጋጁልን” ሲል ጴጥሮስንና ዮሐንስን ላካቸው። እነርሱም “የፋሲካውን ራት የት እንድናዘጋጅ ትፈልጋለህ?” ሲሉ ጠየቁት። እርሱም እንዲህ አላቸው፦ “ወደ ከተማ ስትገቡ እነሆ፥ የውሃ እንስራ የተሸከመ ሰው ታገኛላችሁ፤ እርሱን ተከትላችሁ ወደሚገባበት ቤት ሂዱ። የቤቱንም ጌታ መምህራችን፥ ‘ከደቀ መዛሙርቴ ጋር የፋሲካን ራት የምበላበት የእንግዳ ማረፊያ ቤት የት ነው? ይልሃል’ በሉት። እርሱም በሰገነት ላይ ያለውን ተነጥፎ የተዘጋጀ ሰፊ አዳራሽ ያሳያችኋል፤ በዚያ አዘጋጁ።” ሁለቱ ደቀ መዛሙርትም ሄደው፥ ሁሉ ነገር ልክ ኢየሱስ እንዳላቸው ሆኖ አገኙ፤ የፋሲካውንም ራት በዚያ አዘጋጁ። የእራት ሰዓት በደረሰ ጊዜ ኢየሱስ ከሐዋርያት ጋር በማእድ ተቀመጠ። እንዲህም አላቸው፤ “መከራ ከመቀበሌ በፊት ከእናንተ ጋር ይህን የፋሲካ ራት ለመብላት እጅግ እመኝ ነበር፤ የዚህ ነገር እውነተኛ ምሥጢር በእግዚአብሔር መንግሥት ፍጹም ሆኖ እስኪገለጥ ድረስ ከእንግዲህ ወዲህ ይህን የፋሲካ ራት ከቶ አልበላም እላችኋለሁ።” ከዚህ በኋላ ኢየሱስ ጽዋውን አንሥቶ ከአመሰገነ በኋላ እንዲህ አለ፦ “እንካችሁ ይህንን ተካፈሉ፤ በእውነት እላችኋለሁ ከአሁን ጀምሮ የእግዚአብሔር መንግሥት እስክትመጣ ድረስ ከዚህ ከወይን ፍሬ የሚገኘውን መጠጥ አልጠጣም።” ቀጥሎም ኢየሱስ ኅብስት አንሥቶ ከአመሰገነ በኋላ፤ ቈርሶ ለደቀ መዛሙርቱ “እንካችሁ፤ ይህ ለእናንተ የሚሰጥ ሥጋዬ ነው፤ ይህን ለመታሰቢያዬ አድርጉት” ብሎ ሰጣቸው። እንዲሁም ከእራት በኋላ ጽዋውን አንሥቶ ሰጣቸውና እንዲህ አላቸው፤ “ይህ ጽዋ ስለ እናንተ በሚፈሰው ደሜ የሚፈጸም አዲስ ኪዳን ነው። “ነገር ግን አሳልፎ የሚሰጠኝ ሰው እጅ እነሆ፥ ከእኔ ጋር በማእድ ነው። የሰው ልጅ ስለ እርሱ አስቀድሞ በተወሰነው መሠረት ይሞታል፤ ነገር ግን የሰውን ልጅ አሳልፎ ለሚሰጠው ለዚያ ሰው ወዮለት!” እነርሱም “ከእኛ መካከል ይህን ነገር የሚያደርግ የትኛው ነው?” በማለት እርስ በርሳቸው ተጠያየቁ። ቀጥሎም እነርሱ፥ “ከሁላችን የሚበልጥ ማን ነው?” እያሉ እርስ በርሳቸው ይከራከሩ ጀመር። ኢየሱስ ግን እንዲህ አላቸው፤ “የዚህ ዓለም ነገሥታት በሕዝቡ ላይ ሥልጣን አላቸው፤ ገዢዎችም የሕዝቡ በጎ አድራጊዎች ይባላሉ፤ እናንተ ግን እንደ እነርሱ ልትሆኑ አይገባም፤ ይልቅስ ከእናንተ መካከል ትልቅ የሆነ እንደ ትንሽ ይሁን፤ አለቃ የሆነም እንደ አገልጋይ ይሁን። በማእድ ተቀምጦ ከሚመገበውና ቆሞ ከሚያገለግለው የትኛው ነው ትልቅ? ትልቅ የሚባለው በማእድ የተቀመጠው አይደለምን? እኔ ግን በመካከላችሁ እንደ አገልጋይ ነኝ። እናንተ በመከራዬ ጊዜ ሁሉ ከእኔ ጋር ጸንታችሁ ቈይታችኋል። ስለዚህ አባቴ እኔን እንደ ሾመኝ እኔም እናንተን እሾማችኋለሁ። በመንግሥቴም በማእድ ተቀምጣችሁ ትበላላችሁ፤ ትጠጣላችሁ፤ በዙፋን ላይ ተቀምጣችሁ በዐሥራ ሁለቱም የእስራኤል ነገዶች ላይ ትፈርዳላችሁ።” ቀጥሎም ኢየሱስ እንዲህ አለ፦ “ስምዖን! ስምዖን! እነሆ፥ ገበሬ ስንዴውን ከገለባ አበጥሮ እንደሚለይ እንዲሁም ሰይጣን እናንተን ሊያበጥራችሁ ፈለገ። ነገር ግን የአንተ እምነት እንዳይጠፋ እኔ ለአንተ እጸልያለሁ፤ እንደገና በተመለስህ ጊዜ ወንድሞችህን አጽና።” ጴጥሮስም “ጌታ ሆይ! ለእስራትም ሆነ ለሞት ከአንተ ጋር አብሬ ለመሄድ ዝግጁ ነኝ!” አለ። ኢየሱስ ግን “ጴጥሮስ ሆይ! ዛሬ ዶሮ ሳይጮኽ ‘አላውቀውም’ ብለህ ሦስት ጊዜ ትክደኛለህ እልሃለሁ” አለው። ከዚህ በኋላ ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱን፦ “የገንዘብ ቦርሳ፥ ከረጢት፥ ጫማም ሳትይዙ በላክኋችሁ ጊዜ የጐደለባችሁ ነገር ነበርን?” አላቸው። እነርሱም “ምንም የጐደለብን ነገር አልነበረም” ሲሉ መለሱለት። ኢየሱስም እንዲህ አላቸው፤ “አሁን ግን የገንዘብ ቦርሳም ሆነ ከረጢት ያለው ይያዝ፤ ሰይፍም የሌለው ልብሱን ሸጦ ሰይፍ ይግዛ። ስለ እኔ አስቀድሞ የተጻፈው ሁሉ መፈጸም ስለሚገባው ‘ከዐመፀኞች ጋር ተቈጠረ’ የሚለው የቅዱስ መጽሐፍ ቃል በእኔ ላይ መፈጸም አለበት እላችኋለሁ።” ደቀ መዛሙርቱም “ጌታ ሆይ! እነሆ፥ እዚህ ሁለት ሰይፎች አሉ!” አሉት። እርሱም “ይበቃል!” አላቸው።

ሉቃስ 22:1-38 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)

ፋሲካም ተብሎ የሚጠራው የቂጣ በዓል ቀረበ። የካህናት አለቆችና ጻፎች እርሱን የሚገድሉበትን መንገድ ይፈልጉ ነበር፤ ሕዝቡን ይፈሩ ነበርና። ሰይጣንም ከዐሥራ ሁለቱ መካከል አንዱ በነበረውና የአስቆሮቱ በሚባለው በይሁዳ ውስጥ ገባ፤ ሄዶም እንዴት አሳልፎ እንደሚሰጣቸው ከካህናት አለቆችና ከቤተ መቅደስ አዛዦች ጋር ተነጋገረ። እነርሱም ደስ አላቸው፤ ገንዘብም ሊሰጡት ተዋዋሉ። እሺም አለ፤ ሕዝብም ባልተገኘበት ጊዜ አሳልፎ ሊሰጣቸው ምቹ ጊዜ ይፈልግ ነበር። የፋሲካም በግ የሚታረድበት የቂጣ በዓል ደረሰ፤ ጴጥሮስንና ዮሐንስንም “ፋሲካን እንድንበላ ሄዳችሁ አዘጋጁልን፤” ብሎ ላካቸው። እነርሱም “የት እንድናዘጋጅ ትፈልጋለህ?” አሉት። እርሱም አላቸው “እነሆ፥ ወደ ከተማ ስትገቡ የውሃ እንስራ የተሸከመ ሰው ይገናኛችኋል፤ ወደሚገባበት ቤት ተከተሉት፤ ለባለቤቱም ‘መምህሩ ከደቀ መዛሙርቴ ጋር ፋሲካን የምበላበት የእንግዳ ቤት ክፍል የት ነው?’ ይልሃል በሉት፤ እርሱም በሰገነት ላይ የተነጠፈውን ታላቅ አዳራሽ ያሳያችኋል፤ በዚያም አሰናዱልን።” ሄደውም እንዳላቸው አገኙና ፋሲካን አሰናዱ። ሰዓቱም በደረሰ ጊዜ ከዐሥራ ሁለቱ ሐዋርያት ጋር በማዕድ ተቀመጠ። እርሱም “ከመከራዬ በፊት ይህን ፋሲካ ከእናንተ ጋር ልበላ እጅግ እመኝ ነበር፤ በእግዚአብሔር መንግሥት እስኪፈጸም ድረስ፥ ወደ ፊት ከዚህ አልበላም እላችኋለሁና፤” አላቸው። ጽዋንም ተቀበሎ፥ አመስግኖም “እንካችሁ፤ ይህን በመካከላችሁ ተካፈሉት፤ የእግዚአብሔር መንግሥት እስክትመጣ ድረስ ከአሁን ጀምሮ ከወይኑ ፍሬ አልጠጣም እላችኋለሁና” አለ። ኅብስትንም አንሥቶ፥ አመስግኖ፥ ቆረሰና እንዲህ ሲል ሰጣቸው፦ “ይህ ስለ እናንተ የሚሰጠው ሥጋዬ ነው፤ ይህን ለመታሰቢያዬ አድርጉት”። እንዲሁም ከእራት በኋላ ጽዋውን አንሥቶ እንዲህ አለ “ይህ ጽዋ ስለ እናንተ በሚፈሰው በደሜ የሚሆን አዲስ ኪዳን ነው። ነገር ግን አሳልፎ የሚሰጠኝ ሰው እጅ እነሆ በማዕድ ከእኔ ጋር ናት። የሰው ልጅስ በተወሰነው መሠረት ይሄዳል፤ ነገር ግን አሳልፎ ለሚሰጠው ሰው ወዮለት።” እነርሱም ከነሱ መሀል ይህንን የሚያደርገው ማን እንደሆነ ለማወቅ እርስ በርሳቸው ይጠያየቁ ጀመር። ደግሞም ከእነሱ መሀል ማን እንደሚበልጥ ለማወቅ ክርክር ተነሣ። እንዲህም አላቸው አሕዛብን ንጉሦቻቸው ይገዙአቸዋል፤ በላያቸውም ሥልጣን ያላቸው በጎ አድራጊዎች ይባላሉ። እናንተ ግን እንዲህ አትሁኑ፤ ነገር ግን ከእናንተ ታላቅ የሆነ በእናንተ መሀል እንደ ታናሽ፥ ሥልጣን ያለውም እንደሚያገለግል ይሁን። ለመሆኑ ማነው ታላቅ? በማዕድ የተቀመጠ ወይስ የሚያገለግል? የተቀመጠው አይደለምን? እኔ ግን በእናንተ መሀል እንደሚያገለግል ነኝ። እናንተ በመከራዬ ከእኔ ጋር ጸንታችሁ የኖራችሁ ናችሁ፤ አባቴ እኔን እንደ ሾመኝ እኔ ደግሞ ለመንግሥት እሾማችኋላሁ፤ በመንግሥቴም ከእኔ ማዕድ ትበላላአችሁ፥ እንዲሁም ትጠጣላችሁ፤ በዐሥራ ሁለቱ የእስራኤል ነገዶች ላይም ለመፍረድ በዙፋኖች ላይ ትቀመጣላችሁ። ጌታም “ስምዖን ስምዖን ሆይ! እነሆ፥ ሰይጣን እንደ ስንዴ ሊያበጥራችሁ ለመነ፤ እኔ ግን እምነትህ እንዳይጠፋ ስለ አንተ ጸለይሁ፤ አንተም በተመለስህ ጊዜ ወንድሞችህን አጽና፤” አለ። እርሱም “ጌታ ሆይ! ወደ ወኅኒም ሆነ ወደ ሞት ከአንተ ጋር ለመሄድ ዝግጁ ነኝ፤” አለው። እርሱ ግን “ጴጥሮስ ሆይ! ዛሬ ዶሮ ሳይጮኽ፥ ‘አላውቅህም’ እያልህ ሦስት ጊዜ ትክደኛለህ እልሃለሁ” አለው። ከዚያም፥ “ያለ ቦርሳና ያለ ከረጢት፥ ያለ ጫማም በላክኋችሁ ጊዜ፥ የጐደለባችሁ ነገር ነበርን?” አላቸው። እነርሱም “ምንም” አሉ። እርሱም “አሁን ግን ቦርሳ ያለው ይያዘው፤ ከረጢትም ያለው እንዲሁ፤ የሌለውም ልብሱን ሽጦ ሰይፍ ይግዛ። ይህ ‘ከዓመፀኞች ጋር ተቈጠረ፤’ ተብሎ የተጻፈው በእኔ ላይ የግድ መፈጸም አለበት እላችኋልለሁ፤ አዎን፤ ስለ እኔ የተባለው አሁን ይፈጸማልና፤” አላቸው። እነርሱም “ጌታ ሆይ! እነሆ፥ በዚህ ሁለት ሰይፎች አሉ፤” አሉት። እርሱም “ይበቃል፤” አላቸው።