ፋሲካም የሚባለው የቂጣ በዓል ቀረበ። የካህናት አለቆችና ጻፎችም ሊገድሉት ይሹ ነበር፤ ነገር ግን ሕዝቡን ይፈሩአቸው ነበር። ቍጥሩ ከዐሥራ ሁለቱ በነበረው በአስቆሮቱ ይሁዳ ልብ ሰይጣን አደረ። ሄዶም ከካህናት አለቆችና ከታላላቆች ጋር እርሱን አሳልፎ እንዲሰጣቸው ተነጋገረ። ደስ ብሏቸውም ሠላሳ ብር ሊሰጡት ተስማሙ። እርሱም እሺ አለ፤ ሰው ሳይኖርም እርሱን አሳልፎ ሊሰጣቸው ምቹ ጊዜ ይሻ ነበር። የፋሲካን በግ የሚያርዱባት የቂጣ በዓልም ደረሰች። ጌታችን ኢየሱስም ጴጥሮስንና ዮሐንስን፥ “ሂዱና የምንበላውን የፋሲካ በግ አዘጋጁልን” አላቸው። እነርሱም፥ “ወዴት ልናዘጋጅልህ ትወዳለህ?” አሉት። እንዲህም አላቸው፥ “ወደ ከተማ በገባችሁ ጊዜ፥ የውኃ ማድጋ የተሸከመ ሰው ታገኛላችሁ፤ ወደሚገባበትም ቤት እርሱን ተከተሉት። የዚያን ቤት ጌታ፦ መምህር ከደቀ መዛሙርቴ ጋር የፋሲካን በግ የምበላበት ቤት ወዴት ነው? ብሎሃል በሉት። እርሱም በሰገነት ላይ የተነጠፈ ታላቅ አዳራሽ ያሳያችኋል፤ በዚያ አዘጋጁልን።” በሄዱም ጊዜ እንዳላቸው አገኙ፤ የፋሲካውንም በግ አዘጋጁ። ሰዓቱም በደረሰ ጊዜ ጌታችን ኢየሱስ በማዕድ ተቀመጠ፤ ዐሥራ ሁለቱ ደቀ መዛሙርቱም ከእርሱ ጋር ተቀመጡ። እርሱም እንዲህ አላቸው፥ “ከመከራዬ አስቀድሞ ይህን ፋሲካ ከእናንተ ጋር ልበላ እጅግ ወደድሁ። ነገር ግን፤ በእግዚአብሔር መንግሥት እስኪፈጸም ድረስ እንግዲህ ከእርሱ እንደማልበላ እነግራችኋለሁ” አላቸው። ጽዋውንም ተቀብሎ አመሰገነ፤ እንዲህም አለ፥ “ይህን እንኩ ሁላችሁም ተካፈሉት። እላችኋለሁ፥ የእግዚአብሔር መንግሥት እስክትመጣ ድረስ፤ እንግዲህ ወዲህ ከዚህ የወይን ፍሬ አልጠጣም።” ኅብስቱንም አነሣ፤ አመስገነ፤ ፈትቶም ሰጣቸው፤ እንዲህም አላቸው፥ “ስለ እናንተ ቤዛ ሆኖ የሚሰጥ ሥጋዬ ይህ ነው፤ ይህንም ለመታሰቢያዬ አድርጉት፤” እንዲሁም ከእራት በኋላ ጽዋዉን አንሥቶ እንዲህ አላቸው፥ “ይህ ጽዋ ስለ እናንተ በሚፈስሰው ደሜ የሚሆን አዲስ ኪዳን ነው። “ነገር ግን አሳልፎ የሚሰጠኝ ሰው እጅ እነሆ፥ በማዕድ ከእኔ ጋር ነው። የሰው ልጅስ ስለ እርሱ እንደ ተጻፈ ይሄዳል፤ ነገር ግን የሰው ልጅ በእጁ ለሚሰጥበት ለዚያ ሰው ወዮለት።” ደቀ መዛሙርቱም ከእነርሱ ይህን የሚያደርግ ማን እንደ ሆነ እርስ በርሳቸው ተነጋገሩ። ከዚህም በኋላ ከእነርሱ ማን እንደሚበልጥ እርስ በርሳቸው ተከራከሩ። እርሱም እንዲህ አላቸው፥ “አሕዛብን ንጉሦቻቸው ይገዙአቸዋል፤ በላያቸውም ሥልጣን ያላቸው ቸርነት አድራጊዎች ይባላሉ። ለእናንተ ግን እንዲህ አይደለም፤ ነገር ግን ከእናንተ ታላቁ እንደ ታናሽ ይሁናችሁ፤ አለቃውም እንደ አገልጋይ ይሁን። የሚበልጥ ማንኛው ነው? በማዕድ ላይ የተቀመጠው ነው? ወይስ የሚላላከው? በማዕድ ላይ የተቀመጠው አይደለምን? እነሆ፥ እኔ በመካከላችሁ እንደ አገልጋይ ነኝ። ነገር ግን ስለ እኔ የታገሣችሁ እናንተ በመከራዬ ከእኔ ጋር ናችሁ። አባቴ ለእኔ እንደ ሰጠኝ፥ እኔም ለእናንተ መንግሥትን አዘጋጅላችኋለሁ፤ በመንግሥቴ በማዕዴ ትበሉና ትጠጡ ዘንድ፥ በወንበሮችም ተቀምጣችሁ በዐሥራ ሁለቱ ነገደ እስራኤል ትፈርዱ ዘንድ።” ጌታችን ኢየሱስም እንዲህ አለ፥ “ስምዖን፥ ስምዖን ሆይ፥ ሰይጣን እንደ አጃ ሊያበጥራችሁ አሁን ልመናን ለመነ። እኔ ግን ሃይማኖታችሁ እንዳይደክም ስለ እናንተ ጸለይሁ፤ አንተም ተመልሰህ ወንድሞችህን አጽናቸው።” እርሱም፥ “አቤቱ፥ እኔ ለመታሰርም ቢሆን፥ ለሞትም ቢሆን እንኳ ከአንተ ጋራ ለመሄድ የተዘጋጀሁ ነኝ” አለው። እርሱ ግን፥ “ጴጥሮስ ሆይ፥ እልሃለሁ፥ ዛሬ ዶሮ ሳይጮኽ እንደማታውቀኝ ሦስት ጊዜ ትክደኛለህ” አለው። ደግሞም፥ “ያለ ስልቻ፥ ያለ ከረጢትና ያለ ጫማ በላክኋችሁ ጊዜ በውኑ የተቸገራችሁት ነገር ነበርን?” አላቸው፤ እነርሱም፥ “የለም” አሉት። እርሱም እንዲህ አላቸው፥ “አሁን ግን ኮሮጆ ያለው ኮሮጆውን ይያዝ፤ ከረጢትም ያለው እንዲሁ ያድርግ፤ ሰይፍ የሌለውም ልብሱን ሸጦ ሰይፍ ይግዛ። እላችኋለሁ፥ ከኃጥኣን ጋር ተቈጠረ ተብሎ የተጻፈው በእኔ ይደርሳል፤ ስለ እኔ የተጻፈውም ሁሉ ይፈጸማል።” እነርሱም፥ “አቤቱ፥ እነሆ፥ እዚህ በእኛ ዘንድ ሁለት ሰይፎች አሉ” አሉት፤ እርሱም፥ “እንግዲያስ ይበቃችኋል” አላቸው።
የሉቃስ ወንጌል 22 ያንብቡ
ያዳምጡ የሉቃስ ወንጌል 22
Share
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: የሉቃስ ወንጌል 22:1-38
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
Home
Bible
Plans
Videos