የኃጢአትንም መሥዋዕት ወይፈን አቀረበ፤ አሮንና ልጆቹም በኃጢአቱ መሥዋዕት ወይፈን ራስ ላይ እጆቻቸውን ጫኑ። አረደውም፤ ሙሴም ደሙን ወስዶ በጣቱ የመሠዊያውን ቀንዶች ዙሪያ ቀባ፥ መሠዊያውንም አነጻው፤ ደሙንም ከመሠዊያው በታች አፈሰሰው፥ ያስተሰርይለትም ዘንድ ቀደሰው። በሆድ ዕቃውም ላይ ያለውን ስብ ሁሉ፥ ጕበቱንም መረብ፥ ሁለቱንም ኩላሊቶች ስባቸውንም ወሰደ፤ ሙሴም በመሠዊያው ላይ አቃጠለው። እግዚአብሔርም ሙሴን እንዳዘዘው ወይፈኑን፥ ቍርበቱንም፥ ሥጋውንም፥ ፈርሱንም ከሰፈሩ ውጭ በእሳት አቃጠለ። ለሚቃጠል መሥዋዕትም የሚሆን አውራ በግ አቀረበ፤ አሮንና ልጆቹም በአውራው በግ ራስ ላይ እጆቻቸውን ጫኑ። አረደውም፤ ሙሴም ደሙን በመሠዊያው ዙሪያ ረጨው። አውራውንም በግ በየብልቱ ቈረጠ፤ ሙሴም ጭንቅላቱን ብልቶቹንም ስቡንም አቃጠለ። የሆድ ዕቃውንና እግሮቹንም በውኃ አጠበ፤ ሙሴም አውራውን በግ ሁሉ በመሠዊያው ላይ አቃጠለው፤ ይህ ጣፋጭ ሽታ እንዲሆን የሚቃጠል መሥዋዕት ነበረ፤ እግዚአብሔር ሙሴን እንዳዘዘው ለእግዚአብሔር የእሳት ቍርባን ነበረ። ለቅድስናም የሚሆነውን ሁለተኛውን አውራ በግ አቀረበ፤ አሮንና ልጆቹም በአውራው በግ ራስ ላይ እጆቻቸውን ጫኑ። አረደውም፤ ሙሴን ከደሙ ወስዶ የአሮንን የቀኝ ጆሮውን ጫፍ፥ የቀኝ እጁንም አውራ ጣት የቀኝ እግሩንም አውራ ጣት አስነካው። የአሮንንም ልጆች አቀረበ፤ ሙሴም የቀኝ ጆሮአቸውን ጫፍ፥ የቀን እጃቸውንም አውራ ጣት፥ የቀኝ እግራቸውንም አውራ ጣት ከደሙ አስነካ፤ ሙሴም ደሙን በመሠዊያው ዙሪያ ረጨ።
ኦሪት ዘሌዋውያን 8 ያንብቡ
ያጋሩ
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: ኦሪት ዘሌዋውያን 8:14-24
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
ቤት
መጽሐፍ ቅዱስ
እቅዶች
ቪዲዮዎች