ኦሪት ዘሌዋውያን 8
8
1እግዚአብሔርም ሙሴን እንዲህ ብሎ ተናገረው፦ 2አሮንን፥ ከእርሱም ጋር ልጆቹን፥ ልብሱንም፥ የቅብዓቱንም ዘይት፥ ለኃጢአት መሥዋዕትም የሆነውን ወይፈን፥ ሁለቱንም አውራ በጎች፥ የቂጣውንም እንጀራ ሌማት ውሰድ፤ 3ማኅበሩንም ሁሉ ወደ መገናኛው ድንኳን ደጃፍ ሰብስባቸው። 4ሙሴም እግዚአብሔር እንዳዘዘው አደረገ፤ ማኅበሩ ሁሉ ወደ መገናኛው ድንኳን ደጃፍ ተሰበሰቡ። 5ሙሴም ማኅበሩን፦ እግዚአብሔር ይደረግ ዘንድ ያዘዘው ነገር ይህ ነው አላቸው። 6ሙሴም አሮንንና ልጆቹን አቀረበ፥ በውኃም አጠባቸው። 7ሸሚዝም አለበሰው፥ በመታጠቂያም አስታጠቀው፥ ቀሚስም አለበሰው፥ ኤፉድም ደረበለት፥ በብልሃትም በተጠለፈ ቍድ አስታጠቀውና በእርሱ ላይ አሰረው። 8የደረት ኪስ በእርሱ ላይ አደረገ፤ በደረቱ ኪስም ውስጥ ኡሪምንና ቱሚምን አኖረበት። 9እግዚአብሔርም ሙሴን እንዳዘዘው በራሱ ላይ መጠምጠሚያውን አደረገ፤ በመጠምጠሚያውም ላይ በፊቱ በኩል የተቀደሰውን አክሊል፥ ቅጠል የሚመስለውን የወርቅ ምልክት፥ አደረገ። 10ሙሴም የቅብዓቱን ዘይት ወሰደ፥ ማደሪያውንና በውስጡ ያለውን ሁሉ ቀብቶ ቀደሳቸው። 11ከእርሱም በመሠዊያው ላይ ሰባት ጊዜ ረጨ፤ ይቀድሳቸውም ዘንድ መሠዊያውንና ዕቃውን ሁሉ፥ የመታጠቢያውን ሰንና መቀመጫውን ቀባ። 12ከቅብዓቱም ዘይት በአሮን ራስ ላይ አፈሰሰ፥ ይቀድሰውም ዘንድ ቀባው። 13እግዚአብሔርም ሙሴን እንዳዘዘው ሙሴ የአሮንን ልጆች አቀረበ፥ ቀሚሶችንም አለበሳቸው፥ በመታጠቂያም አስታጠቃቸው፥ ቆብም ደፋባቸው። 14የኃጢአትንም መሥዋዕት ወይፈን አቀረበ፤ አሮንና ልጆቹም በኃጢአቱ መሥዋዕት ወይፈን ራስ ላይ እጆቻቸውን ጫኑ። 15አረደውም፤ ሙሴም ደሙን ወስዶ በጣቱ የመሠዊያውን ቀንዶች ዙሪያ ቀባ፥ መሠዊያውንም አነጻው፤ ደሙንም ከመሠዊያው በታች አፈሰሰው፥ ያስተሰርይለትም ዘንድ ቀደሰው። 16በሆድ ዕቃውም ላይ ያለውን ስብ ሁሉ፥ ጕበቱንም መረብ፥ ሁለቱንም ኩላሊቶች ስባቸውንም ወሰደ፤ ሙሴም በመሠዊያው ላይ አቃጠለው። 17እግዚአብሔርም ሙሴን እንዳዘዘው ወይፈኑን፥ ቍርበቱንም፥ ሥጋውንም፥ ፈርሱንም ከሰፈሩ ውጭ በእሳት አቃጠለ። 18ለሚቃጠል መሥዋዕትም የሚሆን አውራ በግ አቀረበ፤ አሮንና ልጆቹም በአውራው በግ ራስ ላይ እጆቻቸውን ጫኑ። 19አረደውም፤ ሙሴም ደሙን በመሠዊያው ዙሪያ ረጨው። 20አውራውንም በግ በየብልቱ ቈረጠ፤ ሙሴም ጭንቅላቱን ብልቶቹንም ስቡንም አቃጠለ። 21የሆድ ዕቃውንና እግሮቹንም በውኃ አጠበ፤ ሙሴም አውራውን በግ ሁሉ በመሠዊያው ላይ አቃጠለው፤ ይህ ጣፋጭ ሽታ እንዲሆን የሚቃጠል መሥዋዕት ነበረ፤ እግዚአብሔር ሙሴን እንዳዘዘው ለእግዚአብሔር የእሳት ቍርባን ነበረ። 22ለቅድስናም የሚሆነውን ሁለተኛውን አውራ በግ አቀረበ፤ አሮንና ልጆቹም በአውራው በግ ራስ ላይ እጆቻቸውን ጫኑ። 23አረደውም፤ ሙሴን ከደሙ ወስዶ የአሮንን የቀኝ ጆሮውን ጫፍ፥ የቀኝ እጁንም አውራ ጣት የቀኝ እግሩንም አውራ ጣት አስነካው። 24የአሮንንም ልጆች አቀረበ፤ ሙሴም የቀኝ ጆሮአቸውን ጫፍ፥ የቀን እጃቸውንም አውራ ጣት፥ የቀኝ እግራቸውንም አውራ ጣት ከደሙ አስነካ፤ ሙሴም ደሙን በመሠዊያው ዙሪያ ረጨ። 25ስቡንና ላቱን፥ በሆድ ዕቃውም ላይ ያለውን ስብ ሁሉ፥ የጕበቱንም መረብ፥ ሁለቱንም ኵላሊቶች ስባቸውንም፥ ቀኝ ወርቹንም ወሰደ፤ 26በእግዚአብሔር ፊት ካለው ከቂጣው እንጀራ ሌማት አንድ የቂጣ እንጐቻ፥ አንድም የዘይት እንጀራ፥ አንድም ስስ ቂጣ ወስዶ በስቡና በቀኝ ወርቹ ላይ አኖራቸው። 27ሁሉንም በአሮንና በልጆቹ እጆች ላይ አደረገ፥ በእግዚአብሔርም ፊት ለመወዝወዝ ቍርባን ወዘወዛቸው። 28ሙሴም ከእጃቸው ተቀብሎ በመሠዊያው በሚቃጥለው መሥዋዕት ላይ አቃጠለው፤ የጣፋጭ ሽታ መቀደሻ ነበረ። እርሱም ለእግዚአብሔር የእሳት ቍርባን ነበረ። 29ሙሴም ፍርምባውን ወስዶ በእግዚአብሔር ፊት ለመወዝወዝ ቍርባን ወዘወዘው፤ እግዚአብሔር ሙሴን እንዳዘዘው ይህ ለቅድስና ከታረደው አውራ በግ የሙሴ እድል ፈንታ ሆነ። 30ሙሴም ከቅብዓቱ ዘይትና በመሠዊያው ላይ ካለው ከደሙ ወስዶ በአሮንና በልብሱ ላይ፥ በልጆቹና በልጆቹ ልብስ ላይ ረጨው፤ አሮንንና ልብሱንም፥ ልጆቹንም፥ የልጆቹንም ልብስ ቀደሰ። 31ሙሴም አሮንንና ልጆቹን አላቸው፦ ሥጋውን በመገናኛው ድንኳን ደጃፍ ቀቅሉ፤ አሮንና ልጆቹ ይበሉታል ብዬ እንዳዘዝሁ በዚያ እርሱንና በሌማቱ ያለውን የቅድስናውን እንጀራ ብሉ። 32ከሥጋውና ከእንጀራውም የተረፈውን በእሳት ታቃጥሉታላችሁ። 33ሰባት ቀን ይክናችኋልና የክህነታችሁ ቀን እስኪፈጸም ድረስ ሰባት ቀን ከማኅበሩ ድንኳን ደጃፍ አትውጡ። 34በዚህ ቀን እንደ ተደረገ ለእናንተ ለማስተስረያ ይደረግ ዘንድ እንዲሁ እግዚአብሔር አዘዘ። 35እግዚአብሔር እንዲሁ አዝዞኛልና እንዳትሞቱ በመገናኛው ድንኳን ደጃፍ ሌሊቱንና ቀኑን ሰባት ቀን ተቀመጡ፥ የእግዚአብሔርንም ሥርዓት ጠብቁ። 36አሮንና ልጆቹም እግዚአብሔር በሙሴ እጅ ያዘዘውን ሁሉ አደረጉ።
Currently Selected:
ኦሪት ዘሌዋውያን 8: አማ54
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ