ኦሪት ዘሌዋውያን 9
9
1በስምንተኛውም ቀን እንዲህ ሆነ፤ ሙሴ አሮንንና ልጆቹን የእስራኤልንም ሽማግሌዎች ጠራ። 2አሮንንም አለው፦ ስለ ኃጢአት መሥዋዕት ከመንጋው እምቦሳውን፥ ስለሚቃጠልም መሥዋዕት አውራውን በግ ነውር የሌለባቸውን ወስደህ በእግዚአብሔር ፊት አቅርባቸው። 3-4የእስራኤልንም ልጆች፦ ዛሬ እግዚአብሔር ይገለጥላችኋልና ለኃጢአት መሥዋዕት አውራ ፍየልን፥ ለሚቃጠልም መሥዋዕት ነውር የሌለባቸውን አንድ ዓመት የሆናቸውን እምቦሳና ጠቦትን፥ ለደኅንነትም መሥዋዕት በሬንና አውራን በግ፥ በዘይትም የተለወሰ የእህልን ቍርባን በእግዚአብሔር ፊት ይሠዉ ዘንድ ውሰዱ ብለህ ንገራቸው። 5ሙሴም ያዘዛቸውን ወደ መገናኛው ድንኳን ደጃፍ አመጡ፤ ማኅበሩም ሁሉ ቀርበው በእግዚአብሔር ፊት ቆሙ። 6ሙሴም፦ ታደርጉት ዘንድ እግዚአብሔር ያዘዘው ይህ ነው፤ የእግዚአብሔርም ክብር ይገለጥላችኋል አለ። 7ሙሴም አሮንን፦ ወደ መሠዊያው ቀርበህ የኃጢአትህን መሥዋዕትና የሚቃጠለውን መሥዋዕትህን ሠዋ፥ ለራስህና ለሕዝቡም አስተስርይ፤ እግዚአብሔርም እንዳዘዘ የሕዝቡን ቍርባን አቅርብ አስተስርይላቸውም አለው። 8አሮንም ወደ መሠዊያው ቀርቦ ስለ ራሱ ኃጢአት መሥዋዕት የሆነውን እምቦሳ አረደ። 9የአሮንም ልጆች ደሙን አቀረቡለት፤ ጣቱንም በደሙ ውስጥ ነክሮ የመሠዊያውን ቀንዶች አስነካ፥ ደሙንም ከመሠዊያው በታች አፈሰሰው። 10እግዚአብሔርም ሙሴን እንዳዘዘው ከኃጢአቱ መሥዋዕት ስቡንና ኵላሊቶቹን፥ የጕበቱንም መረብ በመሠዊያው ላይ አቃጠለ። 11ሥጋውንና ቁርበቱንም ከሰፈሩ ውጭ በእሳት አቃጠለ። 12የሚቃጠለውንም መሥዋዕት አረደ፤ የአሮንም ልጆች ደሙን አመጡለት፥ እርሱም በመሠዊያው ላይ በዙሪያው ረጨው። 13የሚቃጠለውንም መሥዋዕት በየብልቱ፥ ራሱንም አመጡለት፤ እርሱም በመሠዊያው ላይ አቃጠለው። 14የሆድ ዕቃውንና እግሮቹንም አጠበ፤ በመሠዊያውም በሚቃጠለው መሥዋዕት ላይ አቃጠለው። 15የሕዝቡንም ቍርባን አቀረበ፤ ስለ ሕዝቡ ለኃጢአት መሥዋዕት የሆነውን ፍየል ወስዶ አረደው፥ ስለ ኃጢአትም እንደ ፊተኛው ሠዋው። 16የሚቃጠለውንም መሥዋዕት አቀረበ፥ እንደ ሥርዓቱም አደረገው። 17የእህሉንም ቍርባን አቀረበ፥ ከእርሱም እፍኝ ሙሉ ወስዶ በጥዋት ከሚቃጠለው መሥዋዕት ሌላ በመሰዊያው ላይ አቃጠለው። 18ስለ ሕዝቡ የሆነውን የደኅንነት መሥዋዕት በሬውንና አውራውን በግ አረደ፤ የአሮንም ልጆች ደሙን አመጡለት፥ በመሠዊያውም ላይ በዙሪያው ረጨው፤ 19የበሬውንና የአውራውንም በግ ስብ፥ ላቱንም፥ የሆድ ዕቃውንም የሚሸፍነውን ስብ፥ ኵላሊቶቹንም፥ የጕበቱንም መረብ አመጡለት። 20ስቡንም በፍርምባዎቹ ላይ አደረጉ፥ ስቡንም በመሠዊያው ላይ አቃጠለ፤ 21እግዚአብሔርም ሙሴን እንዳዘዘው አሮን ፍርምባዎቹንና ቀኝ ወርቹን በእግዚአብሔር ፊት ለመወዝወዝ ቍርባን ወዘወዘ። 22አሮንም እጆቹን ወደ ሕዝቡ ዘረጋ ባረካቸውም፤ የኃጢያቱን የሚቃጠለውንም የደኅንነቱንም መሥዋዕት ከሠዋ በኋላ ወረደ። 23ሙሴና አሮንም ወደ መገናኛው ድንኳን ገቡ፤ ወጡም፥ ሕዝቡንም ባረኩ፤ የእግዚአብሔርም ክብር ለሕዝቡ ሁሉ ተገለጠ። 24እሳትም ከእግዚአብሔር ዘንድ ወጣ፥ በመሠዊያውም ላይ የሚቃጠለውን መሥዋዕት ስቡንም በላ፤ ሕዝቡም ሁሉ አይተው እልል አሉ፥ በግምባራቸውም ወደቁ።
Currently Selected:
ኦሪት ዘሌዋውያን 9: አማ54
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ