የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

ኦሪት ዘሌዋውያን 10

10
1የአሮንም ልጆች ናዳብና አብዩድ በየራሳቸው ጥናውን ወስደው እሳት አደረጉበት፥ በላዩም ዕጣን አኖሩበት፥ በእግዚአብሔርም ፊት እርሱ ያላዘዛቸውን ሌላ እሳት አቀረቡ። 2እሳትም ከእግዚአብሔር ፊት ወጥቶ በላቸው፥ በእግዚአብሔርም ፊት ሞቱ። 3ሙሴም አሮንን፦ እግዚአብሔር፦ ወደ እኔ በሚቀርቡ እቀደሳለሁ፥ በሕዝቡም ሁሉ ፊት እከብራለሁ ብሎ የተናገረው ይህ ነው አለው፤ አሮንም ዝም አለ። 4ሙሴም የአሮንን አጎት የዑዝኤልን ልጆች ሚሳኤልንና ኤልጻፋንን ጠርቶ፦ ቅረቡ፥ ወንድሞቻችሁንም ከመቅደሱ ፊት አንሥታችሁ ከሰፈር ወደ ውጭ ውሰዱአቸው አላቸው። 5እነርሱም ቀርበው አነሡአቸው፥ ሙሴም እንዳለ በቀሚሳቸው ከሰፈር ወደ ውጭ ወሰዱአቸው። 6ሙሴም አሮንን፥ ልጆቹንም አልዓዛርንና ኢታምርን፦ እንዳትሞቱ በማኅበሩም ሁሉ ላይ ቁጣ እንዳይወርድ ራሳችሁን አትንጩ፥ ልብሳችሁንም አትቅደዱ፤ እግዚአብሔር ስላቃጠለው ማቃጠል ግን ወንድሞቻችሁ የእስራኤል ቤት ሁሉ ያልቅሱ። 7የእግዚአብሔር የቅብዓት ዘይት በላያችሁ ነውና እንዳትሞቱ ከመገናኛው ድንኳን ደጃፍ አትወጡም አላቸው። እንደ ሙሴ ቃልም አደረጉ። 8እግዚአብሔርም አሮንን እንዲህ ብሎ ተናገረው፦ 9እንዳትሞቱ ወደ መገናኛው ድንኳን ስትገቡ አንተና ልጆችህ የወይን ጠጅና የሚያሰክርን ነገር ሁሉ አትጠጡ፤ ይህም ለልጅ ልጃችሁ የዘላለም ሥርዓት ይሆናል፤ 10በተቀደሰውና ባልተቀደሰው፥ በርኩሱና በንጹሑም መካከል ትለያላችሁ፤ 11እግዚአብሔርም በሙሴ ቃል የነገራቸውን ሥርዓት ሁሉ ለእስራኤል ልጆች ታስተምራላችሁ። 12ሙሴም አሮንን፥ የተረፉለትንም ልጆቹን አልዓዛርንና ኢታምርን አላቸው፦ ቅዱሰ ቅዱሳን ነውና ለእግዚአብሔር ከሆነው ከእሳት ቍርባን የቀረውን የእህሉን ቍርባን ውሰዱ፥ ቂጣም አድርጋችሁ በመሠዊያው አጠገብ ብሉት እግዚአብሔርም እንዲህ አዞኛልና፥ 13ለእግዚአብሔር ከሆነው ከእሳት ቍርባን ለአንተም ለልጆችህም የተሰጠ ሥርዓት ነውና በቅዱስ ስፍራ ትበሉታላችሁ። 14እነዚህም ከእስራኤል ልጆች ከደኅንነት መሥዋዕቶች ለአንተና ለልጆችህ ሥርዓት እንዲሆኑ ስለ ተሰጡ፥ የሚወዘወዘውን ፍርምባ፥ የሚነሣውንም ወርች አንተ፥ ከአንተ ጋርም ልጆችህ፥ ሴቶች ልጆችህም በንጹሕ ስፍራ ትበላላችሁ። 15የሚነሣውን ወርች የሚወዘወዘውንም ፍርምባ በእግዚአብሔር ፊት ለመወዝወዝ ቍርባን እንዲወዘውዙ የእሳት ቍርባን ከሆነው ስብ ጋር ያመጣሉ፤ እግዚአብሔር እንዳዘዘ ለአንተ ከአንተ ጋርም ለልጆችህ የዘላለም ሥርዓት ይሆናል። 16ሙሴም የኃጢያቱን መሥዋዕት ፍየል እጅግ ፈለገው፥ እነሆም ተቃጥሎ ነበር፤ ሙሴም የቀሩትን የአሮንን ልጆች አልአዛርንና ኢታምርን ተቆጥቶ፦ 17ቅዱሰ ቅዱሳን ነውና፥ የሕዝቡንም ኃጢያት እንድትሸከሙ፥ በእግዚአብሔርም ፊት እንድታስተሰርዩላቸው ለእናንተ ጥቶታልና ስለ ምን የኃጢያትን መሥዋዕት በቅዱሱ ስፍራ አልበላችሁም? 18እነሆ ደሙን ወደ መቅደሱ ውስጥ አላገባችሁትም፤ እኔ እንዳዘዝሁ በቅዱሱ ስፍራ ውስጥ ትበሉት ዘንድ ይገባችሁ ነበር አላቸው። 19አሮንም ሙሴን፦ እነሆ ዛሬ የኃጢያታቸውን መሥዋዕት፥ የሚቃጠለውንም መሥዋዕታቸውን በእግዚአብሔር ፊት አቀረቡ፤ ይህም ሁሉ ደረሰብኝ፤ ዛሬስ የኃጢያት መሥዋዕት በበላሁ ኖሮ በእግዚአብሔር ፊት መልካም ኖሮአልን? አለው። 20ሙሴም ሰማ በፊቱም መልካም ሆነ።

ማድመቅ

Share

Copy

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ