ከዚህም በኋላ ሙሴ ስለ ኃጢአት ስርየት መሥዋዕት የሚቀርበውን ኰርማ አመጣ፤ አሮንና ልጆቹ በኰርማው ራስ ላይ እጃቸውን ጫኑ፤ ሙሴም ዐረደው፤ ከደሙም ጥቂት በጣቱ ነክሮ የመሠዊያውን አራት ማእዘን ጒጦች በመቀባት አንጽቶ ቀደሰው፤ ከዚያም የተረፈውን ደም በመሠዊያው ሥር አፈሰሰው፤ በዚህም ዐይነት መሠዊያውን ለእግዚአብሔር በመለየት አነጻው፤ ሙሴ በእንስሳው ሆድ ዕቃ ላይ ያለውን ስብ ሁሉ፥ ጒበቱን እንደ መረብ ሆኖ የሚሸፍነው ስብ፥ ኲላሊቶቹንና በእነርሱ ላይ ያለውን ስብ ወስዶ፥ ሁሉንም በመሠዊያው ላይ አቃጠለው። ከኰርማው የቀረውንም ቆዳውን፥ ሥጋውንና አንጀቱን ወስዶ፥ እግዚአብሔር ባዘዘውም መሠረት ከሰፈር ውጪ አውጥቶ አቃጠለው። ከዚያም በኋላ ሙሴ ለሚቃጠል መሥዋዕት የሚቀርበውን የበግ አውራ አመጣ፤ አሮንና ልጆቹ በአውራው በግ ራስ ላይ እጆቻቸውን ጫኑ፤ ሙሴም ዐረደው፤ ደሙንም በመሠዊያው አራት ማእዘን ረጨ፤ የበግ አውራውንም ሥጋ በየብልቱ ቈራረጠ፤ ጭንቅላቱን፥ ብልቶቹንና ስቡን አቃጠለ። እግዚአብሔር ባዘዘው መሠረት ሙሴ የሆድ ዕቃዎቹንና እግሮቹን አጥቦ የአውራ በጉን ሥጋ ሁሉ በመሠዊያው ላይ የሚቃጠል መሥዋዕት አድርጎ አቃጠለው፤ ይህም ለእግዚአብሔር ደስ የሚያሰኝ መዓዛ ነበር። ሙሴም እንደገና ስለ ክህነት ሹመት የሚቀርበውን ሁለተኛውን አውራ በግ አመጣ፤ አሮንና ልጆቹ እጆቻቸውን በራሱ ላይ ጫኑ፤ ሙሴ ዐረደው፤ ከደሙም ጥቂት ወስዶ የአሮንን የቀኝ ጆሮውን ጫፍ፥ የቀኝ እጁን አውራ ጣት፥ የቀኝ እግሩንም አውራ ጣት ቀባ፤ ቀጥሎም የአሮንን ልጆች ወደ ፊት አቅርቦ የቀኝ ጆሮዎቻቸውን ጫፎች፥ የቀኝ እጆቻቸውን አውራ ጣቶችና የቀኝ እግሮቻቸውን አውራ ጣቶች ቀባ፤ ከዚህ የተረፈውንም ደም ሙሴ በመሠዊያው ጐን በአራቱም ማእዘን ረጨው።
ኦሪት ዘሌዋውያን 8 ያንብቡ
ያጋሩ
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: ኦሪት ዘሌዋውያን 8:14-24
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
ቤት
መጽሐፍ ቅዱስ
እቅዶች
ቪዲዮዎች