ዘሌዋውያን 8:14-24

ዘሌዋውያን 8:14-24 NASV

ሙሴም የኀጢአት መሥዋዕት የሆነውን ወይፈን አመጣ፤ አሮንና ልጆቹም በወይፈኑ ራስ ላይ እጃቸውን ጫኑ። ሙሴም ወይፈኑን ዐረደ፤ ደሙንም ወስዶ መሠዊያውን ያነጻ ዘንድ በጣቱ የመሠዊያውን ቀንዶች ሁሉ ቀባ፤ የቀረውንም ደም ከመሠዊያው ሥር አፈሰሰው። ለመሠዊያውም እንዲህ አድርጎ ያስተሰርይለት ዘንድ ቀደሰው። ሙሴም የሆድ ዕቃውን የሚሸፍነውን ሥብ ሁሉ፣ የጕበቱን ሽፋን፣ ኵላሊቶችንና ሥባቸውን ወስዶ በመሠዊያው ላይ አቃጠለ። ሙሴም እግዚአብሔር ባዘዘው መሠረት ወይፈኑን፣ ቈዳውን፣ ሥጋውንና ፈርሱን ከሰፈር ውጭ አቃጠለ። ሙሴ ለሚቃጠል መሥዋዕት የሚሆነውን አውራ በግ አቀረበ፤ አሮንና ልጆቹም እጃቸውን በበጉ ላይ ጫኑ። ሙሴም በጉን ዐርዶ ደሙን በመሠዊያው ላይ ዙሪያውን ረጨ። በጉንም በየብልቱ ቈራረጠ፤ ሙሴም ጭንቅላቱን፣ ብልቶቹንና ሥቡን አቃጠለ። ሆድ ዕቃውንና እግሮቹን በውሃ አጠበ፤ ሙሴም እግዚአብሔር ባዘዘው መሠረት፣ በጉን በሙሉ ለእግዚአብሔር በእሳት የሚቀርብ፣ ሽታውም ደስ የሚያሰኝ የሚቃጠል መሥዋዕት አድርጎ በመሠዊያው ላይ አቃጠለው። ሙሴ ለቅድስና የሚሆነውን ሌላ አውራ በግ አቀረበ፤ አሮንና ልጆቹም እጆቻቸውን በበጉ ራስ ላይ ጫኑ። ሙሴ አውራ በጉን ዐረደ፤ ከደሙም ጥቂት ወስዶ የአሮንን ቀኝ ጆሮ ጫፍ፣ የቀኝ እጁን አውራ ጣትና የቀኝ እግሩን አውራ ጣት አስነካ፤ የአሮንንም ልጆች ወደ ፊት ጠራ፤ ሙሴም ከደሙ ጥቂት ወስዶ የቀኝ ጆሯቸውን ጫፍ፣ የቀኝ እጃቸውን አውራ ጣትና የቀኝ እግራቸውን አውራ ጣት አስነካ፤ የቀረውንም ደም በመሠዊያው ላይ ዙሪያውን ረጨ።