ኦሪት ዘሌዋውያን 8
8
የአሮንና የልጆቹ የክህነት ሹመት
(ዘፀ. 29፥1-37)
1እግዚአብሔር ሙሴን እንዲህ አለው፤ 2“አሮንንና ወንዶች ልጆቹን እንዲሁም የክህነት ልብሱን፥ የቅባቱን ዘይት፥ ስለ ኃጢአት ስርየት መሥዋዕት የሚቀርበውን ኰርማ ሁለቱን የበግ አውራዎች፥ እርሾ ያልነካው ቂጣ ያለበትን መሶብ፥ አብረህ አምጣ፤ 3ከዚያም የእስራኤልን ሕዝብ በመገናኛው ድንኳን ደጃፍ ሰብስብ።”
4ሙሴም እግዚአብሔር እንዳዘዘው አደረገ፤ ሕዝቡም ተሰበሰበ፤ 5ሙሴም “እግዚአብሔር እንዲደረግ ያዘዘው ነገር ይህ ነው” አላቸው።
6ሙሴም አሮንንና ወንዶች ልጆቹን አቅርቦ በውሃ አጠባቸው፤ 7አሮንን ቀሚስ አልብሶ፥ ካባ ደርቦ፥ መታጠቂያ አስታጠቀው፤ በዚያም ላይ ኤፉድ አደረገለት፤ እርሱንም በልዩ ጥበብ በተጠለፈ ቀበቶ አያይዞ በወገቡ ዙሪያ አሰረለት፤ 8በኤፉዱም ላይ የደረት ኪስ ሰፍቶ የእግዚአብሔር ፈቃድ የሚገለጥባቸውን ኡሪምና ቱሚምን አኖረ፤ #8፥8 እና 8 ስለ ዑሪምና ቱሚም እንዲሁም ኤፉድ በኦሪት ዘጸአት ም. 29 ይመለከቷል። 9በራሱም ላይ ጥምጥም አደረገለት፤ በጥምጥሙም ላይ ከፊት ለፊት በኩል እግዚአብሔር ሙሴን ባዘዘው መሠረት በወርቅ አጊጦ የተሠራውን የቅድስና ምልክት የሆነውን አክሊል አኖረ።
10ከዚህም ቀጥሎ ሙሴ የቅባቱን ዘይት ወስዶ የተቀደሰውን ድንኳንና በውስጡ ያሉትንም ነገሮች ቀባ፤ በዚህ ዐይነት ሁሉንም ለእግዚአብሔር አገልግሎት የተለየ እንዲሆን አደረገው፤ 11ከዘይቱም ጥቂት ወስዶ በመሠዊያው ላይ ሰባት ጊዜ ረጨ፤ በዚሁ ዐይነት ለእግዚአብሔር አገልግሎት የተለዩ ይሆኑ ዘንድ በመሠዊያውና ለእርሱ መገልገያ በተሠሩት ዕቃዎች ሁሉ ላይ እንዲሁም በመታጠቢያው ሳሕንና በሳሕኑ ማስቀመጫ ላይ ረጨ። 12የቅባቱንም ዘይት በአሮን ራስ ላይ በማፍሰስ ቀብቶ ለእግዚአብሔር አገልግሎት የተለየ በማድረግ የክህነት ሹመት ሰጠው፤ 13ቀጥሎም ሙሴ እግዚአብሔር ባዘዘው መሠረት የአሮንን ወንዶች ልጆች ወደፊት አቅርቦ ቀሚስ አለበሳቸው፤ በወገባቸውም ዙሪያ መታጠቂያ አድርጎ በራሳቸውም ላይ ቆብ ደፋላቸው።
14ከዚህም በኋላ ሙሴ ስለ ኃጢአት ስርየት መሥዋዕት የሚቀርበውን ኰርማ አመጣ፤ አሮንና ልጆቹ በኰርማው ራስ ላይ እጃቸውን ጫኑ፤ 15ሙሴም ዐረደው፤ ከደሙም ጥቂት በጣቱ ነክሮ የመሠዊያውን አራት ማእዘን ጒጦች በመቀባት አንጽቶ ቀደሰው፤ ከዚያም የተረፈውን ደም በመሠዊያው ሥር አፈሰሰው፤ በዚህም ዐይነት መሠዊያውን ለእግዚአብሔር በመለየት አነጻው፤ 16ሙሴ በእንስሳው ሆድ ዕቃ ላይ ያለውን ስብ ሁሉ፥ ጒበቱን እንደ መረብ ሆኖ የሚሸፍነው ስብ፥ ኲላሊቶቹንና በእነርሱ ላይ ያለውን ስብ ወስዶ፥ ሁሉንም በመሠዊያው ላይ አቃጠለው። 17ከኰርማው የቀረውንም ቆዳውን፥ ሥጋውንና አንጀቱን ወስዶ፥ እግዚአብሔር ባዘዘውም መሠረት ከሰፈር ውጪ አውጥቶ አቃጠለው።
18ከዚያም በኋላ ሙሴ ለሚቃጠል መሥዋዕት የሚቀርበውን የበግ አውራ አመጣ፤ አሮንና ልጆቹ በአውራው በግ ራስ ላይ እጆቻቸውን ጫኑ፤ 19ሙሴም ዐረደው፤ ደሙንም በመሠዊያው አራት ማእዘን ረጨ፤ 20የበግ አውራውንም ሥጋ በየብልቱ ቈራረጠ፤ ጭንቅላቱን፥ ብልቶቹንና ስቡን አቃጠለ። 21እግዚአብሔር ባዘዘው መሠረት ሙሴ የሆድ ዕቃዎቹንና እግሮቹን አጥቦ የአውራ በጉን ሥጋ ሁሉ በመሠዊያው ላይ የሚቃጠል መሥዋዕት አድርጎ አቃጠለው፤ ይህም ለእግዚአብሔር ደስ የሚያሰኝ መዓዛ ነበር።
22ሙሴም እንደገና ስለ ክህነት ሹመት የሚቀርበውን ሁለተኛውን አውራ በግ አመጣ፤ አሮንና ልጆቹ እጆቻቸውን በራሱ ላይ ጫኑ፤ 23ሙሴ ዐረደው፤ ከደሙም ጥቂት ወስዶ የአሮንን የቀኝ ጆሮውን ጫፍ፥ የቀኝ እጁን አውራ ጣት፥ የቀኝ እግሩንም አውራ ጣት ቀባ፤ 24ቀጥሎም የአሮንን ልጆች ወደ ፊት አቅርቦ የቀኝ ጆሮዎቻቸውን ጫፎች፥ የቀኝ እጆቻቸውን አውራ ጣቶችና የቀኝ እግሮቻቸውን አውራ ጣቶች ቀባ፤ ከዚህ የተረፈውንም ደም ሙሴ በመሠዊያው ጐን በአራቱም ማእዘን ረጨው። 25ስቡን፥ ላቱን፥ ሆድ ዕቃውን የሚሸፍነውን ስብ ሁሉ፥ እንደ መረብ ሆኖ ጒበቱን ከሚሸፍነው ስብ ምርጥ የሆነውን ክፍል፥ ኲላሊቶቹን፥ በእነርሱ ላይ ያለውን ስብና በቀኝ በኩል ያለውን ወርች ወሰደ፤ 26በእግዚአብሔር ፊት ካለው እርሾ ያልነካው ቂጣ ከሚቀመጥበትም መሶብ አንድ ኅብስት ወሰደ፤ እንዲሁም በዘይት የታሸ አንድ ኅብስትና አንድ ስስ ቂጣ ወስዶ በስቡና በቀኝ እግሩ ላይ አኖረው፤ 27ይህን ሁሉ ምግብ ወስዶ ለአሮንና ለልጆቹ በእጃቸው አስያዛቸው፤ አነርሱም በመወዝወዝ ለእግዚአብሔር ልዩ መባ አድርገው አቀረቡት። 28ከዚህ በኋላ ሙሴ ምግቡን ከእነርሱ ወሰደ፤ ስለ ክህነት ሹመት መባ እንዲሆን በሚቃጠል መሥዋዕት መሠዊያ ላይ አድርጎ አቃጠለው፤ ይህም መዓዛው እግዚአብሔርን ደስ የሚያሰኝ የምግብ ቊርባን ነበር። 29ቀጥሎም ሙሴ ፍርምባውን ወስዶ በመወዝወዝ ለእግዚአብሔር ልዩ መባ አድርጎ አቀረበ፤ ስለ ክህነት ሹመት ከሚቀርበው የበግ አውራ የሙሴ ድርሻ ይህ ነበር።
30ሙሴ ከቅባት ዘይት ጥቂት እና በመሠዊያው ላይ ከነበረውም ከደሙ ጥቂት ወስዶ በአሮንና በልጆቹ እንዲሁም በልብሳቸው ሁሉ ላይ ረጨው፤ በዚህም ሁኔታ ሙሴ እነርሱንና ልብሶቻቸውን ለእግዚአብሔር የተለዩ አደረገ።
31“ሙሴም አሮንንና ልጆቹን እንዲህ አላቸው፤ ሥጋውን በመገናኛው ድንኳን ደጃፍ ቀቅሉት፤ አሮንና ልጆቹ ይብሉት ብዬ እንዳዘዝኩት ያን በመሶብ ውስጥ ካለው የተቀደሰ ኅብስት ጋር ብሉት። 32የተረፈ ሥጋም ሆነ ዳቦ ቢኖር በእሳት አቃጥሉት፤ 33የክህነት ሹመታችሁን ሥርዓት ለመፈጸም ሰባት ቀን ስለሚወስድ ይኸው ሥርዓት እስከሚፈጸምበት እስከ ሰባት ቀን ድረስ ከመገናኛው ድንኳን ደጃፍ አትወጡም። 34ኃጢአታችሁን ለማስወገድ ይህን ዛሬ ያደረግነውን ሥርዓት እንድንፈጽም እግዚአብሔር አዞናል፤ 35ስለዚህም እግዚአብሔር ያዘዘውን ሁሉ በመፈጸም ሰባት ቀን ሙሉ ሌሊትና ቀን በመገናኛው ድንኳን ደጃፍ ትቈያላችሁ፤ ይህን ባታደርጉ ግን ትሞታላችሁ፤ ይህ እግዚአብሔር ያዘዘኝ ሕግ ነው።” 36አሮንና ልጆቹም በሙሴ አማካይነት እግዚአብሔር ያዘዘውን ሁሉ ፈጸሙ።
Currently Selected:
ኦሪት ዘሌዋውያን 8: አማ05
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ
© The Bible Society of Ethiopia, 2005
© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997