ኦሪት ዘሌዋውያን 7:11-38

ኦሪት ዘሌዋውያን 7:11-38 አማ54

ሰው ለእግዚአብሔር የሚያቀርበው የደኅንነት መሥዋዕት ሕግ ነው። ለምስጋና ቢያቀርበው፥ ከምስጋናው መሥዋዕት ጋር በዘይት የተለወሰ የቂጣ እንጎቻ፥ በዘይትም የተቀባ ስስ ቂጣ፥ በዘይትም የተለወሰ መልካም ዱቄት ያቀርባል። ለምስጋና የሚሆነውን የደኅንነት መሥዋዕት ባቀረበ ጊዜ እርሾ ያለበትን ኅብስት ያቀርባል። ከቍርባኑም ሁሉ ለእግዚአብሔር የማንሣት ቍርባን እንዲሆን ከእነርሱ አንዱን ያነሣል። እርሱም የደኅንነትን መሥዋዕት ደም ለሚረጨው ካህን ይሆናል። ለምስጋና የሚሆነው የደኅንነት መሥዋዕት ሥጋ በሚቀርብበት ቀን ይበሉታል፤ ከእርሱ እስከ ነገ ምንም አያድርም። የቁርባኑም መሥዋዕት የስእለት ወይም የፈቃድ ቢሆን፥ መሥዋዕቱ በሚቀርብበት ቀን ይብሉት፤ ከእርሱም የቀረውን በነጋው ይብሉት፤ ከመሥዋዕቱም ሥጋ እስከ ሦስተኛው ቀን የሚቆየው በእሳት ይቃጠላል። በሦስተኛው ቀን ከደኅንነት መሥዋዕት ሥጋ ቢበላ፥ አይሠምርም ላቀረበው ሰው የተጠላ ይሆንበታል እንጂ ቁርባን ሆኖ አይቈጠርለትም፤ ከእርሱም ቢበላ ኃጢአቱን ይሸከማል። ርኩስ ነገር የሚነካውን ሥጋ አይብሉት፤ በእሳት ይቃጠል። ንጹሕ የሆነ ሰው ሁሉ ግን ከሥጋው ይብላ። ሰውም የረከሰ ቢሆን፥ ለእግዚአብሔርም ከሆነው ከደኅንነት መሥዋዕት ሥጋ ቢበላ፥ ያ ሰው ከሕዝቡ ተለይቶ ይጥፋ። ማናቸውንም ርኩስ ነገር ቢነካ፥ የሰውን ወይም የረከሰን እንስሳ ወይም ሌላውን የተጠላ ርኩስን ቢነካ፥ ለእግዚአብሔርም ከሆነው ከደኅንነት መሥዋዕት ሥጋ ቢበላ፥ ያ ሰው ከሕዝቡ ተለይቶ ይጥፋ። እግዚአብሔርም ሙሴን እንዲህ ብሎ ተናገረው፦ የእስራኤልን ልጆች እንዲህ ብለህ ተናገራቸው፦ የበሬ ወይም የበግ ወይም የፍየል ስብ ከቶ አትብሉ። የሞተውን ስብ፥ አውሬ የሰበረውንም ስብ ለሌላ ተግባር አድርጉት፤ ነገር ግን ከእርሱ ምንም አትብሉ፤ ለእግዚአብሔር በእሳት ከሚቀርበው ከእንስሳ ስብ የሚበላ ሁሉ፥ ያ የበላ ሰው ከሕዝቡ መካከል ተለይቶ ይጠፋልና። በማደሪያዎቻችሁም ሁሉ የወፍ ወይም የእንስሳ ደም ቢሆን አትብሉ። ደም የሚበላ ሰው ሁሉ ያ ሰው ከሕዝቡ መካከል ተለይቶ ይጥፋ። እግዚአብሔርም ሙሴን እንዲህ ብሎ ተናገረው፦ የእስራኤልን ልጆች እንዲህ ብለህ ተናገራቸው፦ ለእግዚአብሔር የደኅንነት መሥዋዕት የሚያቀርብ ሰው ቁርባኑን ለእግዚአብሔር ከደኅንነቱ መሥዋዕት ያመጣል። የእርሱ እጆች ለእግዚአብሔር የእሳቱን ቁርባን ያመጣሉ፤ ፍርምባው በእግዚአብሔር ፊት ለመወዝወዝ ቁርባን ይወዘውዝ ዘንድ ስቡንና ፍርምባውን ያመጣል። ካህኑም ስቡን በመሠዊያው ላይ ያቃጥላል፤ ፍርምባውም ለአሮንና ለልጆቹ ይሁን። ከደኅንነት መሥዋዕታችሁ ቀኝ ወርቹን ለማንሣት ቁርባን እንዲሆን ለካህኑ ትሰጡታላችሁ። ከአሮንም ልጆች የደኅንነትን መሥዋዕት ደሙንና ስቡን ለሚያቀርብ ለእርሱ ቀኝ ወርቹ እድል ፈንታው ይሆናል። የሚወዘወዘውን ፍርምባና የሚነሣውን ወርች ከእስራኤል ልጆች ከደኅንነት መሥዋዕታቸው ወስጄአለሁ፥ ለካህኑ ለአሮንና ለልጆቹም ለዘላለም እድል ፈንታ እንዲሆን ከእስራኤል ልጆች ዘንድ ሰጥቼአቸዋለሁ። እግዚአብሔርን በክህነት ያገለግሉት ዘንድ ባቀረባቸው ቀን ለእግዚአብሔር ከሆነ ከእሳት ቁርባን የአሮንና የልጆቹ እድል ፈንታ ይህ ነው። ለልጅ ልጃቸው ለዘላለም እድል ፈንታቸው እንዲሆን በቀባቸው ቀን የእስራኤል ልጆች ይሰጡአቸው ዘንድ እግዚአብሔር ያዘዘው ይህ ነው። የሚቃጠል መሥዋዕትና የእህል ቁርባን፥ የኃጢአትና የበደል መሥዋዕት፥ የቅድስናና የደኅንነት መሥዋዕት ሕግ ይህ ነው። እግዚአብሔር በሲና ምድረ በዳ ቁርባናቸውን ለእግዚአብሔር ያቀርቡ ዘንድ ለእስራኤል ልጆች ባዘዘ ጊዜ በሲና ተራራ ለሙሴ ያዘዘው ይህ ነው።